ፈልግ

"ሴት መሪዎች እና ብሩህ የወደፊት ጊዜ" "ሴት መሪዎች እና ብሩህ የወደፊት ጊዜ" 

ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመጠቆም ሴቶች ቁልፍ የመሪነት ሚናን እንደሚጫወቱ ተገለጸ

ከዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ጋር በመተባበር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ አምባሳደሮች እና ባለሙያዎች፥ "ሴት መሪዎች እና ብሩህ የወደፊት ጊዜ" በሚል ርዕሥ የአንድ ቀን ስብሰባ ለማካሄድ በሮም ተሰብስበዋል። በስብሰባው ከዓለም ዙሪያ የመጡ ባለሞያዎች በንግግራቸው ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሴቶች የአመራር ሚና አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም የሚገኙ የልዩ ልዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እና ሊቃውንት ያካሄዱት አቀፉዊ ስብሰባ፥ የሴቶች አመራር በሁሉም ዘርፍ ያለውን ጠቀሜታ ለማሳየት እና ለማስተዋወቅ እንዲሁም የወቅቱን ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት የተሻለ ዓለምን ለመገንባት የሚያስችል አስፈላጊ እና ወሳኝ አስተዋፅዖ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

የሴቶች አመራር ለብሩህ የወደፊት ሕይወት

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 2024 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዝግጅት አካል የሆነው የቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ኮንፌዴሬሽን “ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ”፣ በቅድስት መንበር የአውስትራሊያ እና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች በመተባበር ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ስብሰባ ረቡዕ የካቲት 27/2016 ዓ. ም. አካሂደዋል። “የሴቶች አመራር ለብሩህ የወደፊት ሕይወት” በሚል መርህ የተዘጋጀው የአንድ ቀን ስብሰባ በማዕከላዊ ሮም በሚገኘው የኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት ተካሂዷል።

የፓናል ውይይቶቹ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶችን አቅም ማጎልበት እና የእምነት ቤቶች እና የመንግሥት ተዋናዮች በመካከላቸው እንዴት ትብብርን ማሳደግ እንደሚችሉ በሚለው ላይ ተወያይተዋል። ትምህርትን፣ ኢኮኖሚን እና ክህሎትን ማጎልበት ሴቶች መሪዎችን በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መስኮች ውስጥ እንዴት ማፍራት እንደቻለ ባለሙያዎች የተለያዩ የስኬት ታሪኮችን ጠቅሰው ተወያይተዋል።

በስብሰባው ላይ ንግግር ካደረጉት መካከል የዓለም አቀፍ ገዳማውያት ኅብረት ጠቅላይ ጸሐፊ እህት ፓትሪሲያ ሙሬይ እና የኢየሱሳውያን ማኅበር የበላይ አለቃ አባ አርቱሮ ሶሳ አባስካል ይገኙበታል። ከቫቲካን ተወካዮች መካከል የሲኖዶስ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤኳርት እና በቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን ሙራይ ይገኙበታል። ከአውስትራሊያ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ፕሮፌሰር ሜቭ ሄኒን ጨምሮ ሴት የነገረ መልኮት ምሁራንም ተገኝተዋል። ከደቡብ አፍሪካ የቅዱስ ኦገስቲን ኮሌጅ የመጡ ዶ/ር ኖንታዶ ሃዴቤ እና ከሞሪሸስ፣ ህንድ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሜክሲኮ የመጡ የሴቶች ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል።

ለተሻለ የወደፊት ተሳትፎ

በቅድስት መንበር የብሪታንያ አምባሳደር ክሪስቶፈር ትሮት፥ የተሻለ የወደፊት ሕይወትን ለመገንባት እና ዓለም ዛሬ ላጋጠማት ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት ሴቶች ወሳኝ እንደሆኑ ገልጸው፥ ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሁሉም ሰው የሚጠቀምበት አረንጓዴ እና የበለጸገ ዓለምን ለመገንባት ሴቶች እና ልጃገረዶች የጥረታችን ዋና አካል ሆነው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ለውጥን ለማምጣት የሚያግዝ ልዩነት

በቅድስት መንበር የአውስትራሊያ አምባሳደር ኪያራ ፖሮ፥ ሴቶች እና ልጃገረዶች በጾታዊ ልዩነታቸው ዛሬ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ዋና ተዋናይ እንደሆኑ አስምረው፥ የእነዚህ ተዋናዮች ዕውቀት እና ልምድን በአመራር ደረጃም መጠቀም አለብን ብለዋል። መሰናክሎችን እና ተግዳሮቶችን ማሸነፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ከጾታ ልዩነት ባሻገር ሁሉም ሰው የአቅሙን ማበርከት የሚችልበት የተሻለ ዓለምን መገንባት አገራቸው የገባችበት የቁርጠኝነት አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

የቆዩ እና አዳዲስ እንቅፋቶችን ማሸነፍ

የስብሰባው ተባባሪ አዘጋጅ እና የ “ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ” ዋና ጸሐፊ አሊስታይር ዱተን በበኩላቸው፥ ድህነት፣ አመጽ እና የትምህርት እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እጦት ለሴቶች ተሳትፎ ማነስ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ በመሆናቸው መስተካከል እንዳለባቸው አስታውሰዋል። ለዚህም ነው “ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ” ከ200 በሚበልጡ አገራት እና ክልሎች ውስጥ ከሕዝባዊ አካላት ጋር በመሆን የሴቶችን አቅም፣ ትምህርት እና ተሳትፎን፣ በየደረጃው ያለውን የአመራር እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በማስፋፋት ሁሉንም ዓይነት መሰናክሎች ለማሸነፍ እና የሴቶች ልምድ እና ዕውቀት ዋጋ ያለው እንደሆነ፣ ብሩህ የወደፊት ሕይወት መገንባት እንደሚቻል ለማሳየት እንደሚሠራ አስረድተዋል።

07 March 2024, 13:24