ፈልግ

PHILIPPINES RELIGION HOLY ROSARY

እምቢ ለመንፈሳዊ ዓለማዊነት

ከሃይማኖተኛነት ገጽታና ከቤተክርስቲያን ፍቅር ጀርባ ተሸሽጎ የሚገኘው መንፈሳዊ ዓለማዊነት የጌታን ክብር ሳይሆን የሰውን ክብርና የግል ደህንነትን ይፈልጋል። ይህም ጌታ “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” (ዮሐ.5፡44) በማለት ፈሪሳዊያንን የነቀፈበት ምግባር ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ “የኢየሱስን ሳይሆን የራስን ጥቅም” (ፊልጵ.2፡21) የመፈለግ ዓይነተኛ መንገድ ነው። ዓለማዊ መንፈሳዊነት ሰርጎ እንደሚገባባቸው ሰዎችና ቡድኖች ሁኔታ የተለያዩ መልኮች ይኖሩታል። በጥንቃቄ በዳበሩ ገጽታዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሁልጊዜ ከውጫዊ ኃጢአት ጋር አይያያዝም፤ ከውጭ ሲታይ ሁሉም ነገር መሆን በሚገባው መልኩ የሆነ ይመስላል። ነገር ግን፣ ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰርጎ ሲገባ “ግብረ ገባዊ ብቻ ከሆነ ሌላ ማናቸውም ዓይነት ዓለማዊነት ይበልጥ አደገኛ ይሆናል”።

ይህ ዓለማዊነት በጥብቅ በተያያዙ በሁለት መንገዶች ሊባባስ ይችላል። አንዱ ቁሳዊ ዓለምን ስለ መጥላትና መንፈሳዊ ዓለምን ስለ መቀበል የሚያስተምር ኖስቲስዝም የሚባል ፍልስፍና ማራኪነት ነው። ይህ ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ በግል እምነት ላይ የተመሠረተ፣ የማጽናናትና የማሳወቅ ዓላማ ባላቸው፣ ነገር ግን፣ ሰውን የገዛ ራሱ ሃሳቦች ባሪያ በሚያደርጉ በተወሰነ ተሞክሮ ወይም የሀሳቦች ስብስብና ቅንጭብ መረጃዎች ላይ ያተኮረ ነው። ሌላው የራሳቸውን ኃይል ብቻ የሚያምኑና አንዳንድ ሕጎችን ስለሚጠብቁ ወይም ከጥንት የመጣ አንድ ልዩ ካቶሊካዊ ዘዴን የሙጥኝ ብለው ስለሚያምኑ ከሌሎች የበለጡ የሚመስላቸው በራሳቸው ሃሳብ የተጠመዱ (ፕሮሜትያን ኒዮፔላጅያኒዝም አስተሳሰብ ያላቸውን) ሰዎች ይመለከታል። ይህ ትምህርት ወይም የትምህርት ዘርፍ አንድን ሰው ወንጌልን ከመስበክ ይልቅ ሌሎችን ወደሚተነትንበትና ወደሚፈርጅበት፣ ለጸጋ በር ከመክፈት ይልቅ የራሱን ጉልበት በመፈተሽና በማረጋገጥ ሥራ ላይ ወደሚያባክንበትና ራስን ወደሚያመልክበት  ፈላጭ ቆራጭ ልሂቅነት የሚመራ ነው። ከነዚህ ሁሉ አንዳቸውም በሐቅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም ስለ ሌሎች ሰዎች አይጨነቁም። እነዚህም የሰው ልጅ በተፈጥሮው የልዕልና ባህርያት አሉት ብሎ የማመን (የአንትሮፖስንትሪክ እማኔንትዝም) መገለጫዎች ናቸው። ከእነዚህ የተበረዙ የክርስትና ዓይነቶች  ውስጥ እውነተኛ የስብከተ ወንጌል ታማንነት ይወጣል ተብሎ ማሰብ አይቻልም።

ይህ ተንኮለኛ ዓለማዊነት ተቃራኒ የሚመስሉ፣ ነገር ግን፣ “የቤተክርስቲያንን ቦታ የመውሰድ” ተመሳሳይ ሽንገላ ባላቸው አያሌ አስተሳሰቦች ይገለጻል። በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ለሥርዓተ አምልኮ፣ ለቤተክርስቲያን ትምህርትና ለቤተክርስቲያን ክብር የይስሙላ አሳብ እንዳለ እንገነዘባለን። ነገር ግን፣ አለማዊነት ወንጌል ለሕዝበ እግዚአብሔር ስላለው ተጨባጭ ውጤትና ስለ አሁኑ ዘመን ተጨባጭ ፍላጎቶች   አይጨነቅም። በዚህ አካሄድ፣ የቤተክርስቲያን ሕይወት ወደ ቤተመዘክር ዕቃነት ወይም የጥቂት ምርጦች ንብረት ወደመሆን ይቀየራል። በሌሎች ዘንድ ደግሞ ይህ መንፈሳዊ ዓለማዊነት ከማህበራዊና ፖለቲካዊ ትርፍ፣ ወይም ተጨባጭ ነገሮችን ከመቆጣጠር ችሎታቸው፣ ወይም ከራስ አገዝና ከራስ ጥረት ስኬታማ ከሆኑ ፕሮግራሞች ማራኪነት በስተጀርባ ተሸሽጎ ይገኛል። እንደዚሁም በዐይን ወደሚታይ ጭንቀት፣ በታይታዎች፣ በስብሰባዎች፣ በእራት ግብዣዎችና በመስተንግዶዎች ወደተሞላ ማኅበራዊ ሕይወት ሊለወጥ ይችላል። ዋና ተጠቃሚዎቹ  ሕዝበ እግዚአብሔር ሳይሆኑ፣ ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም ብቻ ተጠቃሚ ወደምትሆንባቸው፣ በአስተዳደራዊ ሥራዎች፣ በስታትስቲክስ፣ በዕቅድና ግምገማ ወደተጠመደ የንግድ አስተሳሰብም ሊመራ ይችላል። ሥጋ የለበሰው፣ የተሰቀለውና ከሙታን ተለይቶ የተነሣው የክርስቶስ ምልክት  በውስጡ የለበትም፤ ለሌሎች ዝግ የሆኑ ጥቂት ቡድኖች ብቻ ይፈጠራሉ። ሩቅ ወዳሉት ወይም ክርስቶስን ወደተጠሙ ብዙሃን ለመሄድ ምንም ጥረት አይደረግም። የወንጌል የጋለ ስሜት በባዶ የራስ እርካታና የፈለጉትን በማድረግ ስሜት ይተካል።

ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ትንሽ ሥልጣን ያላቸውና በመዋጋት ላይ የሚገኙ የጦር ክፍሎች ተራ አባል ከመሆን ይልቅ የተሸነፈ ጦር ሠራዊት ጄነራል መሆንን የሚመርጡ ሰዎችን ግብዝነት ይጨምራል። እንደ ተሸነፉ ጄኔራሎች በጥንቃቄ የታቀዱ ሰፊ ሐዋርያዊ ፕሮጀክቶችን ስንት ጊዜ ተመኘን! ይህማ የመሥዋዕትነት፣ የተስፋና የዕለታዊ ትግል፣ እንዲሁም በአገልግሎትና በሥራ ታማኝነት ያለፈውንና  ክቡር የሆነውን የቤተክርስቲያን ታሪካችንን መካድ ነው። ምከንያቱም ምንም ያህል አድካሚ ቢሆን፣ ሥራ ሁሉ “የፊታችን ወዝ “ ነውና።  እኛ ግን “ምን መደረግ አለበት” እያልን ጊዜ እናጠፋለን። ይህም ከላይ ሆነው ትዕዛዝ የሚሰጡ የመንፈሳዊ ጌቶችና ሐዋርያዊ ባለሙያዎች ኃጢአት ነው ማለት እንችላለን። መጨረሻ በሌላቸው ቅዠቶች ውስጥ ስለምንገባ ከሕዝባችን ተጨባጭ ኑሮና ችግሮች ጋር ግንኙነት አይኖረንም።

ወደዚህ ዓለማዊነት የወረዱ ሰዎች ከላይና ከሩቅ ሆነው ይመለከታሉ፤ የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ትንቢት አይቀበሉም፤ ጥያቄ የሚያነሡትን ያዋርዳሉ፤ ሁልጊዜ የሌሎችን ስህተቶች ይጠቁማሉ፣ በታይታ ይማረካሉ። ልባቸውን በራሳቸው ባህርይና ጥቅም ልክ ይከፍታሉ፣ ከዚህም የተነሣ ከኃጢአታቸው ከቶ አይማሩም፣ በሐቅ ይቅርታ ለማድረግም ዝግጁ አይደሉም። ይህ እንደ በጎ ሥራ የተደበቀ፣ ነገር ግን ከፍ ያለ እምነት ማጉደል ነው። እኛም ቤተክርስቲያንን ያለማቋረጥ ከራስዋ እንድትወጣ፣ ተልእኮዋን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንድትመሠርትና፣ ድሆችን ለመርዳት ዝግጁ እንድትሆን በማድረግ ይህን ብልሹነት ማስወገድ ይኖርብናል። እግዚአብሔር በጥራዝ ነጠቅ መንፈሳዊነትዋ ሐዋርያዊ ወጥመድ ውስጥ ከወደቀች ዓለማዊት ቤተክርስቲያን ያድነን። ይህ አፋኝ ዓለማዊነት ሊፈወስ የሚችለው እግዚአብሔር የሌለበትን የታይታ መንፈሳዊነት ካባ ከለበሰ ራስ ወዳድነት ነጻ የሚያወጣንን የመንፈስ ቅዱስ ንጹህ አየር በመተንፈስ ነው። ወንጌልን እንዳንነጠቅ እንጠንቀቅ።

ምንጭ፡ “የወንጌል ደስታ”  በተሰኘ አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ካስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 93-97 ላይ የተወሰደ።

 

 

07 March 2024, 15:33