እህት ፊሎሜና በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሥነ-ልቦና እና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሴቶች ጋር  እህት ፊሎሜና በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሥነ-ልቦና እና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሴቶች ጋር  

በደቡብ ሱዳን ሴቶች በወንጌል ላይ ተመሥርተው ሰላምን ደረጃ በደረጃ እየገነቡ እንደሆነ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአንድ ዓመት በፊት በእርስ በርስ ጦርነት ወደምትሰቃይ ደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚያች አገር ለዓመታት ከደረሰው የሰው ሕየት መጥፋት እና የንብረት ውድመት በኋላ የፈውስ እና የእርቅ ሂደት እየተካሄደ ሲሆን፥ በዚህ ጥረት ውስጥ ገዳማውያት እህቶች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ደቡብ ሱዳን ከአሥርት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 9/2011 ዓ. ም. ሉዓላዊ አገር እንደሆነች ይታወቃል። በደቡብ ሱዳን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር ወር 2005 ዓ. ም. የሰላም ስምምነት በሚፈረምበት ወቅት ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከቀያቸው ተፈናቅለው ይገኙ እንደ ነበር እና 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል። ይህም በተቀናቃኞቹ ጎሳዎች መካከል ሥር የሰደደ አለመተማመንን ጥሎ አልፏል።

በደቡባዊው ሱዳን ፈተናዎች እየጨመሩ ቢመጡም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 2011 ዓ. ም. ወደ ነፃነት የሚመራ ታሪካዊ ሕዝበ ውሳኔ መካሄዱ ይታወሳል። ነገር ግን ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 9/2011 ዓ. ም.  በደስታ ስትመሠረት ያለመተማመን እና የፍርሃት ቁስሎች ሙሉ በሙሉ አልተፈወሱም ነበር። አዲስ በተመሠረተች ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚያገለግሉ ገዳውያት እህቶች ይህን መሰናክል ተገንዝበው የሰላም ውጥኖችን በማስፋፋት ረገድ አስተዋፅዖ አድርገዋል።

የተስፋ ብርሃኖች

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በዋው ግዛት ውስጥ የሚገኝ የካቶሊክ ጤና ማሰልጠኛ ተቋም (CHTI) ባሕላዊ ውይይቶችን በማዘጋጀት ወንድ እና ሴት ተማሪዎች ሥር የሰደደውን ጭፍን ጥላቻን እንዲያሸንፉ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በኅብረት ለመሥራት የተቋቋመው የገዳማውያን እና ገዳማዊያት አንድነት ማኅበር ለመምህራን እና ነርሶች የቤት ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ለምግብ ዋስትና፣ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ምሥረታ እና በጦርነቱ ምክንያት የሥነ-ልቦና እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበርሰብ ክፍልን ለማከም ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። የተቋሙ የመጀመሪያ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2013 ዓ. ም. ሲሆን ማዕከሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. 181 ነርሶችን እና 87 አዋላጆችን አሰልጥኖ አስመርቋል።

ከፖላንድ የመጡት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍራንችስካዊ ሚስዮናዊያት ማኅበር አባል የሆኑት እህት ብሪጂዳ ማኒዩርካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት 2022 ዓ. ም. ጀምሮ በማዕከሉ ውስጥ የሠሩ ሲሆን፥ ማዕከሉም ሁሉንም ባሕሎች በማክበር እና በመቻቻል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸው፥ በሚያከናውኑት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እና ልምምዶች ወዳጅነትን በማጎልበት ሰላምን እና አንድነትን እንደሚያበረታቱ አስረድተዋል። እህት ብሪጂዳ በማከልም ማዕከላቸው ከሚሰጠው የነርስ እና የአዋላጅነት ስልጠናዎች በተጨማሪ ተማሪዎቻቸው በመካከላቸው ሰላማዊ ግንኙነቶችን መገንባት እና አብሮ የመሥራት ጥበብን እንደሚማሩ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹን በዕድገት ጉዟቸው ማገዝ በርካታ የውይይት ጊዜን እንደሚጠይቅ የተናገሩት እኅት ብሪጂዳ፥ ሆኖም ግን ከሦስት ዓመታት በኋላ ለውጦችን መመልከት እንደሚያስደስት፣ ከማኅበረሰባቸው እና ከሚሠሩበት ተቋም ምስጋናን ሲቀበሉ ደስታቸው የበለጠ እንደሚሆን አክለው ተናግረዋል።

ሕመም በራሱ እንክብካቤ የሚሆንበት ጊዜ

ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያምቢዮ ግዛት በጦርነቱ ምክንያት የሥነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ታውቋል። በአካባቢው ማኅበረሰብ እህት ባኪታ በመባል የሚታወቁት እህት ፊሎሜና ፍራንሲስ፥ በምዕራብ ደቡብ ሱዳን ትንሿ ከተማ ንዛራ የመጡ ሲሆን፥ የንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍራንችስካዊ ሚሲዮናዊያን እህቶች ማኅበርን ከመቀላቀላቸው በፊት ወደ ግብፅ የሚሰደዱ አምስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ደቡብ ሱዳናውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ካርቱም ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

እህት ፊሎሜና ፍራንሲስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1995 ዓ. ም. ለአገልግሎት ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከመሄዳቸው በፊት ዛሬ ደቡብ ሱዳን ተብላ በምትጠራው አገር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰባቸውን መጎብኝት  ችለው እንደነበር ታውቋል። በዚያን ጊዜ አካባቢው በሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ጦር “SPLA” ቁጥጥር ሥር በነበረበት ወቅት ቤተሰቦቻቸው እና እህቶቻቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ቢገኙም ነገር ግን በወታደሮች የሚደርስባቸው ጾታዊ ጥቃት እና በደል ሕይወታቸውን አሳዛኝ አድርጎ እንደ ነበር ይታወሳል።

እህት ፊሎሜና በቤተሰባቸው ላይ ይደርስ የነበረው ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳት፥ ለሴት ተጎጂዎች የምክር እና የማገገም አገልግሎትን እንዲጀምሩ ያነሳሳቸው ሲሆን፥ ለሴት ተጎጂዎች የሚሰጥ ይህ አገልግሎት በድጋፍ ሰጭ ድርጅት በመታገዝ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2006 ዓ. ም. በእህት ፊሎሜና እና በሌሎች ሁለት ሴቶች መጀመሩ ይታወሳል።

የንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍራንችስካዊ ሚሲዮናዊያን እህቶች ማኅበር በታምቡራ ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. የተከፈተ ሲሆን፥ እህት ፊሎሜና የአካባቢው ሴቶች እና ወንዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን ታሪክ ተመስጥዖ እንዳላቸው የሚናገሩት እህት ፊሎሜና፥ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ1964 ዓ. ም. የካርቱም መንግሥት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ላደረሰው ጥቃት የዓይን ምስክሮች ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት በቀጭን ትዕዛዝ ሁሉም ሚስዮናውያን ከሥፍራው መባረራቸውን አስታውሰዋል።

ያም ሆኖ ለሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ጥቂት የቁምስና ካኅናት እና በርካታ ምዕመናን ምስጋና ይድረሳቸው እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በአካባቢው ጸንቶ እንደሚገኝ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. በያምቢዮ እና አካባቢው አዲስ ብጥብጥ በመከሰቱ በአካባቢው ነዋሪዎች እና በእህት ፊሎሜና ቤተሰብ ላይ የበለጠ ስቃይ ደርሶበት እንደነበር ይታወሳል።

በልጅነታቸው በእርሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ይደርስ የነበረው ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት የዛሬን አገልግሎት ለመጀመር እንዳነሳሳቸው የሚገልጹት እህት ፊሎሜና፥ ሁለገብ አገልግሎት በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን አሰቃቂ ሁኔታ ለማስቆም፣ የጎሳ ቡድኖችን ለመቅጣት ተብሎ በብዙ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የተፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት በማከም ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ እንደሚችል እህት ፊሎሜና ገልጸዋል።

 

18 March 2024, 16:38