ፈልግ

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤ አረጋውያንን መንከባከብ

“በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ” (መዝ. 71፡9)። ይህ የመረሳትና የመጠላት ፍርሃት ያደረበት አረጋዊ ልመና ነው። እግዚአብሔር የድሆች ጩኸት መስሚያ መሣሪያ እንድንሆን እንደሚጠይቀን ሁሉ፥ የአረጋውያንንም ጩኸት እንድንሰማ ይፈልጋል። ይህም ለቤተሰቦችና ለማኅበረሰቦች ተግዳሮት ነው። ምክንያቱም “ቤተክርስቲያን በአረጋውያን ላይ የሚደርሰውን ትዕግሥት የማጣት፣ የቸልተኝነትና የንቀት አስተሳሰብ አትቀበልም፤ ልትቀበለውም አትችልም። አረጋውያን የማኅበረሰቡ ሕያው አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው እነርሱን የማመስገን፣ የማድነቅና የማስተናገድ የጋራ ስሜትን ማነቃቃት ይኖርብናል። የእኛ አረጋውያን ከእኛ በፊት እኛ በመጣንበት መንገድ፣ በራሳችን ቤት፣ ዋጋ ያለው ሕይወት ለመኖር በምናደርገው ዕለታዊ ትግላችን ውስጥ አልፈው የመጡ ወንዶችና ሴቶች፣ አባቶችና እናቶች ናቸው”።  በእርግጥ “በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል በሚፈጠር አዲስ መተቃቀፍ እጅግ የምትደሰትና ተጠቅሞ የመጣልን ባህል የምታወግዝ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት በወደድሁ!”

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቤተሰቦቻችን ውስጥ ለአረጋውያን ሚና ትኩረት እንድንሰጥ ይጠይቁናል። ምክንያቱም “በተለይ ቅጥ ባጣ የኢንዱስትሪና የከተማ ዕድገት መባቻ ትናንትም ሆነ ዛሬ አረጋውያንን ያለ አግባብ ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርጉ” ባህሎች አሉ። አረጋውያን “ክፍተትን በመሙላት ረገድ ያላቸው ግርማ ሞገስ የትውልዶችን ቀጣይነት” እንድናደንቅ ይረዳናል። አብዛኛውን ጊዜ ዋና ዋና እሴቶች ለልጅ ልጆች መተላለፋቸውን የሚያረጋግጡት አያቶች ናቸው። “ብዙ ሰዎችም የክርስትና ሕይወት ጅማሮአቸው በአያቶቻቸው እንደተመቻቸ ይመሰክራሉ”። ንግግራቸው፣ ፍቅራቸውና በአካል መገኘታቸው ብቻ ታሪክ በእነርሱ እንዳልተጀመረ፣ እነርሱ ደግሞ አሁን የእርጅና ጉዞ አካል እንደ ሆኑና ከእነርሱ አስቀድሞ የመጣውን ሁሉ ማክበር እንደሚገባቸው ልጆች እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።  ካለፈው ጊዜ ጋር ያላቸውን ትስስር ሁሉ የሚያቋርጡ፣ የተረጋጉ ግንኙነቶችን መፍጠርና እውነታ ከእነርሱ እንደሚበልጥ መረዳት ይከብዳቸዋል። ስለዚህ “ለአረጋውያን ትኩረት መስጠት በኅብረተሰብ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ኅብረተሰብ በእርግጥ ለአረጋውያን ያስባል? ለአረጋውያንስ ቦታ ይሰጣል? ይህን የመሰለ ኅብረተሰብ የአረጋውያንን ጥበብ ካከበረ ወደ ፊት ይጓዛል”።

የታሪክ መታሰቢያ አለመኖር በኅብረተሰባችን ውስጥ አሳሳቢ ጉድለት ነው። “ያ ያኔ አለፈ፤ አሁን አሁን ነው” የሚል አመላከከት ብስለት የለውም። ያለፉ ሁነቶችን ማወቅና መገምገም ትርጉም ያለው መጪ ጊዜ ለመገንባት ብቸኛ መንገድ ነው። ትውስታ ለዕድገት አስፈላጊ ነው፤ “የቀድሞውን ዘመን አስቡ” (ዕብ. 10፡32)። አረጋውያን ታሪካቸውን ሲናገሩ መስማት ለልጆችና ለወጣቶች ጥሩ ነው። ምክንያቱም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከአካባቢያቸውና ከአገራቸው ታሪክ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ሕያው ትውስታ የሆኑ አያቶቹን የማያከብርና የማይንከባከብ ቤተሰብ ከወዲሁ በውድቀት ላይ ነው። የሚያስታውስ ቤተሰብ ግን ተስፋ አለው። “ችግር ይፈጥራሉ በሚል ሰበብ ለአረጋውያን ቦታ የሌለው ወይም እነርሱን ገለል የሚያደርግ ኅብረተሰብ ‘በገዳይ ቫይረስ’ የተጠቃ ነው”። “ሥሩ የተነቀለ ነው”።  

በባህላዊ መምረጥ፣ በሥረ መሠረት መነቀልና ሕይወታችንን በሚቀርጹ የእርግጠኝነት ስሜቶች መጥፋት ምክንያት በዘመናችን የሚታየው ወላጅ አልባነት ቤተሰቦቻችንን ልጆችን በጋራ ታሪክ የዳበረ አፈር ላይ ሥራቸውን የሚተክሉባቸው ሥፍራዎች እንዳናደርጋቸው ፈተና ሆኖብናል።

ወንድሞችና እህቶች ስለ መሆን

በወንድሞችና በእህቶች መካከል ያሉ ግንኙነቶች በጊዜ ሂደት ሥር እየሰደዱ ይሄዳሉ። “በቤተሰብ ውስጥ በልጆች መካከል የሚፈጠር የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ትስስር ለሌሎች ግልጽ በሆነ የመማር ማስተማር ከባቢ ጽኑ መሠረት ላይ የቆመ ከሆነ ትልቅ የነጻነትና የሰላም ትምህርት ቤት ይሆናል። በቤተሰብ ውስጥ በአንድነት እንዴት መኖር እንዳለብን እንማራለን። ምናልባት ሁልጊዜ ይህን አናስበው ይሆናል፤ ነገር ግን ቤተሰብ ራሱ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በዓለም ውስጥ እንዲሰርጽ ያደርጋል። በቤት ውስጥ በፍቅርና በትምህርት ከበለጸገ ከዚህ ቀዳሚ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ልምድ በመነሣት የወንድማማችነት ዘይቤ እንደ ተስፋ ቃል በመላው ኅብረተሰብ ላይ ይፈነጥቃል”።

ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ማደግ እርስ በርስ ለመተሳሰብና ለመረዳዳት የሚያስችል ግሩም የሆነ ልምድን ለማዳበር ይረዳል። ምክንያቱም “ወንድማማችነት በቤተሰብ ውስጥ በተለይ ሊደምቅ የሚችለው ለደካማ፣ ታማሚ ወይም ለአካል ጉዳተኛ ታናሽ ወንድም ወይም እህት ክብካቤ፣ ትዕግሥትና ፍቅርን ስናይ ነው”። “የሚወዳችሁን ወንድም ወይም የምትወዳችሁን እህት ማግኘት ጥልቅ፣ ክቡርና ዓይነተኛ ተሞክሮ” መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ልጆችን እንደ ወንድማማችና እህትማማች እንዲተያዩ በትዕግሥት ማስተማር ያስፈልጋል። ይህ ሥልጠና አንዳንድ ጊዜ ከባድ ቢሆንም፥ እውነተኛ የማኅበራዊ ኑሮ ትምህርት ቤት ነው። አንድ ልጅ ብቻ መውለድ ልማድ በሆነባቸው አንዳንድ አገሮች ወንድም ወይም እህት የመሆን ልምድ ይበልጥ አናሳና ያልተለመደ ነው። አንድ ልጅ ብቻ መውለድ በተቻለበት ሁኔታ፣ እርሱ ወይም እርስዋ በብቸኝነት ወይም በገለልተኝነት አለመኖራቸውን ማረጋገጫ መንገዶችን ማፈላለግ ያስፈልጋል።

ሰፊ ልብ መኖር

ከባል፣ ከሚስትና ከልጆቻቸው ንኡስ ክልል በተጨማሪ ችላ ሊባል የማይችል ሰፊ ቤተሰብ አለ። በእርግጥ “በባልና ሚስት መካከል ያለው ፍቅርና ከእርሱም የሚመነጨውና ሰፋ ያለው በተመሳሳይ ቤተሰብ አባላት፣ ማለትም በወላጆችና በልጆች፣ በወንድሞችና በእህቶች እንዲሁም በዘመዶችና የቤተሰብ አባላት መካከል ያለው ፍቅር፣ ሕይወትና ምግብ የሚያገኘው ቤተሰብን ወደ ጥልቅና ጠንካራ ኅብረት በሚመራው የማያቋርጥ ውስጣዊ ኃይል ነው። ይህም ለጋብቻ ኅብረት፣ ለቤተሰብ መሠረትና እስትንፋስ ነው”። ጓደኞችና ሌሎች ቤተሰቦች የዚህ ሰፊ ቤተሰብ እንዲሁም በችግራቸው፣ በማኅበራዊ ግዴታዎቻቸውና በእምነታቸው ጊዜ እርስ በርስ የሚደጋገፉ የቤተሰቦች ማኅበራት አባላት ናቸው።

ሰፊው ቤተሰብ በአሥራዎቹ ዕድሜ የወለዱ እናቶችን፣ ወላጅ አልባ ሕጻናትን፣ ልጆችን በብቸኝነት የሚያሳድጉ እናቶችን፣ ልዩ እንክብካቤና ቅርበት የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞችን፣ በሱስ የሚሠቃዩ ወጣቶችን፣ ላጤዎችን፣ ሥራ ፈቶችን ወይም ባል ወይም ሚስት የሞቱባቸውን ብቸኞች እንዲሁም የልጆቻቸው ድጋፍ የሌላቸው አረጋውያንንና አካል ጉዳተኞችን መወደድና መደገፍ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ “ሕይወታቸው የተበላሸባቸውን ጭምር መቀበል ይኖርባቸዋል”። ይህ ሰፊ ቤተሰብ የወላጆችን ጉድለት የሚሞላ፣ ሕጻናት የሚደርስባቸውን በደልና እንግልት ጭምር የሚጠቁምና የሚያሳውቅ እንዲሁም ወላጆች ይህን ማድረግ በማይችሉባቸው ሁኔታዎች ሙሉ ፍቅርና የቤተሰብ መረጋጋትን የሚለግስ ሊሆን ይችላል።

በመጨረሻም ይህ ሰፊ ቤተሰብ አማቾችን፣ አማቶችንና የባልና ሚስት ዘመዶችን ሁሉ እንደሚያካትት ልንዘነጋ አይገባም። የፍቅር አንዱ ልዩና ስስ ገጽታ እነዚህን ዘመዶች እንደ ባላንጣዎች፣ እንደ ሥጋት ምንጭ ወይም እንደ ሰርጎ ገቦች አድርጎ አለማየትን መማር ነው። የጋብቻ ኅብረት ወጎቻቸውንና ባህሎቻቸውን ማክበርን፣ ቋንቋቸውን ለማወቅ ጥረት ማድረግንና ከመተቸት መቆጠብን፣ እነርሱንም መንከባከብንና ለእነርሱ ዋጋ መስጠትን እንዲሁም የባልና ሚስትን ተገቢ የሆነ ብቸኝነትና የግል ነጻነት መጠበቅን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ዝግጁ መሆን ደግሞ ለትዳር አጋር የሚሰጥ የለጋስ ፍቅር ክቡር መገለጫ ነው።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 191-198 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ፥ ክቡር አባ ዳንኤል ኃይለ

 

13 April 2024, 17:31