ፈልግ

በአውስትራሊያ ስድኒ ውስጥ በጳጳስ እና ሌሎች ሦስት ምዕመናን ላይ የደረሰ ጥቃት በአውስትራሊያ ስድኒ ውስጥ በጳጳስ እና ሌሎች ሦስት ምዕመናን ላይ የደረሰ ጥቃት   (ANSA)

አውስትራሊያ ውስጥ በአንድ የቤተ ክርስቲያን አባት ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ተገለጸ

“ክርስቶስ መልካም እረኛ” በመባል የሚታወቅ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በሆኑት በአቡነ ማር ማሪ አማኑኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ተነገረ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አቡነ ማር ማሪ አማኑኤል በመንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት መካከል በስብከት አገልግሎት ላይ እያሉ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ በአውስትራሊያ የጸጥታ ኃይል በቁጥጥር መዋሉ ታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው በሲድኒ ከተማ ዳርቻ ሲሆን ከአንድ ቀን በፊት በአካባቢው በሚገኝ የገበያ ማዕከል ከተፈጸመው ጥቃት ጋር ተያያዥነት ያለው አይመስልም ተብሏል።

በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በሚገኝ “የክርስቶስ መልካም እረኛ” ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በነበሩት ጳጳስ እና በሌሎች ሦስት ምዕመናን ላይ ጥቃት ያደረሰውን ወጣት የአካባቢው ፖሊስ በቁጥጥር አውሎታል።

ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የሆነው እና “ክርስቶስ መልካም እረኛ” በመባል የሚታወቅ ቤተ ክርስቲያን መሪ በሆኑት አቡነ ማር ማሪ አማኑኤል እና ሌሎች ሦስት ምዕመናን ላይ ስለት ባለው መሣሪያ ጥቃት ቢደርስባቸውም ከባድ ጉዳት አለመድረሱን የአካባቢው የጸጥታ ኃይል ተናግሯል። ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር በሚገኝበት በዚህ ወቅት ፖሊስ የጥቃቱን መንስኤ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የተፈጸመው ጥቃቱ በሲድኒ ምሥራቃዊ ዳርቻ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ውስጥ ጥቃት ከተፈፀመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን፥ በጥቃቱ ስድስት ሰዎች ተገድለው ቢያንስ ስምንት ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል።በሲድኒ ከተማ በሚገኝ የክርስቶስ መልካም እረኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰነዘረው ጥቃት ከገበያ ማዕከሉ ጥቃት ጋር ተያያዥነት ያለው አይመስልም ተብሏል።

 

16 April 2024, 17:41