ፈልግ

በማዳጋስካር በማናንጃሪ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ የኤኮል ቨርቴ ልጆች በማዳጋስካር በማናንጃሪ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ የኤኮል ቨርቴ ልጆች 

በማዳጋስካር ውስጥ የሚገኙ ለልጆች የተቋቋሙ ‘አረንጓዴ ትምህርት ቤቶች’

በአፍሪካ ደቡብ ምስራቅ የባህር ዳርቻ የምትገኘው የማዳጋስካር ደሴት በአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች በእጅጉ ተጎድታለች። ለዚያም ነው በደቡብ ምስራቅ የሚገኘው የማናንጃሪ ሀገረ ስብከት በወጣት ማላጋሲዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለመስራት እና ለጋራ ምድራችን ጥበቃ ይረዳ ዘንድ በሃገሪቷ ከሚሰጡት የትምህርት ኮርሶችን በተጨማሪ “አረንጓዴ ትምህርት ቤቶች” የሚለውን ፕሮጄክት ለመጀመር የወሰነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አባ ላራይሰን ራሞስ አንዲሪያናሪቮ እና ሌሎች ሦስት የሀገረ ስብከቱ አባላት በጣም ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች በአቧራማው መንገድ ላይ በሚጓዙበት ወቅት እንኳን የመጡበትን ኪሎ ሜትሮች አይቆጥሩም፣ ትዝም አይላቸውም። እድሜያቸው ከ5 እስከ 14 ዓመት የሆናቸው 15,000 የመናንጃሪ ሀገረ ስብከት የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች “አረንጓዴ ትምህርት ቤት” በሚለው ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑት በእነሱ ያላሰለሰ ጥረት እና ጽናት ነው።

የአደጋ መከላከያ ኮፊያ ያደረጉት ቀናተኛው ካህን አባ ላራይሰን እንደገለጹት፥ ሃሳቡ አዲሱን ትውልድ ተፈጥሮን እንዲወድ እና እንዲጠብቅ ማስተማር ነው ብለዋል።

ጽንሰ-ሐሳቡ ቀላል ቢሆንም ለወጣት ማላጋሲዎች የህልውና ጥያቄ ነው። እንደ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ማዳጋስካር ለአየር ንብረት ለውጥ ከተጋለጡ ሀገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ፣ይህም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ስለሚኖር የሚያስከትለው መዘዝ የበለጠ አስደንጋጭ ነው።

አደገኛውን አዙሪት መስበር

በ2013 ዓ.ም. ዩኒሴፍ ባወጣው ሪፖርት “ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ግማሽ ሚሊዮን ህጻናት በምግብ እጦት ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል” ሲል የማስጠንቀቂያ ደወል አሰምቷል። በእርግጥም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ካለፉት 40 ዓመታት ከተከሰቱት የድርቅ አደጋዎች የከፋው የአሁኑ ድርቅ፥ በአገሪቱ በአንደኛ ደረጃ ለምግብነት የሚውሉትን 60 በመቶ የሩዝ እና የበቆሎ ምርት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።

ይህን ተከትሎ ከመጣው ከፍተኛ የኢኮኖሚ አደጋ ለማምለጥ አብዛኛው የሃገሪቱ ህብረተሰብ ፊቱን ወደ ከሰል ማምረት አዙሯል። እነዚህ የከሰል አምራቾች ደግሞ አነስተኛ ገቢ ለማግኘት ሲሉ ደኖችን ያቃጥላሉ፥ ነገር ግን ይህ ተግባር ለእነሱም ኪሳራ ነው።

የደን ቃጠሎ የደን ጭፍጨፋን ይፈጥራል፤ በጫካ እና በደን አካባቢዎች ለሚመነጨው ከባድ ዝናብ የመከላከል ሥራ እያነሰ በመምጣቱ የጎርፍ መጥለቅለቆች እና ከልክ በላይ የሚፈሱ ወንዞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ነው። ከዚህም በላይ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ሃይል ምንጭ የሚገኘው ከብሄራዊ የደን ሃብት እና ከቅሪተ አካል ቃጠሎ ነው።

ከዚህ አደገኛ አዙሪት ለመውጣት ትምህርት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አባ ላራይሰን ያምናሉ። “በእርግጥም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነውን ‘ላውዳቶ ሢ’ ን በተግባር ላይ በማዋል የተሻለ ምሁራዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ አካባቢን መፍጠር ነው” ሲሉም ያስረዳሉ። ወጣቱ ማላጋሲያዊው ካህን በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የበለጠ የተማሩ እና የተዘጋጁ ልጆች የተሻሉ አዋቂዎች እንደሚሆኑ በጽኑ ያምናሉ።

ተግሣጽ እና አክብሮትን ማስተማር

በአረንጓዴ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስልጠና በመሠረቱ በጽሁፍ እና በተግባራዊ ኮርሶች ይሰጣሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ልጆች ስለ ተፈጥሮ፣ ሰብሎች፣ የአየር ንብረት መዛባት መንስኤዎች እና ውጤቶች እንዲገነዘቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይሄንንም አስመልክተው አባ ላራይሰን “ልጆች ለአካባቢያቸው ፍቅር እንዲኖራቸው እንፈልጋለን፣ በእግዚአብሔር የተፈጠረውን ተፈጥሮ ስለ መጠበቅ እና ማክበር እንዲያውቁ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ከዚያ በኋላ ለችግሮቹ መፍትሄ የምናገኝበት ጊዜ ነው። ተማሪዎች አበባን መትከል እና ማልማት፣ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባትን፣ የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎችን፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀናባበሪያ ሥፍራዎችን ስለመገንባት ይማራሉ፥ በደን መልሶ የማልማት ልምድ ይቀስማሉ። በተጨማሪም የአትክልት እና ፍራፍሬ ማሳዎችን ያዘጋጃሉ ብሎም ይዘራሉ፣ ያመርታሉ። ይህን በማድረጋቸው በትምህርት ቤት የምግብ ፍጆታቸውን ከመቻላቸው አልፎ ተርፎም ለሽያጭ ይቀርባሉ።

የሙከራ ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ የተካሄደው በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በሚገኝ የድሃ ድሃ የሆኑ ልጆች የሚማሩበት አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን፥ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለተዘሩት ተክሎች እና ዘሮች በተማሪዎቹ ላይ የታየው ቸልተኝነት እና ትኩረት ማጣት፥ ስለ ክብር እና ራስን ስለመግዛትን እንዲማሩ መንገድ ከፍቷል። በአሁኑ ወቅት በልጆቹ ላይ የታየውን ተጨባጭ ለውጥ እንዲሁም ጎልማሶች፣ ወላጆች እና አስተማሪዎችም ላይ ጭምር ያሳደረውን ተፅዕኖ በማየታቸው ተደስተው “እኔ አብሬያቸው በሌለሁበት ጊዜ እንኳን አበባዎችን እና ተክሎችን ያጠጣሉ” ብለዋል አባ ላራይሰን።

የማዳጋስካር ልዩ የብዝሃ ሕይወት

ታላቋ አፍሪካ ደሴት የሆነችው ማዳጋስካር ልዩ የሆነ የብዝሃ ህይወት ባለቤት ስትሆን፥ አባ ላራይሰን ሳይታክቱ ጥረታቸውን በታላቅ ቁርጠኝነት ሲያከናዉኑ የነበረው ይህንን የፍጥረት ስጦታ ለማዳን እንደሆነ ሲገልፁ፣ “እኛ የምንኖረው የጋራ በሆነችው ምድራችን ውስጥ ነው፥ ምድራችን ላይ አደጋ የሚያደርሱ እና በጥፋቱም ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ። አዎ፣ የዚህ ስልታዊ የተፈጥሮ ውድመት የመጀመሪያ ተጠቂዎች የሆንነው እኔ እና ህዝቤ ተናድደናል፣ ነገር ግን መላመድ አለብን እናም አዲስ የሆነ የኢኮኖሚ አይነት ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ሰጪዎችን ለማበረታታት መታገል አለብን” ብለዋል።

የማዳጋስካር ጉዳይ በእውነቱ አስፈሪ ምሳሌ ነው፤ የአየር ንብረት ኢፍትሃዊነት ተምሳሌት ናት፣ ነዋሪዎቿ በግሪንሀውስ ጋዝ ልቀቶች እና በደን መጨፍጨፍ ምክንያት በሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታ ይሠቃያሉ።

በ2012 ዓ.ም. ብቻ የቡድን 20 ሀገራት 75 በመቶውን የዓለም በካይ ልቀትን ለቀዋል፥ በአጭሩ፣ ዓለም የምትጠፋ ከሆነ የማዳጋስካር “ጥፋት” አይደለም፣ ነገር ግን ይህች አስደናቂ ምድር በዓለም እጅግ የተበከሉ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች።

‘ሌሙር’ ተብለው የሚጠሩት ልዩ የማዳጋስካር ዝንጀሮዎችን፣ እንቁራሪቶችን፣ ወፎችን እና እስስቶችን ጨምሮ በርካታ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በማዳጋስካር ውስጥ ይኖራሉ፥ ይህም በዓለም ላይ ሦስተኛው ትልቁ የዛጎል እንዲሁም ‘ማንግሩች’ ተብለው የሚጠሩ እና ለሥርዓተ-ምህዳሩ ጠቃሚ እና ውድ የሆኑ በውሃ አከባቢ የሚበቅሉ እፅዋቶች የሚገኙበትም ጭምር ነው።

ይህንን በመጥፋት ላይ ያለውን ፍጥረት ለማዳን ሲሉ አባ ላራይሰን ጥልቅ በሆነ አርቆ አሳቢነታቸው አጥብቀው የያዙት ይህንን የትግል መንፈስ ለህፃናት እያስተላለፉ ይገኛሉ።
 

17 April 2024, 16:54