ፈልግ

በጋዛ ውስጥ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሆሳዕና ዕለት የተነሳ በጋዛ ውስጥ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሆሳዕና ዕለት የተነሳ  (AFP or licensors)

በጋዛ ትንሳኤ ዳግመኛ ይጀምራል

በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደብር ካህን የሆኑት አባ ገብርኤል ሮማኔሊ በቅድስት ሀገር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት የትንሳኤ በዓል በሚከበርበት ወቅት በጋዛ ቀራንዮ ውስጥ የተደበቀውን የሰላም ተስፋ አስመልክተው አስተንትኖ አድርገዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ 

በእየሩሳሌም የሞት ፍርዱ ከተፈጸመ ከሶስት ቀናት በኋላ፥ ቀራንዮ መስቀሎች፣ መዶሻዎች፣ ሚስማሮች እና ገመዶች ብቻ የሚታዩበት የጥፋት ቦታ ሆኖ ነበር የቀረው ፤ የጠዋት ጤዛ በድንጋይ መካከል የሚበቅሉትን የዱር አበቦች ሸፍነዋል።

ጥልቅ ጸጥታ፥ የተሰባበሩ ድንጋዮች፥ ማለቂያ የሌለው ብቸኝነት፥ ከዚያ እግዚአብሔር ከምድር “የተለየበት” ከሚመስለው ሥፍራ፣ ምንም እንኳን እስከ መጨረሻ ባይለየንም፥ ሁሉም ነገር ያበቃለት ይመስላል። የዓለም ቤዛ የሆነው የቅዱሳነ - ቅዱሱ ነፍስ ከሥጋው የተለየው በዚያ በቀራንዮ፣ በዚያ ከሰዓት በኋላ፣ በዘጠኝ ሰዓት ቀኑ የጨለመብት፣ በዚያ ሥፍራ ነው። ያ ጥፋት ከተፈጸመ ሶስት ቀናት አልፈዋል... ።

ከዚያ ሥፍራ በጣም በቅርብ ርቀት የሰው ልጅ እውነተኛው አዲስ ህይወት ጅማሮ የሚያገኝበት ቦታ አለ፥ የክርስቶስ የመቃብር ቦታ።

አዎ ፣ ሆኖም ግን መቃብሩ ባዶ ነበር! ሕያው ሆኖ ወጥቷል፣ ተነስቷል፣ ወደዚያም አይመለስም።

የጋዛ ቀራንዮ ግን ዛሬም ጥፋት አለ፥ ብዙዎች ሞተዋል! እየሞቱም ነው። የቆሰሉ፣ የታመሙ፣ የተራቡ፣ ወደ እጣ ፈንታቸው የሚሄዱ ሰዎች፣ ታጋቾች እና እስረኞች የሚገኙበት፥ ብቸኝነት እና ድብርት የተንሰራፋበት አከባቢ ሆኗል። በተወሰኑ ሣሮች ላይ ያለው የጠዋት ጤዛ እና ጥቂት ተክሎች ላይ ብቻ የሚታዩ አበቦች ጸደይ መድረሱን ያመለክታሉ።

ፀደይ እዚህም አለ፥ እንደዛም ሆኖ ፀሀይን በእጃችን መሸፈን ወይም በጋዛ ያለው እውነታ ጥሩ ነው ብለን ማስመሰል አንችልም። እየተፈጸሙ ያሉ ነገሮች ጥሩ አይደሉም፥ እጅግ በጣም መጥፎ ድርጊቶች ናቸው እየተደረጉ ያሉት! ነገር ግን እኛ፣ በትንሳኤው ጌታ የምናምን አማኞች፣ ያንን ሌላኛውን፣ ከሙታን ተለይቶ የተነሳውን ፀሐይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መደበቅ ወይም መሸፈን አንችልም።

ለትንሳኤ በዓል አከባበር ምስጋና ይግባውና፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያ ሥፍራ፣ ከጋዛ ተመልሶ እንደተነሳ እናውቃለን። ዛሬ ደግሞ በእምነት ወንድሞቻችን የሆኑ በርካታ ሰዎች በቅዱስ ቁርባን በኩል ኢየሱስን ይቀበላሉ። ነገር ግን ተመልሶ በክብር በመምጣቱ ጻድቅ ነፍሳትን ሁሉ በጸጋ እንደሚሞላ እና እንደሚያበራም እናምናለን።

ምናልባት ብዙዎች በአማኑኤል፣ የእግዚአብሔር ልጅ እና የዳዊት ልጅ በሆነው፣ ከድንግል በተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ገና አላወቁም ይሆናል፥ ይህ ማለት ግን በምስጢር ከትንሳኤው ጸጋ መካፈል አይችሉም ማለት አይደለም። ያለ ሕግ የተወለደ ሁሉ ያለ ሕግ እንደሚፈረድበት ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል። ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ፥ እያንዳንዳችንን ጨምሮ እያንዳንዱን የሰው ልጅ መፍረድ እና ማየት የሱ ፋንታ ነው።

እርሱን በቅን ልቦና የሚሹትን እንደሚወዳቸው እናውቃለን፣ እናም በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ የተባረኩ ሰዎች በመንፈሳቸው ይህንን ጦርነት እንደማይፈልጉ እርግጠኛ ነኝ። በፍፁም አይፈልጉትም፥ እንደውም ይጠሉታል።

ከጋዛ፣ ከነዚያ የመቃብር ስፍራዎች፣ ብዙዎች፣ በእርግጥ እጅግ በጣም ብዙ፣ የመጨረሻውን የትንሣኤ ቀን ይጠባበቃሉ። ነገር ግን እኛ ብዙ ጊዜ በርካታ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከአመድ ዳግመኛ ሲወለዱ ያየነው፥ ከዚያ ሥፍራ ትንሳኤ እንደገና ይጀምራል ብለን ልናስብ እንችላለን።

ምናልባት በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ይሆን ዘንድ አሁንም የተወሰነ ጊዜ ሊኖር ይችላል፥ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ እነዚያን ድሆች በቀራንዮ አይተዋቸውም።

ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ፥ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ፥ የተወሰነም ቢሆን የሰው ልጅ አዲስ የተስፋ ብርሃን ሁሉም በእርሱ ለማመን፣ እርሱን ለመጠበቅ እና እርሱን ለመውደድ ይቻል ዘንድ ምልክት እና እድል ይሆናል።

በመከራ ውስጥም ቢሆን በትንሳኤው ደስታ በተሞሉ ልቦች፣ በጋዛ የሚገኘው የካቶሊክ ማህበረሰባችን መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆንላችሁ ይመኛል፣ እንዲሁም ለተደረጉልን በርካታ ጸሎቶች እና ድጋፍ እናመሰግናለን።

*የጋዛ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካህን
 

03 April 2024, 15:25