ፈልግ

አንደኛ የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ አንደኛ የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ 

አንደኛ የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ

ጌተችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እንደተፈረደበት

አይሁዳውያን ጌታችንን ከያዙ በኋላ እንደ በደለኛና ወንጀለኛ አስረው ሞት እንዲፈረድበት በሊቅ ካህናት ቀያፊ ፊት አቆሙት፡፡ እርሱም ይሙት ብሎ ከፈረደበት በኋላ ወደ አገረ ገዥው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት፡፡ ጲላጦስም ኢየሱስን ካየው በኋላ «በዚህ ሰው ላይ ያቀረባችሁት ክስ ምንድነው?» (ዮሐ. 18፣29) ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነሱም «ይህ ሰው ክፋ አድራጊ ባይሆን ኖሮ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር» (ዮሐ. 18፣30) ሲሉ መለሱለት፣ ቀጥሎም «ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም፣ ለቄሳርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል፣ ደግሞም እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሰው» (ሉቃ.  23፣2) ብለው ይከሱት ጀመር፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ጲላጦስም «አንተ የአይሁድ ንጉስ ነህን?» ብሎ ጠየቀው (ሉቃ  .23፣3) ኢየሱስም «አንተ ይህንን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ሰለ እኔ ነግረውሃል» (ዮሐ. 18፣34) አለው፡፡ ጲላጦስ አይሁዳውያን ደጋግመው ኢየሱስን አጥብቀው ሲከሱት አይቶ «ስንት ነገር አቅርበው እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?» (ማቴ. 27፣ 13) አለው፣ ጌታችን ግን ሳይመልስ ዝም አለ፡፡

ጲላጦስ የአይሁዳውያን ክስ ከሰማ በኋላ ኢየሱስን ደህና አድርጐ መርምሮና አጣርቶ በደል እንደሌለበት ስላረጋገጠ የአይሁዳውያን ክስ የጥላቻና የቅናት ፍሬ ብቻ መሆኑን ተረዳ፡፡ ሰለዚህ እንደምንም ብሎ ኢየሱስን ከሞት ሊያድነው ፈልጐ «እነሆም ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፣ እንግዲያውስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ» (ሉቃ. 23፣16) አላቸው፡፡ እነርሱም ሁሉም «ይሰቀል!» በማለት በጩኸት መለሱለት፡፡

ሌላ በርባን የሚባል ከፍተኛ ወንጀል የሰራ፣ ነፍስ ገዳይ አብሮ ተከሶ ነበርና ጲላጦስ ኢየሱስን ከሞት አድኖ በርሱ ፈንታ በርባንን ይጠሉ እንደሆነ ብሎ በርባንና ኢየሱስን አቅርቦ «በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማናቸውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?» አላቸው፡፡ …የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ግን በርባርንን እንዲፈታ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፋ ሕዝቡን አስተባበሩ፣… እነርሱም በርባንን አሉ (ማቴ. 27፣17-23)

ጲላጢስ ኢየሱስን ካስገረፈው በኋላ “አነሆ! ሰውየው እነሆ! ንጉሣቸሁ በደል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ» አላቸው፡፡ እነርሱም እንደገና ስቀለው! ስቀለው!» ብለው በመጮህ ግርግር ፈጠሩበት፡፡ ጲላጦስም ምን አደረገ?» ቢላቸው «ይህን ሰው ከፈታኸው የሮም ንጉሠ ነገሥት የቄሳር ወዳጅ አይደለህም» (.ዮሐ. 19፣12) እያሉ አስፈራሩት፡፡ ጲላጦስ የሚቻለውን ሁሉ ካደረገ በኋላ ኢየሱስ ለማዳን ሲል ራሱን እንዳይጐዳ ፈርቶ በደል የሌለውን ኢየሱስን የሰውን ዓይን በመፍራት ሞት ፈረደበት፡፡ ወዲውም በአይሁዳውያን እጅ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ኢየሱስ በቀያፋና በጲላጦስ ፊት ጠላቶቹ አይሁዳውያን በሐሰት ሲከሱት አልተከላከለም፡፡ አፉን ዘግቶ ዝም አለ፤ በዚህም ጲላጦስ ሳይቀር ስለገረመው «አትመልስምን?» አለው፡፡ ኢየሱስ ዝም ማለቱ በደል ኖሮት ወይም ደግሞ መከላከል አቅቶት አልነበረም ስላልፈለገ ብቻ ነው፡፡

አይሁዳውያን ደጋግመው በሐሰት ይከሱት ነበር፡፡ እርሱ ግን ሐሰተኛ ክሳቸውንና ስድባቸውን ዝም ብሎ ተቀብለው፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ሳንበድል በድለንም ቢሆን ሰው ሲከሰን በጣም እናዝናለን፤ ከክሱ ነጻ ለመውጣትና በጥፋተኛነት ላለመጠየቅ አቅማችን በፈቀደል መጠን ራሳችንን እንከላከላለን፤ የሚከሰንንም ሰው እንጠላዋለን፡፡ የክርስቶስ መንፈስ ይህ ነው ወይ? የኛ አስተሳሰብና መንፈስ ጌታ ከተወልን የሚያስደንቅና የሚገርመን መልካም አብነት፣ትዕግስት፣ ዝምታ፣ ትሕትና እንዴት ይስማማል? የእርሱን አብነት ተከትለን መንፈሳችንን እንቀይር፣ ክርስቶስን እንምሰል፣ የሰላም ወዳጆች በመሆን ፍቅርን እንጠብቅ፡፡

አይሁዳውያን ኢየሱስን ከያዙት በኋላ እንደ ትልቅ በደለኛ አስረው እያዋረዱና እየሰደቡ ወሰዱት፡፡ እርሱ ግን እንደ በግ አንድም ቃል ሳይናገር ተከተላቸው፡፡ አምላክ ሳለ ፍጥረቶቹ ሲቀልዱበትና ሲዘባበቱበት ዝም ብሎ ተመለከታቸው፣ ንጹሕ ሳለ እንደ በደለኛ ተቆጠረ፡፡ እንዴት ያለ ትህትና ነው «ኦ! ትህትና ዘመጠነዝ ትሕትና፣ ኦ! ትዕግሥት ዘመጠነዝ ትዕግሥት፣ ኦ! አርምሞት ዘመጠነዝ አርምሞት፡- እንዴት ያለ ትሕትና; ይህን ያህል ትሕትና ይህን ያህል ትዕግሥት; ይህን ያህል ዝምታ እያለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይደነቃል፣ ይገረማል (መጽሐፈ ቅዳሴ ተመልከት)፡፡ እኛን ሰው ሲበድለን በፍጥነት እንቆጣለን፣ እንነቅፋለን፣ ብርቱ ውርደት ሆኖ ይሰማናል፣ በልባችን ቂም እናሳድራለን፡፡

ጲላጦስ አይሁዳውያንን ፈርቶ ኢየሱስን በደል ሳይኖረው ሞት ፈረደበት፣ ኰነነው፡፡ እኛም ብዙ ጊዜ እንደዚህ እናደርጋለን፣ ከኢየሱስ ይልቅ ሰዎችን ፈርተን ኢየሱስን እንክዳለን፤ ሰዎችን ለማስደሰት ብለን ኢየሱስን እናሳዝናለን፡፡ በኃጢአታችን ብዛት እንደገና በኢየሱስ ሞት እንፈርድበታለን፡፡ ኢየሱስ ስለእኛ ይህን ሁሉ ውርደትና መከራ ተቀብሎአል፡፡ ለደኀንነታችን ብሎ ሲፈርዱበትና ሲያዋርዱት ዝም ብሎ ተመለከታቸው፡፡ ፍቅሩንና ስቃዩን በልባችን ውስጥ እናትመው፡፡ ሁለቱንም ዘወትር እያሰብን ከሁሉ አስቀድመን ወደ ኃጢያት እየተመላለስን አናሳዝነው፣ ቀጥለን ደግሞ እርሱ እንደ ወደደን እንድንወደው ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፡፡

12 April 2024, 16:25