ፈልግ

አራተኛው የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ ኢየሱስ ወደ ቀራኒዮ ሲሄድ ሳለ ከእናቱ ጋር ተገናኘ አራተኛው የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ ኢየሱስ ወደ ቀራኒዮ ሲሄድ ሳለ ከእናቱ ጋር ተገናኘ 

አራተኛ የፍኖተ መስቀል ምዕራፍ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሽክሞ ወደ ቀራኒዮ ሲሄድ ሳለ ከእናቱ ጋር ተገናኘ

አይሁዳውያን ኢየሱስን እያዋረዱና እየመቱ እየገረፉ ይወስዱት ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በትሕትና ይታዘዝላቸው ነበር፡፡ “ተጨነቀ፣ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾችም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” (ኢሳ. 53፣ 1-6) ይላል ኢሳይያስ፡፡ እየሱስ ውርደትን ታግሶ ተቀበለ ከባድ መስቀልን በትከሻው ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ሄደ፡፡ በመንገድ ያች የተወደደች ርኀርኀት እናት (ወላዲቱ) ቆየችው፤ ስቃዩን አውቃ በወላጅ እናት ፍቅር ተስባ ልታየው መጥታ ነበር ዓይን ለዓይን የተገናኙት፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

ኢየሱስ እመቤታችን ማርያምን በማየቱ ብርቱ ሐዘን ተሰማው፤ እርስዋ ደግሞ ኢየሱስን ልጅዋን በማየትዋ ትልቅ ሐዘን ተሰማት፡፡ ኢየሱስ በድካም ተሸንፎ የመስቀሉም ሸክም ከብዶት እየተደነቃቀፈ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ፊቱ በእድፍ፣ በቆሻሻ፣ በአክታ፣ በምራቅና በደም ተበላሽቶ ነበረ፡፡ ሰውነቱ በሙሉ ቆስሎ አለመጠን ተለውጦ ተጐሳቁሎና ዝሎ ነበር “መልክና ግርማ አልነበረው ከሁሉ የተዋረደና ዝቅ ያለ፣ መከራና ስቅይን የተሞላ ነው” ይላል ኢሳይያስ፡፡ ይህንን አይታ እመቤታችን ማርያም በፍጹም ደነገጠች፡፡ የእርሱ ስቃይ እንደ ሹል ጦር ልብዋን ወጋት፡፡ ያ የተወደደው ልጅዋ እንዲህ ተዋርዶና ተንገላቶ የእነዚያ ክፉ አይሁዳውያን መዘባበቻ ሆኖ በማየትዋ መራራ ሐዘን ተሰማት፣ ፊትዋ ጠቆረ፣ ከሰል ጠላሸት መሰለ፣ ከዓይኖችዋ እንባዋ እንደጐርፍ ፈሰሰ፡፡

ታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በበኩሉ እናቱ በስቃይና በሐዘን ተውጣ ስለአየ በሐዘን ላይ ሐዘን ተጫነው ተጨመረበት፡፡ የሁለቱም ሐዘን ተገናኘ፣ መከራቸውን ተለዋወጡ፣ እናት ልጅዋን አጽናናች፣ ልጅም ደግሞ እናቱን አጽናና፡፡ እያንዳንዳቸው ስቃያቸውን ለመሸከም ተጋገዙ፡፡

ዛሬም ጌታ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ በመንገዶች እያለፈ ስናገኘው ምን ይሰማናል፣ ምን እንለዋለን፣ እንዴት አድርገን እናየዋለን፣ እንደገና በጊዜያችን ደክሞ፣ ቆሽሾ ፊቱ በላብና በምራቅ በአክታ በአፈር መልኩ ተለውጦ እንየው? ስንቴ ተዋርዶ እናየዋለን? ግን ካየነውስ ምን እናደርግለታለን? እንደ እመቤታችን ማርያም ሄደን እናጽናናዋለን መከራውንና ኀዘኑን እንካፈላለን ወይስ ደግሞ እንዳላየነው ዝም ብለን እናልፋለን? ጠላቶቹ ሲያሰቃዩት ስሙን ሲያዋርዱ ስናይ እርሱንና ሥራውን ለማጥፋት ሲታገሉ ስናይ ምን እናደርጋለን? እኛ ልንክሰው መከራውን ልናቃልልለት ልናጽናናው እንታገል፣ እንጣር፡፡ ከዚህ በፊት እየሱስን ተዋርዶ አዝኖ ስናይ ሳንደነግጥለት፣ ሳንራራለት፣ ሳናጽናናው ዝም ብለን ከሆነ ለወደፊት ወደ እርሱ ቀርበን እንደ አቅማችን በተቻለን መጠን እናጽናናው እንካሰው፡፡

 

19 April 2024, 16:24