ፈልግ

የሕማማት ሣምንት የሕማማት ሣምንት 

የሕማማት ሣምንት

በኢትዮጲያ በሚገኙ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ በሚያዝያ 21/2016 ዓ.ም የሕማማት ሳምንት መጀመሩ ይታወሳል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ እየሩሳሌም ከገባበት የሆሳህና እለተ ሰንበት አንስቶ ሞትን ድል አድርጎ እሰከ ሚነሳበት የትንሳኤ እሁድ ድረስ ያለውን የአንድ ሳምንት ጊዜ የሚያመልክት ነው።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራት ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

1.     እሁድ እለት

ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ (ሉቃስ 19፡28-40)

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሞአቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደ ሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤ “በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው።

2.     ሰኞ እለት

ኢየሱስ በቢታንያ ሽቱ መቀባቱ (ዩሐንስ 12፡1-11)

የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ። በዚያም ለኢየሱስ ሲባል ራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከእርሱ ጋር በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር። ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በጠጒሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዓዛ ሞላው።

ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቊሮ አልነበረም።

ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለ ሆነ እንድታቈየው ተዋት፤ ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁል ጊዜ አታገኙኝም።”

በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤ ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።

3.     ማክሰኞ እለት

አልፎ እንደሚሰጥ ኢየሱስ መናገሩ (ዮሐንስ 13፡18-38)

“ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን አብሮኝ የቈረሰ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። “ሲፈጸም እኔ እንደሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ።እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።” ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ።

ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደሆነ ጠይቀው” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህን ቊራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቊራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። ይሁዳም ቊራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት።

4.     ረቡዕ እለት

ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ (ማቴ 26፡14-26)

ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውና የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።

የጌታ ራት

በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው።

5.     ሐሙስ እለት

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ (ዮሐንስ 13፡1-15)

ጊዜው ልክ ከፋሲካ በዓል በፊት ነበረ፤ ኢየሱስም ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዐወቀ። በዓለም የነበሩትን፣ የራሱ የሆኑትን ወደዳቸው፤ በፍጹም ፍቅሩም ወደዳቸው።

እራትም ቀርቦ ሳለ፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ የስምዖንን ልጅ የአስቆሮቱን ይሁዳ ልብ አነሣሥቶ ነበር። ኢየሱስም፣ አብ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር እንዳደረገለት፣ ከእግዚአብሔር እንደ ተላከና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚመለስ ዐውቆ፣ ከእራት ተነሣ፤ መጐናጸፊያውን አስቀመጠ፤ ወገቡንም በፎጣ ታጠቀ። ከዚያም በመታጠቢያው ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ በታጠቀው ፎጣ ያብስ ጀመር።

ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እግሬን ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የማደርገውን አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “የለም፤ እግሬን ከቶ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፣ “ካላጠብሁህማ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም ራሴንም ዕጠበኝ” አለው።

ኢየሱስም፣ “ገላውን የታጠበ ሰው የሚያስፈልገው እግሩን ብቻ መታጠብ ነው፤ የቀረው አካሉ ግን ንጹሕ ነው። ሁላችሁም ባትሆኑ፣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ” አለው። “ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ዐጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።

ኢየሱስ መከራውን ከመቀበሉ በፊት  ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ከመብላቱ በፊት የሐዋርያቱን እግር ያጠበበት፣ እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የጀመረውን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድያስቀጥሉ በማሰብ ምስጢረ ክህነትን የመሰረተበት እና በተጨማሪም የመጨረሻ ራት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የተካፈለበት ምስጢረ ቅዱስ ቁራባንን የመሰረተበት እለት ነው::

6.     ዐርብ እለት

ኢየሱስ እንዲሰቀል ተፈረደበት (ዮሐንስ 19፡1-42)

ጲላጦስም ኢየሱስን ወስዶ አስገረፈው። ወታደሮችም የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አደረጉ፤ ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤ እየተመላለሱም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ በጥፊ ይመቱት ነበር።

ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ውጭ ወጥቶ፣ “እንግዲህ ወደ እናንተ ያወጣሁት ለክስ የሚያደርስ ወንጀል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ ነው” አላቸው። ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው።

የካህናት አለቆችና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው። አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።

ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤ ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።

ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው። ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።

ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ “የድንጋይ ንጣፍ” በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ “ገበታ” ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ። ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር።

ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ። የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት። በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።

ስቅለት

ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ እርሱም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በአራማይክ “ጎልጎታ” ተብሎ ወደሚጠራው “የራስ ቅል” ወደ ተባለው ቦታ ወጣ። በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር ሁለት ሰዎች፣ አንዱን በዚህ በኩል፣ ሌላውን በዚያ በኩል፣ ኢየሱስንም በመካከል አድርገው ሰቀሉ።

ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር። የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። ጲላጦስም፣ “በቃ፤ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ።

ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር። ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣ “ልብሴን ተከፋፈሉት፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።

በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወድደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።

የኢየሱስ መሞት

ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም የሖመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ሖምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ።

ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት። ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ። ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ። ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቷል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል። ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከዐጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣ ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው።

የኢየሱስ መቀበር

ከዚህ በኋላ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን በድን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነው፤ ዮሴፍም አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። እርሱም ጲላጦስን ካስፈቀደ በኋላ መጥቶ በድኑን ወሰደ። ከዚህ ቀደም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ አንድ መቶ ሊትር ያህል የሚመዝን የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። እነርሱም የኢየሱስን በድን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ ከፈኑት። ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታም የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልቱም ስፍራ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። ዕለቱ ለአይሁድ የሰንበት መዘጋጃ ቀን ስለ ነበርና መቃብሩም ቅርብ ስለሆነ ኢየሱስን በዚያ ቀበሩት።

29 April 2024, 14:39