ፈልግ

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተካሄደ! ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተካሄደ! 

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተካሄደ!

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ማለትም ከአፍሪካ የሃይማኖት ተቋማት ህብረት (United Religions Initiative ‘URI’ for Africa) እና ከቡድን 20 የሃይማኖቶች ህብረት ፎረም (Interfaith Forum Association)፣ ከአፍሪካ ህብረት የዜጎች እና ዲያስፖራ ዳይሬክቶሬት እና ከአፍሪካን ህብረት የሃይማኖቶች ውይይት ፎረም ጋር በመተባበር በክብርት የኢፌዲሪ መንግስት ፕረዚዳንት የበላይ ጠባቂነት የተዘጋጀው ሁለተኛው አለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “የእምነት ተቋማት ትብብር ለሰላም፣ ለሰብዓዊ ክብር፣ ልማትን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር እንዲሁም የጥላቻ ንግግርን፣ ግጭትን እና ብሄርተኝነትን ለመቃወም” በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ አዲስ አበባ በሚገኘው ሂልተን ሆቴል ዛሬ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጀምሯል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዚህም ጉባኤ ላይ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንትን ጨምሮ ክቡር ዶክተር ኬይረዲን ተዘራ የኢፈዲሪ የሰላም ሚንስተር ሚኒስትር ዴኤታ፣ አምባሳደር ሙሴ ሃይሉ የአፍሪካ ህብረት የሃይማኖት ተቋማት ኢኒሺዬቲቭ የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር እና የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ተጠሪ፣ የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ ተሳታፊዎች፣ የተከበሩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የየሃገራት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ “የሃይማኖት ወይም የእምነት ተቋማት ትብብር ለሰላም፣ ለሰብአዊ ክብርን፣ ልማትን አከባቢ ጥበቃን ለማጠናከር እና የጥላቻ ንግግርን፣ ግጭትን እና ጠባብ ብሄርተኝነትን ወይንም ትምክህተኝነትን ለመቃወም” በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው ይሄ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት የሚታሰበው የዓለም ሃይማኖቶች ትብብር ሳምንት እና በየዓመቱ ሚያዚያ 5 ታስቦ የሚውለውን የዓለም አቀፉን የወርቃማ ህግ ቀንን ታሳቢ በማድረግ የዓለም ሃይማኖቶች ትብብር እና ቅንጅት ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው ብለዋል።

ጉባኤው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ባለፈው ዓመት የተዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የምክክር ጉባኤ በዋናነት ሃገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በሆኑ ገዳዮች፥ በተለይም በሰላም፣ በሰብአዊ ክብር፣ በአከባቢ ጥበቃ፣ በዘላቂ ልማት፣ እና በሃይማኖት ወይም በእምነት ነፃነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል።

የመጀመሪያው ጉባኤ ከያዛቸው ዓላማዎች አንዱ፣ የአፍሪካ ህብረት 55 አባል ሃገራቱን በመወከል የG20 አባል እንዲሆን ምክረ ሃሳብ የቀረበበት እና ሃሳቡን ሌሎች አጋሮች እና የሃገራት መሪዎች ጭምር ድጋፍ በማግኘቱ መስከረም 2023 በሃገረ ህንድ፣ በኒውደልሂ ከተማ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሃገራት የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ ላይ ምክረ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ፥ ህብረቱ የቡድን 20 ቋሚ አባል እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

ይህም ጉባኤው በሃገራችን ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰን፥ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጭምር አዎንታዊ ሚናውን ለመወጣት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

ዓለም አቀፍ ጉባኤው በዋናነት በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ጠንካራ መሰረት ያለው የሰላም እና የአብሮነት የመከበር እሴትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወርቃማ ህግን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ለማጠናከር ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለሰብአዊነት፣ ለአከባቢ ጥበቃ እና ለሃይማኖትና እምነት ነፃነት መጠበቅ ያላቸውን ገንቢ እና አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ እና ከሃይማኖቶች አስተምህሮ ጋራ ለሚቃረኑ አሉታዊ አስተሳሰቦችና ህገ ወጥ ተግባራትን በተባበረ አቅም ለመከላከል እንዲቻል ሃገራት አስፈላጊ የሆኑ የህግ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ አማራጭ ሃሳብ ይቀርባል ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የምክክር ጉባኤው ሃገሪቷ ለብሄር እና ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች እና እምነቶች ብዙሃነት የተገነባች ምድረ ቀደምት የሚለውን የቱሪዝም መገለጫ በተጨባጭ ማሳያ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ከማስተዋወቁም ባሻገር፥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የገፅታ ግንባታ እና ሃገራችን የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማስፋት የላቀ አስተዋጽዖ እንደሚያበርክትም ተገልጿል።

ጉባኤው ከተባባሪ አጋሮች ጋር በመሆን እንዲህ አይነቱን ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ጥቃሚ ልምዶችን እና ተመክሮዎችን ከማግኘቱም ባለፈ የሃይማኖት ተቋማት ተልእኮዋቸው ድንበር ዬለሽ ከመሆኑ አንፃር ሁሉንም የሰው ልጆች እንደ አንድ ቤተሰብ በማስተሳሰር ኢፍትሃዊነትን እና በደልን፣ ሃጥያትን እና ኢ-ሃይማኖታዊነትን ለመከላከልም ይረዳል የተባለ ሲሆን፥ ይህም ጉባኤው ከተቋቋመበት መሰረታዊ መርህ እና ዓላማ ጋራ በእጅጉ የሚስማማ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል።

“የኃይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸው ድንበር የለሽ ነው” ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመጨረሻም ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በዚህ መልኩ እንዲከናወን ልዩ ልዩ ተሳትፎ እና አስተዋጽዖ ላበርከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋና በማቅረብ ጉባኤው ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

 

15 April 2024, 13:01