ፈልግ

ሲስተር አንቶኒያ ኤሲየን እና ቡድናቸው በአክዋ ኢቦም፣ ናይጄሪያ ሲስተር አንቶኒያ ኤሲየን እና ቡድናቸው በአክዋ ኢቦም፣ ናይጄሪያ 

አንድ የናይጄሪያ መነኩሴ ‘ያክ ኢያማ’ የሚባል ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚታገል ቡድን አደራጁ

እ.አ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ በናይጄሪያ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እየተንሰራፋ የመጣ መራር እውነታ ሲሆን፥ አሁንም ድረስ በሚያሳዝን ሁኔታ ተግባሩ ቀጥሏል። የናይጄሪያ ብጹአን ጳጳሳት እና ዋና የበላይ አለቆች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት፥ ሲስተር አንቶኒያ ኤሲየን እና ቡድናቸው በአኩዋ ኢቦም ግዛት በሚገኙ የገጠር መንደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ጀምረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሲስተር አንቶኒያ ኤም ኤሲየን በናይጄሪያ የሚገኘው የቅዱሱ ሕፃን የኢየሱስ ባሪያዎች ጉባኤ አባል ሲሆኑ፥ የሃይማኖት ህብረተሰብ ጥናት (ሶሺዮሎጂ) ፕሮፌሰር እና አሁን ላይ የናይጄሪያ ኡዮ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

ሲስተር አንቶኒያ ምንም እንኳን በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት ስራ ቢበዛባቸውም፥ የህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ለመርዳት በሙሉ ልብ በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ዘመቻ ላይ በግንዛቤ እና በክህሎት ማስግኛ ፕሮግራሞች በመሳተፍ ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ።

“የተጎጂዎች ታሪክ ልቤን ነክቶኛል፥ መተኛት አልቻልኩም፥ ለእነሱ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብኝ” ሲሉ ሲስተር አንቶኒያ ተናግረዋል።

የህጻናት እና ታዳጊዎችን ህይወት መታደግ ተችሏል

ከ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲስተር አንቶኒያ በአክዋ ኢቦም ግዛት ውስጥ በሚገኙ የገጠር መንደሮች ውስጥ በርካታ ሃዋሪያዊ ስራዎችን በማከናወን የአከባቢው ማህበረሰብ ስለ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ያለውንን ግንዛቤ ማሳደግ ችለዋል።

ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ለህግ አካላት ተላለፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ከአካባቢው የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር በንቃት እየሰሩ ይገኛሉ።

እያደረጉት ባለው ያላሰለሰ ጥረት በቅርቡ በሀገሪቱ ውስጥ ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተሸጡ በርካታ ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን መታደግ ችለዋል።

ሲስተር አንቶኒያ “ከልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ የሚያውቁት አንድ ትልቅ ሰው እንደሸጣቸው ሲነግሩኝ በጣም ደነገጥኩ” ካሉ በኋላ፥ “መጀመሪያ የወሰድኩት እርምጃ የሁለቱ ልጆች አባት እንደጠፉ ሲነግሩኝ ፖሊስ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር መምሪያን እንዲሳተፉ ማድረግ ነበር፥ እነሱም አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተው ህጻናቱን መታደግ ችለዋል” በማለት ስለጉዳዩ አብራርተዋል።

የማህበረሰብ የድርጊት ቡድን

ሲስተር አንቶኒያ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በጀመሩት የ ‘ያክ ኢያማ ፕሮጀክት’ ላይ የሀገር ውስጥ ለጋሾች እና ባለድርሻ አካላት የሚገኙበት የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ ‘የማህበረሰብ የተግባር ቡድን’ ለመመስረት ሀሳብ አቅርበዋል።

ይህም የማህበረሰብ መሪዎችን እና ወጣቶችን በማሰልጠን ለአካባቢው ማህበረሰብ አባላት ከህገወጥ አዘዋዋሪዎች ለመጠበቅ አብረው የቡድኑ አምባሳደሮች እንዲሆኑ እና ወጣቶችን ስለኑሮአቸው ወይም መተዳደሪያቸው ክህሎት እንዲኖራቸው ማብቃትን ይጠይቃል።

አብረው ለሚሰሩት ገዳማዊያን እህቶች ድጋፍ ምስጋና ይግባውና ከሀገር ውስጥ ለጋሾች እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው አሪስ ፋውንዴሽን ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ሲስተር አንቶኒያ እና ቡድኖቻቸው በአኳ ኢቦም ግዛት ሥር በሚገኘው በአቢያኦክፖ ኢኮት አባሲ ኢንያንግ የገጠር ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ተጋላጭ ሰዎችን መርዳት ችለዋል።

“ይህንን ስራ ለሚደግፉ ሁሉ፣ በተለይም ለአጋዦቻችን በየቀኑ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ብሎም እጸልያለሁ” ሲሉ ሲስተር አንቶኒያ ተናግረዋል።

ፀረ-ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዘመቻዎች

በአክዋ ኢቦም ግዛት አንዳንድ የያክ ኢያማ ቡድን የፀረ-ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዘመቻዎች በገበያ ቦታዎች፣ በጎዳናዎች እና መንደሮች ውስጥ ተካሂደዋል።

ሲስተር አንቶኒያ እና ቡድናቸው ከባድ ሙቀት እና ከባድ ዝናብ ሳይበግራቸው ወደ ህብረተሰቡ በመሄድ ህጻናትን የሚሰርቁ እና ታዳጊዎችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ለህገ ወጥ ዝውውር የሚያማልሉ ሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና እንዴት ይህንን ክፉ ተግባር ለመግታት የሚቻሉባቸው መንገዶች ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ለማሳወቅ ዓላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህንንም በማስመልከት “ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በተለያዩ መንገዶች እንዴት ህዝባችንን እንደሚያታልሉ ማስተማር መቀጠል አለብን፥ ድምፆቻችንም ጎልተው መሰማት አለባቸው፥ በተለይም አንዳንድ የማህበረሰቡ አባላት ሰለባ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ማስተማሩን መቀጠል አለብን” ሲሉ ሲስተር አንቶኒያ አሳስበዋል።

በማከልም “የያክ ኢያማ ቡድን አንዳንድ የአካባቢ ማህበረሰቦችን ለመድረስ ለሰዓታት በእግር መጓዝ የነበረባቸው ጊዜያት ነበሩ፥ ነገር ግን ይሄንን ሲያደርጉ በደስታ እና እርካታ ነበር” ብለዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖ በናይጄሪያ ውስጥ ያሉ ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በጣም ተጋላጭ እና የተገለሉ ማህበረሰቦች ላይ ማነጣጠራቸውን ቀጥለዋል።

ሆኖም ብዙ ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም፣ ሲስተር አንቶኒያ እና ቡድኖቻቸው ተስፋ ሳይቆርጡ በገጠር ውስጥ ለሚገኙ ማህበረሰቦች ግንዛቤ ማስጨበጣቸውን ቀጥለዋል፥ ወጣቶችን በፀረ-ህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ለማበረታታት እንዲሁም በህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን እና በጣም ተጋላጭ ሰዎች ከሁሉም በላይ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማበረታታት የክህሎት ማግኛ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
 

09 May 2024, 18:58