ፈልግ

የፍኖተ መስቀል ወይም የመስቀል መንገድ ጸሎት

ይህም የስቅለተ ዓርብ እለት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊነት፣ በጾም እና በጸሎት፣ መጽዋዕት በመስጠት እና በስግደት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃዮን በተቀበለበት ወቅት የተጓዛቸውን አስራ ዐራት የስቃይ መንገዶች የሚታወሱበት የመስቀል መንገድ ጸሎት እና ስግደር በማድርግ እንደ ሚከበር ይታወቃል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“ፍኖተ መስቀል ወይም የመስቀል መንገድ” ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል ተሰቅሎ ለመሞት መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ያደረገውን የጭንቅ መንገድ የሚያሳስብ ጸሎት ነው። በዚህ ጸሎት ውስጥ ምእመናን ብዙ የነፍስ ጥቅም ያገኙበታል፤ ሙሉ ሥርየት ኃጢአት የሚገኝበት ጸሎት ነው። በ14ቱ ምስሎች ላይ የተመለከቱትን የኢየሱስ ክርሰቶስን ሕማማትና የደረሰበትን መከራና ጭንቅ በማሰብ እያዘኑ ካንዱ ምስል ወዳንዱ ምስል እየተዘዋወሩ የሚያደርጉት ጸሎት ነው።

 

በመንበረ ታቦት ፊት የሚደገም ጸሎት፤

አምላክ ሆይ፤

ጸሎታችንና ሥራችን በሙሉ ባንተ እንዲጀመርና ባንተም እንዲያልቅልን በሥራዎቻችን አስቀድመህ እርዳን፤ ረድተህም አስፈጽመን ብለን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንለምንሃለን። አሜን!

የፀፀት ሥራ

የተወደድህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ በክፉ ሥራዎቻችንና በኃጢአቶቻችን አንተን ስለበደልንህ እየተፀፀትንና እያዘንን እነሆ በቅዱስ ፊትህ ተደፍተን እንገኛለን። ከእንግዲህ ወዲህ አንበድልህም ብለን ቁርጥ ፈቃድ እናደርጋለን፤ ፀፀታችንን ተቀበልልን። ሕማማትህን በመንፈሳዊነት እንድናስብና የኃጢአቶቻችንን ይቅርታና ሥርየት ለማግኘት እንድንችል ጸጋህን ስጠን። የምናገኘው ሥርየት ለራሳችንና በንስሐ ቦታ ለሚገኙ ነፍሶች ሁሉ እንዲሆንልን እንፈልጋለን። አሜን!

  1፤    ያዘን እናት የንባ ባሕር፤ ቁማ ነበር እመስቀል ሥር፣ ተቸንክራ በፍቅር፡፡

ቅድስት እናት ለዘላለም፤ በልቤ ውሰጥ እንዲታተም፤ የልጅሽ የሱስ ሕማም፡፡

1ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ ሞት ተፈረደበት

የጸሎቱ መሪ፦ክርስቶስ ሆይ እንሰግድልሃለን

ሕዝብ፦ በተቀደሰ መስቀል ዓለምን ያዳንህ አንተ ነህና እንሰግድልሃለን እናመሰግንህማለን።

ስለኛ የሚያስቅቅ የሞት ፍርድ የተፈረደብህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፤ እኛ በኃጢአታችን ዘለዓለማዊ ቅጣትን አፈራን፤ አንተ በምሕረትህ ከዘላለማዊ ሞት አድነን። አሜን!

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፤ ማረን።

  2፤    ከባድ ሀዘን የተጫናት፣ ነፍስዋን ቦታ የጠበባት

የኀዘን ሰይፍ የወጋት፤ ቅድስት እናት ለዘላለም

2ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ መስቀሉን ለመሸከም ተቀበለ፤

የጸሎቱ መሪ፦ ክርስቶስ ሆይ እንሰግድልሃለን

ሕዝብ፦ በተቀደሰ መስቀል ዓለምን ያዳንህ አንተ ነህና እንሰግድልሃለን እናመሰግንህማለን።

ከባዱን መስቀል የተሸከምህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን።

እኛም የችግሮችንና የመከራዎችን መስቀል በትዕግሥትና በደስታ ለመቀበል እንድንችል ጸጋህን ስጠን። አሜን።

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፤ ሕ፤ ማረን።

  3፤    ዋ የጭንቅሽ የንባሽ ባሕር፤ መጠን የለው ስፍር ቁጥር፤

ቅድስት ያንድ አምላክ ወንበር፣ ቅድስት እናት ለዘላለም

3ኛ ማረፊያ

ኢየሱስ መስቀሉን እንደተሸከመ ወደቀ፡፡

የጸሎቱ መሪ፦ ክርስቶስ ሆይ እንሰግድልሃለን

ምዕመን፦ በተቀደሰው መስቀል ዓለምን ያዳንህ አንተ ነህና እንሰግድልሃለን እናመሰግንህሣለን፡፡

መስቀልን እንደተሸከምህ የወደቅህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ ከቶ በኃጢአት ወድቀን እንዳናሳዝንህ ጠብቀን፡፡ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  4፤    ምን ይመስል ኀዘንሽ፤ ከመስቀሉ ያ ልጅሽ፤

ቁልቁል አንቺን ሲያይሽ፡፡ ቅድስት እናት —

4ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ ከቅድስት እናቱ ጋር ተገናኘ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

በቀራንዮ መንገድ ከኀዘንተኛይቱ እናትህ ጋር የተገናኘህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡

በሞታችን ጊዜ ካንተ ከውዱ አባታችን ጋር እንድንገናኝ ጸጋን ስጠን፤ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡

  5፤    ማነው ከኛ እስዋን አይቶ፣ያንን ጭንቋን ተመልክቶ

እንባ የማይወጣው ከቶ። ቅድስት እናት —

5ኛ ማረፊያ

ቀሬናዊው ስምዖን ኢየሱስን ረዳ፡፡

ክርስቶስ ሆይ

በተቀደሰ መስቀል

የምትሰቀልበትን ግንድ በመሸከም ቀሬናዊው ስምዖን የረዳህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ፣ እንሰግድልሃለን፡፡ እኛም የቅድስት ሕግህን ቀላል ቀንበር ወደን እንጅንሸከም ጸጋን ስጠን፡፡ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡

  6፤    ማነው ከኛ ሳያዝንላት፣ ደፍሮ ጭንቋን የሚያይላት

ለዚያች ላንድ አምላክ እናት። ቅድስት እናት

6ኛ ማረፊያ

ቨሮኒካ የምትባል ሴት የኢየሱስን ፊት ጠረገችለት፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ቨሮኒካ ፊትህን የጠረገችልህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ ፊትህ በመሐረቧ ላይ ታታሞ እንደተገኘ እንዲሁ እኛ የሰውን ይሉኝታ ሁሉ እንድንንቅና አንተ በልባችን ውስጥ ታትመህ እንድትኖር አድርግልን፤ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡

  7፤    ስለ ሕዝቡ ኃጢአት፣ የሱስን ሲገርፉት

ታየው ነበር በጭንቀት፡፡ ቅድስት እናት —

7ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ ሁለተኛ ጊዜ ወደቀ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ሁለተኛ ጊዜ የወደቅህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ ደግሞ በኃጢአት ወድቀን እንዳናሳዝንህ ከክፉ ምክንያቶችም እንድንርቅ ጸጋን ስጠን፡፡ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  8፤    ያንን ልጅዋን ወዳጅዋን፣ እመስቀል ላይ ድካሙን

ታየው ነበር ሞቱን፡፡ ቅድስት እናት

8ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ሴቶች መከረ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

የጭንቅ መንገድህን በምትጓዝበት ጊዜ የኢየሩሳሌምን ሴቶች የመከርህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ በሕይወታችንና በሞታችንም ጊዜ ካንተ ዘንድ መጥናናትን ለማግኘት እንድንችል በኃጢአቶቻችን እናለቅስ ዘንድ አድርገን አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  9፤    ካንቺ ጋር እንዳነባ፣ ያንቺ ኀዘን ልቤን ይግባ

ቅድስት የፍቅር አበባ፡፡ ቅድስት እናት —

9ኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ሶስተኛ ጊዜ ወደቀ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ሶስተኛ ጊዜ የወደቅህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ በሰማይ ካንተ ዘንድ ከፍ ብለን እንድንገኝ በምድር እውነተኛውን ትሕትና የምናደርግበትን ጸጋ ስጠን አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

 10፤    ልቤ እንደ እሳት እንዲቃጠል፣ ኢየሱስን በማገልገል

አማልጅኝ ቅድስት ድንግል። ቅድስት እናት —

10ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ ልብሶቹን ተገፈፈ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ልብሶችህን የተገፈፍህና መራር ኀሞት የጠጣህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፤ በኛ ላይ ነውር ሆኖ የሚታየውን ነገር ሁሉ አውቀን እንድንጥልና የዚህን ዓለም መጥፎ ፍትወት ሁሉ እንድንጠላ አድርገን፡፡ አሜን!

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  11፤   ያ አንዱ ልጅሽ የሞተልሽ፣ ያለመጠን የወደደኝ

ሕማሙ ሕማም ይሁነኝ፡፡ ቅድስት እናት —

11ኛ ማረፊያ

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸነከረ

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ስለኛ በመስቀል ላይ የተቸነከርህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ በሕዋሳቶቻችን ላይ ተጋድሎን እንድናደርግና ክፉ ዝንባሌዎቻችንን እንድንቸነከር ጸጋን ስጠን፡፡ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  12፤ ላልቅስ ላልቅስ ካንቺ ጋራ፣ ነፍሴ ሳለች ሳላባራ

ስለ ክርስቶስ መከራ፡፡ ቅድስት እናት —

12ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሞተ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ስለኛ በመስቀል ላይ ተቸንክረህ የሞትህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ የዓለምን ፍቅር ሁሉ ትተን ከመጥፎ ዝንባሌዎች ሁሉ እንድንለይ ጸጋ ስጠን አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  13፤   እመስቀል ሥር በተገኘሁ፣ ካንቺ ጋራ ዋይ በነበርሁ

በደም እንባ በታጠብሁ፡፡ ቅድስት እናት —

13ኛ ማረፊያ፤

ኢየሱስን ከመስቀል አውርደው ለናቱ አስታቀፏዋት፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ከመስቀል ባወረዱህ ጊዜ ኀዘንተኛይቱ እናትህ የታቀፈችህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፤ ሞታችን በእጆችህና በቅድስት እናትህ በማርያም እጆች እንዲሆንልን ከክፉም ነገር ሁሉ እንድንድን ጸጋን ስጠን፡፡ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  14፤ ከደናግል ሁሉ ድንግል፣ እንባ ይመጣል ስላንቺ ሲል

ስለ ልጅሽም መስቀል፡፡ ቅድስት እናት —

14ኛ ማረፊያ

ኢየሱስ ተቀበረ፡፡

ክርስቶስ ሆይ —

በተቀደሰ መስቀል —

ለኛ ስትል ሞተህ የተቀበርህ ደጉ ኢየሱስ ሆይ እንሰግድልሃለን፡፡ ክፋቶቻችንና ፍትወቶቻችን ካንተ ጋር እንዲቀበሩ አድርግልን፡፡ በሕማማትህና በሞትህ ያስገኘኸንን ዘለዓለማዊ ክብር ለመውረስ በታላቁ ፍርድ ቀን በክብር ለመነሳት አብቃን፤ አሜን፡፡

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና ለወልድ — ጌታችን ሆይ ማረን፡፡ አሜን

  15፤ ሸክሜ ይሁን ያምላክ ሞቱ፣ ደግሞም ርስቴ ሕማማቱ

ትዝታየም ግርፋቱ፡፡ ቅድስት እናት —

  16፤ እኔን ይውጋኝ ይውጋኝ ቁስሉ፣ ስንክር ያረገኝ በመስቀሉ

እንጸልይ

ባንድ ልጅህ ደም የነፍስን ሕይወት የሚሰጠንን መስቀል የቀባህ አምላክ ሆይ የቅዱስ መስቀልን ክብር የሚወድ ሰውን ሁሉ በልጅህ ልመና ጠብቅ፡፡

ስለ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሐሳብ እንጸልይ

አባታችን — ሰላም ላንቺ — ለአብና —

የቅዱስ ጳውሎስ ቃል

ኢየሱስ የባርያን መልክ ይዞ ሰውን መስሎ ሰው መሆኑም ባኗኗሩ ታይቶ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ ለሞትም እስኪደርስ ድረስ ታዛዥ ሆና ሞቱም በመስቀል ሆኖ ራሱን አዋረደ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ እጅግ አከበረው፡፡ ለኢየሱስ ስም በሰማይ በምድር በሲኦልም የሚገኝ ጉልበት ሁሉ ይሰግድ ዘንድ፤ አንደበትም ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር እንዳለ ይታመን ዘንድ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምን ሰጠው፡፡

የመከራው ማጠቃለያ ጸሎት፤

ዓለምን ለማዳን መወለድን በድኸነት መኖርን በአይሁድ እጅ መጣልን፤ ከከዳተኛው ይሁዳ በመሳም አልፎ መስጠትን መታሠርን፤ እንደ ንጹሕ በግ ለመሥዋዕት መጐተትን፤ ከሐናና በቀያፋ በጲላጦስና በሄሮድስ ፊት አላግባብ ቀርበህ መቆምን፤ በሐሰተኞች ምስክሮች መከሰስን፤ መገረፍን፤ በጥፊ መመታትን፤ መጨነቅን፤ በምራቅ መተፋትን፤ በእሾህ አክሊል መቀዳጀትን፤ በበትር መመታትን፤ ፊት መሸፈንን፤ ልብሶች መገፈፍን፤ በመስቀል ላይ መቸንከርን፤ ከወንበዴዎች ጋራ መቆጠርን፤ ሐሞትንና ኮምጣጣን መጠጣትን፤ በጦርም መወጋትን የፈለግህ፤ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለዘለዓለም የምትኖርና የምትነግሥ አምላክ ሆይ ስለነዚህ እጅግ ስለተቀደሱት ሕማማትህና ስለ ቅዱስ መስቀልህ ስለሞትህም ከገሃነም ሥቃዮች ሠውረን፤ ካንተም ጋራ በቀኝ የተሰቀለውን ፈያታ ወዳደረስህበት ቦታ አድርሰን፡፡ አሜን፡፡

 

03 May 2024, 11:41