ፈልግ

ከትንሣኤ በኋላ ረቡዕ ሚያዝያ 30/2016 ከትንሣኤ በኋላ ረቡዕ ሚያዝያ 30/2016 

እኛም እንነሣ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተነሣ ብቻ ሳይሆን እኛም እንደምንነሣ ማመን አለብን። ይህም እምነት ሞትን በመልካም እንጂ በመጥፎ እንዳንመለከታት ይረዳናል። ይህንንም ስንል ሞት ከዚህ ምድራዊ እስር ቤት መውጣት ይህንን ስቃይ የሞላበት ጊዜያዊ ኑሮ መተው ማለት ነው። በሞት ሕይወታችን ይለወጣል እንጂ አይጠፋም።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የክርስቶስ ሞት ሕይወታችን፣ ትንሣኤውም ደግሞ ትንሣኤያችን ነው። “ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።

ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኗልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ” (1ኛ ቆሮ 15፣12-21) እያለ ቅዱስ ጳውሎስ ያረጋጥልናል። ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ ገብቶ እንዳልጠፋ እኛም በመቃብር ውስጥ አንጠፋም። በሞት ምክንያት በመቃብር ውስጥ ገብቶ የተበላሸውንና ወደ አፈርነት የተለወጠው ሥጋችን ጊዜው ሲደርስ ወደ ድሮው ፍጥረቱ ይመለሳል። ከነበረበት ከመቃብር ወጥቶ ሕይወት ያለው ሰው ሆኖ ይነሳል። ማርታ ኢየሱስን «ጌታ ሆይ አንተ እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር» አለችው። እርሱም ደግሞ «ወንድምሽ ከሞት ይነሣል» አላት። «በመጨረሻው ቀን ከሞት እንዲነሣ አምናለሁ» ስትል መለሰችለት። እንደገናም ኢየሱስ «ትንሣኤ ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል» (ዮሐ. 11፣32-44) በማለት ወንድሟን አስነሣላት። ኢየሱስ ከአልዓዛር ሌሎች ሙታንን ከሞት አስነሣቸው። በዚህም ደግሞ በዓለም መጨረሻ እኛን ሁላችንንም እንደሚያስነሳን ያስገነዝበናል።

«ወንድሞቼ ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ስለ ሞቱት ሰዎች እውነቱን እንድታውቁ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደሞተና ከሞት እንደተነሣ እናምናለን። ስለዚህ በኢየሱስ የሞቱትን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ጋር ያስነሳቸዋል» (1ኛ ተሰ.4፣13 ) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል። በሞት ሕይወታችን ተቋርጦ ወደ ቀድሞው ከንቱነት አንመለስም ከሞትን በኋላ በተወሰነ ጊዜ ተነስተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንጀምራለን። ራሱ ኢየሱስም ተስፋ ሰጥቶናል። በትንሣኤው መሪ ሆኖናል። ትንሣኤያችን ዋስትና ነው። እግዚአብሔር ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንድንነግሥ እንጂ እንድንጠፋ ብሎ አልፈጠረንም።

  «በሙታን ትንሣኤ አምናለሁ» እያለች ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች። ገበሬ የሚዘራው ዘር እንደሚበቅልለት አውቆ በሙሉ እምነት መሬት ላይ እንደሚበትን እኛም ደግሞ እንደምንነሣ አውቀን ሞትን እንጥላ። የሚያስፈራንን የሞት ሐሳብ በዚህ የትንሣኤ ሐሳብ እናሸንፈው።

08 May 2024, 18:47