ካሪታስ ኢንዶኔዥያ 18ኛ ዓመቱን ሲያከብር ወደፊት በተሻለ መልኩ ለመስራት ቃል እገባለሁ አለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኢንዶኔዥያ ብጹአን ጳጳሳት፣ ለጋሾች እና በኤጀንሲው የእርዳታ መርሃ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ ቡድኖች በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ ዝግጅቱ ተካሂዷል።
የአደጋ ጊዜ ዕርዳታ ፓኬጆችን በማቅረብ የሚታወቀው ካሪታስ ኢንዶኔዢያ፣ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ገንዘብ በመሰብሰብ በተለያዩ ፕሮግራሞቹ የተቸገሩትን በመርዳት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።
የካሪታስ ኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት የሆኑት የባንዱንግ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ አንቶን ሱቢያንቶ በክብረ በዓሉ ወቅት ባደረጉት ንግግር የኤጀንሲውን ሚና በማጉላት “ዛሬ ከበርካታ ብጹአን ጳጳሳት ጋር በመሆን፣ በኢንዶኔዥያ እና በመላው ዓለም ያለችውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የርህራሄ መንፈስን ላሳየው እና የሰብአዊነት መገለጫ ለሆነው ተቋማችን ‘ካሪና ክዊ’ ወይም ካሪታስ ኢንዶኔዥያ እግዚያብሄርን እናመሰግናለን” ብለዋል።
ብጹእ አቡነ ሱቢያንቶ በንግግራቸው ኤጀንሲው በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰራ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ለነበሩ ለጋሽ የካቶሊክ ተቋማትን እና ግለሰቦችን ልዩ ተነሳሽነት በማድነቅ፥ ይህ አስተዋጽኦ “በክርስትና እምነት እና እሴቶች የሚመራ ነው፣ ይህም የወደፊት ሕይወታችንን በበጎ ምግባር ያበለጽጋል” ብለዋል።
በሃገር ውስጥ ከሚያደርገው የእርዳታ ስራዎች በተጨማሪ በቱርክ እና በባንግላዲሽ በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ በካሪታስ ኢንዶኔዥያ ለሃገራቱ የተደረጉትን የቅርብ ጊዜ የእርዳታ እርምጃዎችን በመጥቀስ ‘የካሪና ክዊ’ የሰብአዊ ጥረት ከኢንዶኔዥያ ባሻገር መድረሱን አመላክተዋል።
የፓላንካ ራያ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሱትሪስ ናትማካ በበኩላቸው የካሪታስ ኢንዶኔዥያን ጉልህ የሆነ የበጎ አድራጎት አስተዋፅዖዎችን በማንሳት “ለጋሾቻችን የካሪታስ ኢንዶኔዥያ መሰረታዊ መንፈስን በማንፀባረቅ፣ ለሚከሰቱ አደጋዎች ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ግልፅነትን እና ተጠያቂነትን ለማሻሻል ብዙ የካቶሊክ ባለሙያዎች ከካሪታስ ኢንዶኔዥያ ጋር አብረው እንደሚሰሩም ተገልጿል። በዚህም አንፃር ታዋቂ የባንክ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ፍራንሲስካ ሞክ ለኤጀንሲው ተዓማኒነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው የተነገረ ሲሆን፥ እሳቸውም በዝግጅቱ ላይ በመገኘት “ሁሉም ነገር እንከን የለሽ በሆነ መንገድ መያዙን በማረጋገጥ የኦዲት ፕሮቶኮሎችን በጥብቅ እንከተላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢንዶኔዥያ ባንክ የቀድሞ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሃይ ሱስማንቶ የድርጅቱን እውቅና ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ በመግለጽ “ይህ ወቅት ለካሪታስ ኢንዶኔዥያ እራሱን እንደ አንድ የቤተክርስትያን እጅግ አስፈላጊ የሰብአዊ ክንፍ ለማስተዋወቅ አመቺ ጊዜ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሪና ባምባንግ በበኩላቸው የተልዕኳቸውን የተባባሪነት ተፈጥሮ በማጉላት “የርህራሄ ተልዕኳችንን ተግባራዊ ለማድረግ በጉባኤያችን ንቁ ተሳትፎ ላይ እንተማመናለን” ሲሉ ገልጸዋል።
የካሪታስ ኢንዶኔዥያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አባ ፍሬዲ ታሩክ ኤጀንሲው በ162 አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ አካል መሆኑን አብራርተው “የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆናችን መጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመፍታት ቁርጠኞች ነን” ብለዋል።