የሰኔ 09/2016 ዓ.ም የዕርገት በዓል የመጽሀፍ ቅዱስ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. የሐዋ. 1፡1-11
2. መዝሙር 46
3. ፊልጵስዮስ 4፡1-11
4. ማርቆስ 16፡15-20
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
እንዲህም አላቸው፤“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።” ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር። (ማርቆስ 16፡15-20)
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳ ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ሰማይ ያረገበት የዕርገት በዓል ይከበራል። ይህ በዓል ሁለት ዋና ዋና መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን አቅፎ ይዙዋል። በአንድ በኩል ይህ ክበረ በዓል ዓይናችን ኢየሱስ በእግዚአብሄር ቀኝ በክብር ወደ ተቀመጠበት ወደ ሰማይ እንዲያመራ ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እንደ ተጀመረ ያስታውሰናል። ይህም የሆነበት ምክንያት ከሙትና የተነሳው እና ወደ ሰማይ ያረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም እንዲያበስሩ ስለላካቸው ነው። ከእዚህ ከዕርገት በዓል በኃላ እይታችንን ወደ ሰማይ በማድረግ ከእዚያን በመቀጠል ደግሞ ወደ ምድር በመመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአደራ የሰጠንን ተልዕኮ መተግበር ይገባናል። ይሄ እኛ ዛሬ የሰማነው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ሐዋርያቱ እንዲያከናውኑት በአደራ የሰጣቸው ተልእኮ ነው። ይህ ድንበር የለሽ ተልዕኮ ነው! ማለትም ከሰው አቅም በላይ የሆነ ወሰን የለሽ ተልዕኮ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ በእርግጥ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልን ለሁሉም ፍጥረታት ስበኩ” (ማርቆስ 16፡15) ይለናል። በእርግጥም ኢየሱስ በጣም ጥቂት ለሆኑት ተራ ሰዎች እና ምንም ዓይነት ስነ-አእምሮአዊ እውቀት ለሌላቸው ሰዎች ይህንን ተልዕኮ በአደራ መስጠቱ ድፍረት የተሞላው ነገር ይመስላል! ወይም ደግሞ ይህ የመነመነ ቡድን በዓለም ታላላቅ ኃይሎች ዘንድ የማይረባ ነገር ተደርጎ የሚቆጠረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅርና የምሕረት መልእክት ወደ ሁሉም አቅጣጫው ለማድረስ ይላካል። ነገር ግን ይህ እግዚአብሔር ለሐዋርያቱ የሰጠው ተልዕኮ ተግባራዊ የሚሆነው እግዚአብሔር ራሱ ለሐዋርያቱ በሚሰጠው ኃይል ብቻ ነው። ይህም ማለት ይህ ተልዕኮ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ እንደማይለየው ኢየሱስ ራሱ ለሐዋርያቱ አረጋግጦላቸዋል።
እንዲሁም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎዋቸው ነበር። ስለዚህ ይህ ተልዕኮ እውን የሆነው በእዚሁ መልኩ ነው፣ ሐዋርያት ይህንን ተልዕኮ አስጀምረውታል፥ ከእዚያም የእነርሱ ተተኪዎች ይህንን ተልዕኮ እያስቀጠሉት ይገኛሉ። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በአደራ የሰጠው ተልዕኮ በዘመናት ውስጥ ቀጥሎ ይገኛል፣ ዛሬም ይቀጥላል፣ ይህ ተልዕኮ የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል። በእርግጥ እያንዳንዳችን ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት በተቀበልነው የመንፈስ ቅድስ ስጦታ አማካይነት ቅዱስ ወንጌል የማብስር ተልዕኮዋችንን እያንዳንዳችን መወጣት ይኖርብናል። ለእኛ ኃይል የሚሰጠን እና የወንጌል ሰባኪዎች እንድንሆን የሚያበረታታን ምስጢረ ጥምቀት በተቀበልንበት ወቅት የተሰጠን መንፈስ ነው። የጌታ ወደ ሰማይ ማዕረግ ኢየሱስ በአዲስ መልክ በእኛ መካከል እንደ ሚገኝ በር የሚከፍት አጋጣሚ ሲሆን እርሱን ለማገልገል እና እርሱን ለመመስከር ዓይንና ልብ እንዲኖረን ይጠይቃል። የጌታ ዕርገት ተካፋይ የሆንን ሰዎች እንድንሆን ይጠይቀናል፣ ይህም ማለት በዘመናችን ውስጥ ኢየሱስን በመፈለግ እና የኢየሱስን የደህንነት ቃል እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ማብሰር ማለት ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ ክርስቶስን በወንድሞቻችን ውስጥ በተለይም በድሆች ውስጥ፣ በድሮ እና በአዲሱ ስርዓቶች የተነሳ በተፈጠረው ድህነት በሚሠቃዩ ሰዎች ውስጥ ኢየሱስን እናገኛለን። ከሙትና የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመርያዎቹን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተው እንደ ላካቸው ሁሉ ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ ኃይል ተሞልተን፣ ተጨባጭ በሆነ ምልክት ታግዘን በተስፋ ምልክት ተሞልተን ተልዕኮውን እንድናስቀጥል ሁላችንንም ይልከናል። ምክንያቱም ኢየሱስ ተስፋን ስለሰጠ፣ ወደ ሰማይ ሄዶ የሰማይን ደጃፎች ስለከፈተልን እና እኛም በእዚያ እንደ ምንገኝ ተስፋን ስለሰጠን ነው። የመጀመርያዎቹን ሐዋርያት እምነት ያነሳሳች፣ በስረዓተ ቃዳሴ ወቅት እንደ ምንለው “ለባችንን ወደ ሰማይ ከፍ ማድረግ” እንችል ዘንድ እንድትረዳን ከሙታን የተነሳው እና ወደ ሰማይ ያረገው እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንማጸናት ይገባል። በተመሳሳይ መልኩም እግሮቻችንን በምድር ላይ በማድረግ በታላቅ ብርታት ተጨባጭ በሆነ መልኩ በሕይወታችን ዘመን እና በታሪክ ውስጥ የቅዱስ ወንጌል ቃል ለመዝራት እንድንችል እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን። አሜን
የእዚህ አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን