ፈልግ

ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ፣ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል እና  ብጹዕ ካርዲናል ልሣኑ ክርስቶስ ማቴዎስ (ከግራ ወደ ቀኝ) ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ፣ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል እና ብጹዕ ካርዲናል ልሣኑ ክርስቶስ ማቴዎስ (ከግራ ወደ ቀኝ) 

አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በምታበረክተው የወንጌል ምስክርነት ላይ ማብራሪያ ሰጡ

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ ጠቅላላ የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮን በማስመልከት ለቅድስት መንበር የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በኢትዮጵያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስም ለአባላቱ ባሰሙት ንግግር፥ ወንጌልን ለክርስቲያኖች በተለይም ክርስቶስን ገና ላላወቁት ሕዝቦች መመስከር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣት አደራ በመሆኑ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ማወጅ መቀጠሏን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል ምስክርነት ታማኝ በመሆን በማንኛውም ጊዜ ለአገልግሎት መቆሟን ብጹዕነታቸው ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ከሌሎች የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጋር በመሆን “ከፍተኛ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ባጋጠማት የአፍሪካ አኅጉር ውስጥ ክርስቲያኖች እንዴት የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክሮች ሊሆኑ ይችላሉ?” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ አስታውሰዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በብሔረሰቦች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች በርካቶችን ለሞት፣ ለስደት፣ ለመፈናቀል፥ ለአስከፊ ድህነት እና ሥራ አጥነት እንደዳረጋቸው የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሉቃስ፥ ሃይማኖታዊ ጥላቻ ለስልጣን ጥማት ኃይል በሆነበት እና ወደ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በከተተበት ሁኔታ ላይ የወንጌል ምስክርነት ምን ሊመስል ይችላል?” የሚለው ጥያቄ በአገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን
ከአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል አንዷ የሆነች ኢትዮጵያ በምዕራብ ከሱዳን፣ በደቡብ ከኬንያ፣ በምሥራቅ ከሶማሊያ እና ጅቡቲ፣ በሰሜን ከኤርትራ ጋር እንደምትዋሰን ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ገልጸው፥ “በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የምዕራብ አውሮፓ አገራት አፍሪካን በቅኝ ለመግዛት ሲፋለሙ ኢትዮጵያም የጣሊያንን ሙከራ በማክሸፍ ሉዓላዊነቷን በዘላቂነት ያስከበረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት!” በማለት አስረድተዋል።

ከ114 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያላት ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች አገር እንደሆነች የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ሉቃስ፥ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አገር እንደሆነች እና በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ገልጸው፥ ድህነትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ጦርነትን፣ ስደትን፣ መፈናቀልን፣ በአጠቃላይ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለማሸንፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር እንደሆነችም አስረድተዋል። ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ የተመሠረተ እና በአብዛኛው በአየር ንብረት ለውጥ የተጠቃች በመሆኗ ብዙዎች ለረሃብ የተጋለጡባት፣ ዜጎቿ በጦርነት እና በእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ኢትዮጵያ ውስጥ በይፋ የጀመረችው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንደ ነበር ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ሉቃስ፥ እምነቱን በቀዳሚነት ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት የቅዱስ ቪንሴን ማኅበር ገዳማውያን እና ቀጥሎም ፍራንችስካዊ ሚሲዮናውያን እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአሥራ ሦስት ሀገረ ስብከቶች ተዋቅራ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንደምትመራ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ገልጸው፥ በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያና ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የሚተዳደሩት የአዲስ አበባ፣ የአዲግራት፣ የእምደብር እና የባሕር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከቶች እንደሆኑ፥ የሐረር፣ የነቀምት፣ የሶዶ፣ የአዋሳ፣ የመቂ፣ የጂማ-ቦንጋ፣ የጋምቤላ፣ የሆሣዕና ሀገረ ስብክቶች እና የሮቤ ሐዋርያዊ ክልል በቅድስት መንበር የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደሚተዳደሩ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ አንድ ከመቶ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ሌሎች አጋር አገራት በምታገኘው ድጋፍ ምንም ዓይነት አድሎ ሳታደርግ በየዓመቱ ከ8-10 ሚሊዮን ሊሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን በማዳረስ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ አስቸጋሪ የሴቶች የኑሮ ሁኔታን በመለወጥ፣ ለነዋሪዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን በማቅረብ፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱት ሕዝቦች ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት፣ ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት ማለትም የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ማኅበር፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር እና የተልዕኮ ማኅበር ኅብረት በጋራ ላደረጉት ድጋፍ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስም ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።

እነዚህ ድጋፎች የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን በስፋት እንድታከናውን እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ እና በቁሳዊ አቅም እራሷን እስክትችል ድረስ ማኅበራቱ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተስፋ በማድረግ፥ የኢትዮጵያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሚደረግለት ድጋፍ በመታገዝ የተጣለበትን የወንጌል ተልዕኮ አደራን እውን ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

01 July 2024, 17:01