ብጹእ አቡነ ጆን ዊልሰን ብጹእ አቡነ ጆን ዊልሰን 

የብሪታኒያ ሊቀ ጳጳስ አፍሪካውያን ሚስዮናውያን ለአውሮፓ ቤተክርስቲያን ብዙ አስተዋጽዖ አበርክተዋል አሉ

በርካታ አፍሪካውያን ሚስዮናውያንን በሀገረ ስብከታቸው ተቀብለው ያስተናገዱት የሳውዝዋርክ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጆን ዊልሰን በቅርቡ በናይጄሪያ አቡጃ ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ ብጹአን ጳጳሳቱ በእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚጫወቱትን ጠቃሚ ሚና አጉልተዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ቀደም ባሉት ጊዜያት ወንጌልን ለማወጅ እና ለማስፋፋት ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ወደ አፍሪካ አህጉር ሚሲዮናውያን ይላኩ ነበር። ነገር ግን ይላሉ ብጹእ አቡነ ዊልሰን “አሁን ላይ ነገሮች ተለዋውጠዋል ወይም ቢያንስ አዳዲስ አካሄዶች ተጀምረዋል” ብለዋል።

በለንደን የሳውዝዋርክ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ታሪካዊው የእምነት ልምምዶች የቀነሰባቸው የቤተክርስቲያኑ ክፍሎች ከአፍሪካ የመጡትን ጨምሮ ከተለያዩ አህጉራት በመጡ ሚስዮናውያን አዲስ ሕይወት እያገኙ ነው” ብለዋል።

እ.አ.አ በ1969 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ወደ ዩጋንዳ በሄዱበት ወቅት ከባሕር ማዶ የመጡ ሚስዮናውያን ለአፍሪካ ቤተክርስቲያን ላበረከቱት ታላቅ የስብከተ ወንጌል ሥራ እውቅና ሰጥተው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በወቅቱ እንደተናገሩት ይሄንን መሠረት በመንከባከብ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን “የራሳቸውን ሚስዮናውያን እንዲያፈሩ” መክረው ነበር።

በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት አፍሪካውያን ካቶሊኮች በአገራቸውም ሆነ በሌላ አህጉራት በሚስዮናዊነት ሥራ ላይ በሰፊው ተሰማርተው ይገኛሉ። ይሄንን አስመልክተው ብጹእ አቡነ ዊልሰን እንዳሉት “ይህ ለውጥ በአፍሪካ ውስጥ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እድገትና ብስለት የሚያንፀባርቅ ነው” ካሉ በኋላ “ሁላችንም፣ እንደ ተልእኮ ተቀባዮች፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የማካፈል ሀላፊነት እንዳለብን እንገነዘባለን። ይህ ለአንዳንዶቻችን ወደ ሌሎች ሀገራት እና ህዝቦች የመሄድ ጥሪን መገንዘብን ይጨምራል፥ በዚህም መሰረት ለዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ቀጣይ ተልእኮ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል” ብለዋል።

በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ከአፍሪካ የመጡ ሚስዮናውያን ጠቃሚ ሚና
የእንግሊዙ ሊቀ ጳጳስ አፍሪካውያን ሚስዮናውያን በአውሮፓ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፥ “የደመቀ እና ደስተኛ የካቶሊክ እምነትን እንዲሁም የተለያዩ ባህሎች ሙልአትን ያመጣሉ” ብለዋል። ብጹእነታቸው በማከልም “ከዚህም ባለፈ እንደ ምዕመናን፣ ገዳማዊያት፣ እንዲሁም ካህናት ሆነው እዚህ መገኘታቸው የካቶሊክ እምነትን ዓለም አቀፋዊነትን እንድናስታውስ በማድረግ በርካታ የአውሮፓ ደብሮችን አበረታተዋል” ብለዋል።

ሚስዮናውያኑ ለስብከተ ወንጌል፣ ለሃዋሪያዊ ሥራ እና ማህበረሰብ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፣ በተጨማሪም የህይወት ምስክርነታቸው በተለያዩ አስተዳደጎች እና ባህሎች መሃል አንድነትን በማጎልበት የአካባቢውን ካቶሊኮች ለማነሳሳት ይረዳል።

በ 2013 ዓ.ም. ብጹእ አቡነ ዊልሰን በሃገረ ስብከታቸው ውስጥ የዘር እና የባህል መካተትን የሚያበረታታ ኮሚሽን አቋቁመዋል። ይህ ኮሚሽን በተለያዩ ዜግነት እና ባህሎች ባላቸው ህዝቦች መካከል መግባባት እና መከባበር ለመፍጠር ብሎም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የጋራ እምነት ግንዛቤ እንዲኖር በትጋት ይሰራል። ኮሚሽኑ በሁሉም መልኩ ዘረኝነትን ለመዋጋት የአጥቢያ ቤተክርስትያን ቁርጠኝነትን ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ብጹእ አቡነ ዊልሰን ከናይጄሪያ ለመጡ ካቶሊካዊያኖች ወይም በሳውዝዋርክ ውስጥ ለሚገኙ ናይጄራዊያን ሚሲዮናዊያን በቅርቡ ባስተላለፉት ሃዋሪያዊ መልእክት “ከአፍሪካ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ካቶሊኮች በማህበረሰባችን ውስጥ ውብ እና የበለጸገ የተለያየ የእግዚአብሔር ፍጥረትን ወደ ሕይወት በማምጣት ቤተ ክርስቲያናችንን አበልጽገዋል” ካሉ በኋላ “ይህ በዓለም ዙሪያ ላሉት ሃገረ ስብከቶች ላይ የሚታይ እውነት ነው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት ቤተሰብ እንደመሆኗ፣ እኛ ባለንበት ሁሉ ሥፍራ ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ እና የተደበቁ ቢሆኑም የእምነት ማህበረሰብ አለ” ብለዋል።

“በሀገረ ስብከታችን ውስጥ በሚገኙ ከሁሉም ብሔረሰቦች በመጡ ሰዎች አማካኝነት ትልቋን ሁለንተናዊ ቤተ ክርስቲያናችንን አጉልቶ የሚያሳይ አሰራር ለመመስከር በደቡብ ለንደን ከሚገኙ ውብ ደብሮች ውስጥ አንዱን ብቻ መጎብኘት በቂ ነው” ካሉ በኋላ “እያንዳንዱ ሰው ልዩ ስጦታዎችን፣ አመለካከቶችን እና ልምዶችን ያመጣል። የእኛ የሳውዝዋርክ አጥቢያዎች በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ያለውን አንድነት እና ልዩነት የሚያንፀባርቁ ውብ ማሳያዎች ናቸው” በማለትም አክለዋል።

ቤተክርስቲያን እንግዳ የሚስተናገድበት ቦታ መሆን አለባት

ብጹእ አቡነ ዊልሰን ሃገረ ስብከታቸው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያገኝ ያስቻሉትን ጥቂት ጠቃሚ አሰራሮችን በማንሳት “ናይጄሪያ ውስጥ በነበረኝ ጊዜ የተደረገልኝ ጥልቅ የአቀባበል ስሜት በጣም ስለገረመኝ፣ እዚህ ተመልሼ በሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት፣ በአንዳንድ የደብሩ መርሃ-ግብሮች ወይም በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥም ቢሆን ሁሉም ሰው አዲስ ለመጡ ሰዎች ሞቅ ያለ ሰላምታ እንዲሰጥ እጠይቃለሁ” ብለዋል። 

የባህል አገላለጾችን፣ ቋንቋዎችን እና ወጎችን በማክበር ሁሉም ሰው ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠው እና እንዲሰማው ለማድረግ ማካተት መሰረታዊ ነገር መሆኑንም ጭምር ጠቅሰዋል። በእያንዳንዱ ደብር ውስጥ “ዓለም አቀፍ የሆኑ ሥርዓተ ቅዳሴዎች” ይደረጋሉ፥ ከዚህም ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና ልዩነቶችን ለማስወገድ፣ እንዲሁም ጤናማ የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ለመገንባት የሚረዱ የተለያዩ የምግብ፣ የመዝሙር እና የጥበብ ሥራ መርሃግብሮች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ዊልሰን ሃይማኖታዊ ምስረታ ምእመናንን ስለባህል ብዝሃነት እና ስለሚያመጣው ብልጽግና በማስተማር ረገድ ቁልፍ ሚና እንደነበረው በመግለጽ፥ ይህም ውይይትና መግባባትን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

ብጹእነታቸው በካሪታስ ሳውዝዋርክ አማካይነት ሃገረስብከቱ ከቤተክርስቲያን ባሻገር ለሚገኙ ድሆችን፣ የተገለሉ ሰዎችን፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞችን ለማገልገል በርካታ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በመቀጠልም እንደ ሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ የስደተኞች ቅዳሴ፣ ከሌሎች ሃገረ ስብከቶች ምዕመናን፣ ሃይማኖታዊ ማህበራት እና ድርጅቶች ጋር በመሆን እና በካሪታስ ሳውዝዋርክ በመታገዝ እንደ ትምህርት፣ ጤና አጠባበቅ እና ማህበራዊ ፍትህ ባሉ የጋራ ውጥኖች ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። 

የሚስዮናዊነት መንፈስ እና ተጽእኖው
“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ 'ሚስዮናውያን ደቀ መዛሙርት' እንድንሆን አጥብቀው ያሳስቡናል” ያሉት ብጹእ አቡነ ዊልሰን፥ በሃገረ ስብከቱ፣ በአብያተ ክርስቲያናት እና በትምህርት ቤቶች፣ በወንጌል ስርጭት ተቋማት እና በካሪታስ ሳውዝዋርክ፣ እንዲሁም በሁሉም የክርስትና ሕይወት ዘርፎች የሚስዮናውያን አስተሳሰብን ለማዳበር እንጥራለን ብለዋል።

የሳውዝዋርክ ሃገረ ስብከት በየደብሮች፣ ቤተ ጸሎቶች እና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ከሌላ አህጉራት የመጡ ካህናት እና ገዳማዊያት ያሉት ሲሆን፥ ይህም በናይጄሪያ የሚገኙትን የቅዱስ ጳውሎስ የሚሲዮናውያን ማኅበር ካህናትን ጨምሮ ከሌሎች የሚሲዮናውያን ጉባኤዎች የተውጣጡ እና በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ካህናትን ይጨምራል ተብሏል።

ብጹእ አቡነ ዊልሰን በአውሮፓ ውስጥ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በሌሎች የዓለም ክፍሎች በተለይም ወጣት እና ንቁ በሆኑ የአፍሪካ ክፍሎች ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ፍላጎቶችን ማክበር አለባቸው ብለዋል።

“የጎደለውን ለማሟላት ከሌሎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በቀላሉ 'መውሰድ' አንችልም” ያሉት ብጹእነታቸው፥ “የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በሚያከብር ተልዕኮ ውስጥ ከየአካባቢያቸው ጳጳሳት እና አለቆቻቸው ጋር ተገቢውን ምክክር ካደረጉ በኋላ ሚስዮናውያንን ብቻ ከባህር ማዶ በመቀበል እና በመላክ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን በጋራ ለማበልጸግ በሚያገለግል ተልዕኮ ውስጥ ትክክለኛ እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር ሊኖር ይገባል” በማለት አብራርተዋል።

ለመጪው ጊዜ ያለው ተስፋ
ሊቀ ጳጳሱ በእምነት፣ በአንድነት እና በአገልግሎት የምታድግ ቤተክርስቲያን ለማየት ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ “እኛ ሁሉንም የምንቀበል እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና በቃልና በተግባር ለማወጅ ቀዳሚ ተልእኳችን ታማኝ ሆነን የምንቀጥል የሚስዮናውያን ቤተክርስቲያን ነን፣ ከዚህም የበለጠ ለመሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ዊልሰን ቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልሉ፥ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ኤጀንሲዎች አማካይነት ከአፍሪካ እና ከሌሎች አገሮች በመጡ ሰዎች መካከል ቀጣይነት ያለው እና ጥልቅ የሆነ ትስስር በመፍጠር፣ ተገቢውን ግብአትና ሃዋሪያዊ ሥራን ባካተተ መልኩ በየአካባቢያቸው ባሉ ማህበረሰቦች መካከል ይበልጥ አካታች የሆነ ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
 

31 July 2024, 19:11