ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሚሰቃዩት ሕዝቦች ጎን መሆኗን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው
በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቫቲካን የሚደረገውን የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው መሆን አለባት ብለዋል።
“ወደ ቫቲካን የተደረገው ጉዞ የጥንታዊ መንፈሳዊ ጉዞ አካል ነው!”
ከ500 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ወደ ግብጽ እስክንድርያ መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ በቅዱስ ማርቆስ መካነ መቃብር ዙሪያ ተሰባስበው እንደሚጸልዩ፣ ወደ ኢየሩሳሌምም ተጉዘው በጎልጎታ ላይ ጸሎት እንደሚያደርሱ ከዚያም ተነስተው በመርከብ ወደ ሮም በመጓዝ የቅዱሳን ጴጥሮስን እና ጳውሎስ እንዲሁም የሰማዕታትን መቃብር ከጎበኙ በኋላ ዛሬ በቫቲካን ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ በታነጸበት ሥፍራ ያርፉ እንደ ነበር በማስታወስ “እኛም የጥንት መንፈሳዊ ጉዞ ታሪክ ለመቀጠል ወደ ቫቲካን መጥተናል” ብለዋል።
የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት በሮም በሚገኙ አራቱ ዋና ዋና ባዚሊካዎች፥ በታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቅዱስ ጳውሎስ እና በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ባዚሊካ ውስጥ ጸሎት ማድረሳቸው ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ገልጸው፥ በቫቲካን ውስጥ የሚገኙትን የቅድስት መንበር ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን መጎብኘታቸውን እና ዓርብ ሰኔ 21/2016 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በትሕትና እንደተቀበሏቸው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በማስረዳት አገሪቱ በጦርነት እና በጭንቅ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ቅዱስነታቸው ላደረጉት የጸሎት እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ማመስገናቸውን እና ኢትዮጵያን ዘወትር በጸሎት እንዲያስታውሷት መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያን ሁኔታ በማስመልከት እንደገለጹት፥ 120 ሚሊዮን ከሚሆን ሕዝቦቿ መካከል 70% የሚሆነው ወጣቱ ትውልድ እንደሆነ ተናግረው፥ በርካታ ወጣቶች የራሳቸውን እና የወላጆቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ አረብ አገራት እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደሚሰደዱ አስረድተው፥ በተለይ የሱዳንን እና የሊቢያ በረሃን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሚያደርጉት ሙከራ ከፍተኛ እንግልት እንደሚደርስባቸው አስታውሰዋል። “በ 19ኛው ክፍለ ዘመን ለስደት የሚዳረጉ በርካታ አውሮፓውያንን ተቀብለው ድጋፍ የሚያደርጉ አንዳንድ አካባቢዎች ቢኖሩም፥ ነገር ግን ዛሬ እነዚህ ቦታዎች የሉም” ብለዋል።
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት አደራን በተቀበሉ ማግስት፥ የደቡብ ጣሊያን የወደብ ከተማ የሆነችውን ላምፔዱዛን ጎብኝተው እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ አስታውሰው፥ በዚህ ጉብኝታቸው በባሕር ላይ ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞችን በማስታወስ አበባን ባሕር ውስጥ መወርወራቸውን አስታውሰዋል። ስደተኞችን መቀበል ለአውሮፓ አገራት ጠቃሚ እንደሆነ መናገራቸውን ብጹዕነታቸው አስታውሰው፥ ከአፍሪካ፣ ከሶርያ ወይም ከሌሎች አገራት የሚሰደዱ ሰዎችን መርዳት እና በተለይም በድህነት የሚሰቃዩ ሰዎችን ቀርቦ ማገዝ እንደሚገባ አደራ ማለታቸው ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በጦርነት ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመፍረሳቸው ምክንያት ሳይማሩ ከቀሩት ሕፃናት ጋር፣ የጤና ተቋማት በመውደማቸው ምክንያት ሕክምናን ማግኘት ከማይችሉ እናቶች እና ባጠቃላይ ችግር ውስጥ ከወደቁት አረጋውያን ጎን መቆሟን ለቅዱስነታቸው ከገለጹላቸው በኋላ፥ አንድ ጳጳስ በሕዝቡ መካከል በመገኘት አባትነቱን እና ወንድማዊነቱን መግለጽ አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቲያን እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፥ በዚህች ታላቅ ሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው የመሆን ሃላፊነት እንዳለባት ተናግረው፥ “ተግዳሮቶቻችን ድህነት እና ግጭቶች ናቸው” ብለው፥ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከጎናቸው በመሆን ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ተቋሞቿ አማካይነት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በምታበረክተው ማኅበራዊ አገልግሎቶቿ ማለትም በትምህርት፣ በጤና እንክብካቤ እና በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በሁለተኛ ደረጃ እንደምትጠቀስ በመግለጽ፥ “ጌታችን ኢየሱስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነገረን፥ “የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው ለመሆን ተጠርተናል” ብለዋል።
በርካታ ሰዎችን ለስቃይ የዳረገው የትግራይ ግጭት በክልሉ እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት እንደ ነበር አስታውሰው፥ በፕሪቶሪያው ድርድር ከሁለት ዓመት በኋላ ሰላም በመፈጠሩ እግዚአብሔርን አመስግነዋል። ሌላው በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፌደራል መንግሥት ጋር ለአራት ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ እንደቆየ እና በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ ደሴት ዛንዚባር የሰላም ድርድር እንደተጀመረ እና ገና ወደ ስምምነት አለመደረሱን ገልጸዋል። ሦስተኛው የግጭት ግንባር ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለ ግጭት እንደሆነ ብጹዕነታቸው ተናግረው፥ በድርድር ወደ መፍትሄ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሁሉ ለየትኛውም አካል ሳትወግን ነገር ግን ከሚሰቃዩ ሕዝቦች ሁሉ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከጎናቸው እንደምትገኝ አስረድተዋል።
ፍላጎታችን ለተቸገሩት ዕርዳታን ማቅረብ እና ከጦርነት በኋላ እርቅ ተደርጎ ሰላም እንዲሆን ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ወቅት የጥቃት ሰለባ የሆኑት ልጃገረዶች እና እናቶች፣ ቤተሰቦቻቸው በፊታቸው ሲገደሉባቸው ተመልክተው የደነገጡት በሙሉ ከድንጋጤአቸው እንዲፈወሱ ማገዝ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህን ማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለች ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን እና አብረውን ከሚሠሩ ከመላው ዓለም ከመጡ ሚስዮናውያን ጋር በመተባበር እንደሆነ ብጹዕነታቸው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።