በኢሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የሕፃናት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከጥላቻ በላይ መሆኑን ገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት ምክረ ሃሳብ ይፋ የሆነው፥ በድሩዝ ከተማ በ12 ሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያን በማስመልከት በኢየሩሳሌም የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤን በመወከል የላቲን ፓትርያሪክ ጽሕፈት ቤት ባወጣው የሐዘን መግለጫ መልዕክት በኩል
የመጫወቻ ሥፍራው ጥቃትን በተመለከተ
እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. በኢራን የሚደገፈው እና በሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው ሂዝቦላህ ቡድን ሃላፊነቱን አልወሰደም ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ወቀሳዋን አቅርባለች። በእስራኤል በተያዘው የጎላን ከፍታ በተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ቀደም ሲል በጋዛ ከደረሰው አስከፊ የሰብዓዊ ድንገተኛ አደጋ በዘለለ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሰፊ ጦርነት ስጋትን ፈጥሯል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የተፈጸመውን ጥቃትን በማውገዝ በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ሐዘኑን ገልጾ የሰላም እና አብሮ የመኖር ጥሪውን አቅርቧል።
“ለመናገር የሚከብድ የጥቃት ድርጊት ነው!”
በተስፋ እና በህልም የተሞላው የእነዚህ ንጹሐን ሕይወት በቃላት ሊገለጽ በማይችል የዓመፅ ድርጊት መወሰዱን የተገነዘበው የላቲን ፓትርያሪክ ጽሕፈት ቤት መልዕክት፥ “እንዲህ ያለውን አስጸያፊ የዓመፅ ድርጊት በመጋፈጥ የሚሰማንን ሐዘን እና ቁጣ ሙሉ በሙሉ መግለጽ አይቻልም” ሲል ገልጿል።
የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው የድሩዝ ማኅበረሰብ ጸሎት በማቅረብ እና አጋርነቱን በመግለጽ “ይህ ሊነገር የማይችል አደጋ በሁላችንም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብሎ፥ “የዓመፅ አዙሪት ማብቃት አለበት” በማለት በዚህ የሐዘን ወቅት ሰላምን በመከተል እና ዓመፅን በመቃወም የጠፉትን በክብር እናስታውሳቸዋለን” ብሏል።
ለጋራ መከባበር የቀረበ ጥሪ
“በሁሉም ወገኖች ዘንድ መግባባት እና መከባበርን እንዲኖር እናሳስባለን” ያሉት የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት አባላቱ፥ “ጥቃት፣ ጥላቻ እና ንቀት ይብቃን! ሁሉም ወገኖች የግጭት እና የትጥቅ መንገድን ትተው የመግባባት እና የመከባበር መንገዶችን እንዲከተሉ አጥብቀን እንጠይቃለን” ብለዋል።
“የሕፃናት የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና የማኅበረሰባችን ደህንነት ከጥላቻ ወጥቶ የርህራሄ እና አብሮ የመኖር መርሆዎችን በመቀበል ችሎታችን ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት መልዕክት አስጠንቅቋል።
ውድ ሕይወትን ከአደጋ ለመጠበቅ አስቸኳይ ሰላም ያስፈልጋል
ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በጻፈው መልዕክት “ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉ” ያለውን የጠቀሰው የጽሕፈት ቤቱ መልዕክት፥ በጦርነት እና በመሣሪያ ኃይል የሚወገድ ምንም ነገር የለም ሲል ገልጿል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት፥ እግዚአብሔር ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን እና ብርታትን እንዲሰጥ በመማጸን፥ ትዝታዎቻቸው የሕይወትን ውድነት እና አስቸኳይ የሰላም አስፈላጊነት እንዲያስታውስ በመጸለይ መልዕክቱን ደምድሟል።