ፈልግ

ኢየሱስ ንጉሣችን ነው ኢየሱስ ንጉሣችን ነው 

ኢየሱስ ንጉሣችን ነው

ኢየሱስ ንጉሣችን ነው አይሁዳውያን ኢየሱስን በጲላጦስ ፊት ካቆሙት በኋላ «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ” ይላል እያሉ ከሰሱት። ጲላጦስም «የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” የሚል ጥያቄ ለኢየሱስ አቀረበለት። ኢየሱስም መልሶ «አንተ ይህንን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። ቀጥሎም ኢየሱስ «መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎች ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም´ (ዩሐ. 18፣36) አለው። ጲላጦስም «ታዲያ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም «እኔን ንጉሥ እንደ ሆንኩ አንተ ትላለህ” አለው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ሳይወለድ ከስንት ዘመናት በፊት ነቢዩ ዳዊት «አንተ ንጉሤና አምላኬ ነህ” (መዝ. 44፣4) እያለ ይተነበይለትና ይለምነው ነበር። ካህኑ ዘካሪያስ ደግሞ «ለጽዮን ልጅ ኢየሩሳሌም ንጉሥሽ እየመጣ ነው በሏት´ (ዘካ. 9፡9)) እያለ ይናገር ነበር። ቅዱስ ገብርኤል እግዚእተነ ማርያምን ምስጢረ ሥጋዌን ሲያበስራት ሳለ «ጌታ እግዚአብሔር አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤት ላይም ያነግሠዋል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም” (ሉቃ. 1፣34)።

አይሁዳውያን አንድ ትልቅ ተአምር ስላዩ የእስራኤል ንጉሥ ብለው ይጠሩት ነበር። ነጥቀው ንጉሥ እንዲያደርጉት ይፈለጉ ነበር (ዮሐ. 6፣15)። በሕማማቱ ጊዜ «የአይሁድ ንጉሥ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት እያላገጡ ይሰግዱለት ነበር። ከተሰቀለ በኋላ ደግሞ «የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ ከመስቀል ላይ ውረድ በአንተ እናምናለን” (ሉቃ. 23፣37) በማለት ያዋርዱት ነበር። የኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ብቻ አይደለም የዓለም ሕዝብ ሁሉ ንጉሥ ነው። የሁሉም ሕዝብ ንጉሥ እና ፈጣሪ ሲሆን በመንግሥቱ እንደ ሌሎች የዓለም ነገሥታት ለጥቂት ዓመታት አይደለም። የእርሱ መንግሥት ለዘለዓለም የሚኖር መጨረሻ የሌለው መንግሥት ነው (ሉቃ. 1፣33)። «ከባሕር እስከ ባሕር ሊገዛ፣ የምድር ነገሥታት ሁሉ ሊሰግዱለት፣ ሕዝቦችም ሁሉ እርሱን ሊያገለግሉ ነው” (መዝ. 71) ይላል ዳዊት። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ «የነገሥታት ንጉሥ” በማለት ይጠራዋል (1ኛ. ጢሞ. 6፣15)።

ኢየሱስ ከፍጥረታት ሁሉ አስቀድሞ ንጉሥ ነው። ከኢምንትነት ወደ ሕይወት ወይም ወደ ዓለም አመጣን። እኛም የእርሱ ንብረትና ገንዘብ ነን። በሕይወት የሚያኖረን እርሱ ነው። በኋላ ደግሞ በማዳን በደኀንነት ዘመን እኛን ስለሚገዛን ዘለዓለማዊ ንጉሣችን ነው። በኃጢአት ወድቀን የሰይጣን ባርያዎች ስንሆን ከሰማይ ወደ ምድር ሊያድነን መጣ፤ ደሙንም አፍስሶ ተቤዠን፣ ከአስከፊ የሰይጣን ግዛት ነፃ አውጥቶን ወደ እርሱ ዘለዓለማዊ የደስታ ግዛት መለሰን፤ የመንግሥቱ ወራሾችም አደረገን።

ኢየሱስ በእርግጥ የነፍስና የሥጋ ንጉሥ ነው። በተለይ ደግሞ የነፈሳችን ንጉሥ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ለሕዝበ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥነት ሲናገሩ «ነፍሶቻችን አንድ ታላቅ የዋህ ንጉሥ አላቸው፤ ይህ ንጉሥ ሊያድነንና ሕይወት ሊሰጠን ስለ እኛ ሞቷል። በመካከላችን እንዲኖር በእንጀራና በወይን መልክ ምስጢረ ቁርባንን ሠራልን። ይህም ቢሆንም ብዙዎች የእርሱ ተቃራኒዎች ሆነው ተነሥተዋል ወደ ሥጋቸው ፍላጐት እና ወደ ሰይጣን ባርነት ተመልሰዋል” ብለው ነበር።  

አይሁዳውያን ኢየሱስን ንጉሣቸውና መድኃኒታቸውን በሕይወት ዘመኑ ይወዱትና ያከብሩት ነበር። በተጨማሪ በሆሳዕና ቀን ደግሞ «በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን” እያሉ በታላቅ ደስታ እና ክብር የተቀበሉት ሁሉ በሕማማቱ ሳምንት ካዱት ሰደቡት ረገሙት፣ ክፉኛ አዋረዱት አሰቃይተውም በመስቀል ላይ ሰቀሉት። ጲላጦስ «ንጉሣችሁ እንዳደረገው ትፈልጋላችሁ? ወይስ በነፃ ልልቀቀው?” እያለ ሲጠይቃቸው «ስቀለው ስቀለው …. ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” አሉ። እኛስ በእንደዚህ ዓይነት ክህደትና ጭካኔ አንገኝምን? በአፋችን ኢየሱስ ንጉሣችን እያልን በሥራችን ስናዋርደው እንገኛለን። በኃጢአታችን ስናሳዝነውና እርሱን አስወግደን ሰይጣንን እና ዓለምን በልባችን አናነግሥምን?

እንደዚህ የምናደርግ ከሆነ ቶሎ ብለን እንታረም። በበደላችን ተጸጽተን በእግሩ ሥር ተደፍተን ከጠላቶቹ ተባብረን ስላሰቃየነው «ማረን” እንበለው። በተለይም ከእንግዲህ ወዲህ እንደማንክደውና እንደማንበድለው ይልቁንም እንደ ተወዳጅ ንጉሣችን አድርገን ልናገለግለው ዝግጁ እንደሆንን እናሳውቀው። ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች «እናንተ እንደ አባቶቻችሁ ክፉ ነገሥታት ጣዖትን ማገለገል የምትፈልጉ ናችሁን? ወይስ እውነተኛ ንጉሥ የሆነውን አምላካችንን?” ካላቸው በኋላ ሁሉም በአንድነት ከእርሱ በስተቀር ሌላ ንጉሥ የለንም፤ ሌላ ንጉሥም ማገልገል አንፈልግም” አሉ። እኛም እንደዚህ እንበል እናድርግም።

26 July 2024, 16:02