ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎችን በጎበኙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካናዳ ቀደምት ነዋሪዎችን በጎበኙበት ወቅት 

በካናዳ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ከቀደምት ነዋሪዎች ጋር ያላትን ኅብረት እንደምትቀጥል ገለጸች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የንስሐ ንግደት” የተሰኘ ታሪካዊ ጉብኝት በካናዳ ካደረጉበት ከሁለት ዓመታት በኋላ የካናዳ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ከአገሬው ቀደምት ተወላጆች ጋር በአብሮነት ለመጓዝ ቁርጠኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በካናዳ ታሪካዊ የተባለለት ሐዋርያዊ ጉብኝት ካደረጉበት ከሁለት ዓመታት በኋላ የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት የአገሬውን ተወላጆች ተሞክሮ እያዳመጡ በአንድነት ለመጓዝ እና መንገዱን ለመምራት ቁርጠኞች እንደሆኑ ተናግረዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ ለእግዚአብሔር ሕዝቦች በጻፉት መልዕክታቸው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአገሬው ቀደምት ማኅበረሰቦች ላይ የተፈጸመውን አስከፊ ተግባር እና ውጤቱን በማስመልከት በተናገሩት የእርቅ እና የፈውስ ጉዞ ላይ በማሰላሰላሰል አብረው መጓዝ ጀመራቸውን ገልጸዋል።

ወደ እርቅ እና ወደ ፈውስ የሚወስዱ ተነሳሽነቶች
ብጹዓን ጳጳሳቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ቤተ ክርስቲያን በካናዳ ያከናወኗቸውን አንዳንድ ተነሳሽነቶች አጉልተዋል።

የመጀመሪያው ለአገሬው ተወላጆች ቅድሚያን በመስጠት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን እንደሚያካትት፣ በዚህም መሠረት የፈውስ እና የእርቅ መርሃ ግብርን ለመደገፍ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሰላሳ ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ለማሰባሰብ ቃል መግባታቸውን ጳጳሳቱ ገልጸዋል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የተሰበሰበ ሲሆን፥ ገንዘቡ በአካባቢው ተወላጅ ማኅበረሰቦች መካከል ተከፋፍሎ ለተነሳሽነቱ እንደሚውል እና በአገር በቀል የእርቅ ፈንድ ቁጥጥር እንደሚደረግ ታውቋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ በተጨማሪም የወንጌል ተልዕኮን፣ ቅዱሳት ምስጢራትን፣ የቀብር መዝገቦች እንዲሁም ሌሎች ሠነዶችን ግልጽ እና ተደራሽነት ባለው መንገድ ለማስፈጸም ራሳቸውን ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ስላጋጠሟቸው ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶች አስመልክቶ እውነቱን በማውጣት እና በማወቅ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን አስታውሰው፥ ከእርቅ በፊት እውነት መውጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም በአገሪቱ ውስጥ ሕመምን የሚያስከትል ውርስን በተመለከተ ብዙ አስቸጋሪ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረው፥ ይህ ጥልቅ የእውነት እና የግልጽነት ፍላጎት በመጀመሪያ በአገሪቱ ቀደምት ማኅበረሰቦች እና በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ከጥቃት የተረፉ ሰዎች ዘንድ መኖሩን በመገንዘብ፥ ሀገረ ስብከቶች እና ካቶሊክ ምዕመናን በሙሉ የአከባቢው ቀደምት ማኅበረሰቦች በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕመም በሚያስከትል ታሪክ ውስጥ የገቡትን ሰዎች እንዲደግፉ ብጹዓን ጳጳሳቱ አደራ ብለዋል።

የእርቅ እና የተስፋ መንገድ
የካናዳ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካናዳ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቆራጥ እርምጃ እንድትወስድ እና ለምንከተለው አዲስ መንገድ የማይቀለበስ ቁርጠኝነት ከካናዳ ተወላጆች ጋር ለማድረግ ያቀረቡትን አቤቱታ አስታውሰዋል።

“የዕርቅ እና የተስፋ መንገድ አንድ ላይ የሚጓዙት መሆን አለበት” ያሉት ጳጳሳቱ፥ “በዚህ ጉዞ ወቅት ከጥቃቱ የተረፉትን እና የአገሬው ተወላጆችን ማዳመጥ እና መደገፍን እንቀጥላለን” ብለዋል።
 

27 July 2024, 16:00