ፈልግ

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን 

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ቤተክርስቲያን ያስተላለፈችው መልእክት

እሁድ ሐምሌ 14 እና ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከሁለት መቶ ሰዎች በላይ መሞታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ተቀብረው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ዛሬም ለአራተኛ ቀን እየተካሄደ ይገኛል።

በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ እና በአቅራቢያው እሁድ ሌሊት ማለትም ሃምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ እሁድ እና ሰኞ ማለዳ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደተከሰቱ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ካሳሁን አባይነህ ተናግረው፥ በዚህም አደጋ እስካሁን ድረስ ከ 250 ሰዎች በላይ ህይወት ማለፉን ገልጸዋል።  የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ እና ያደረሰውን አስከፊ ጉዳት ተከትሎ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአብሮነት መልዕክት ያስተላለፈች ሲሆን፥ መልዕክቱም እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጉዳዩ፡ የአብሮነት መልዕክት ስለማስተላለፍ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፥ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በመሬት መንሸራተት ምክንያት በተከሰተው አደጋ እጅግ ማዘኗን ትገልፃለች። አደጋው ክቡር በሆነው በሰው ልጅ ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያደረሰ በመሆኑ ሃዘናችን ጥልቅ ነው። በዚህ አስከፊ አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ዜጎች ለነፍሳቸው እረፍት እየጸለይን፥ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ ቤተክርስቲያናችን መፅናናትን ትመኛለች።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የልማት ሥራ ሃላፊ፣ የሶዶ ሃገረስብከት ካህናት እና የሥራ ሃላፊዎች፣ የካቶሊክ ተራዕዶ ድርጅት የሥራ ሃላፊዎች አደጋው በተከሰተበት ቦታ በመገኘት የአደጋውን አስከፊነት ተመልክተዋል። በርካቶች ልጆቻቸውን፣ እናቶቻቸውን፣ አባቶቻቸውን አጥተዋል። አደጋው አፋጣኝ የነፍስ ማዳን እና የሰብዓዊ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥም በአደጋው የተሰማኝን ሃዘን እየገለጽኩ ዞኑ ለተፈጠረው አደጋ ለሚያደርገው ተግባር ቤተክርስቲያናችን ከጎናችሁ እንደምትቆም በአክብሮት እገልፃለሁ።

መላው ካቶሊካዊያን እና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የመልሶ ማቋቋም ሂደት አቅማችሁ በሚፈቅደው ሁሉ እንድትተባበሩም ጥሪ አቀርባለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ !

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት

26 July 2024, 10:33