ፈልግ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት (ENDF) ወታደሮች ጋሸና በሚባለው አከባቢ መንገድ ላይ ሲጓዙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት (ENDF) ወታደሮች ጋሸና በሚባለው አከባቢ መንገድ ላይ ሲጓዙ   (AFP or licensors)

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ እየደረሰ ካለው ጥፋትና ውድመት መካከል ተስፋ አለ አሉ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሱ ያሉትን ግጭቶች እና ሰብዓዊ ቀውሶች ለመፍታት ሰላም፣ ትምህርት እና የሙያ ሥልጠና እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ከተማ የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተከሰቱት እና አሁንም ድረስ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ የተከሰቱትን ሰብዓዊ ቀውሶችን ለመፍታት ቤተክርስቲያኗ ሁሌም የበኩሏን ተሳትፎ እንደምታደርግ ገልጸዋል። ብጹእነታቸው በቅርቡ ከፊደስ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ግጭቶች አሉ፥ ነገር ግን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም” ብለዋል።

በርካታ ግጭቶች

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በቃለ ምልልሱ ወቅት በሀገሪቱ ስላለው ውስጣዊ ግጭት በማንሳት በህዝቡ ላይ ስላደረሰው ስቃይ ተናግረዋል። በርካቶችን ለስቃይ የዳረገው የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማብቃቱን አስታውሰው፣ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ከፍተኛ የሰብዓዊ ፍላጎቶች እንዳልተሟሉ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው ያሉት ብጹእነታቸው፣ የግጭቱ ውጤት የተፈናቀሉትንም ሆነ በጦርነቱ ውስጥ የቀሩትን እየጎዳ ይገኛል ብለዋል። በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየታዩ ሲሆን፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራል መንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ቀውሱን አባብሶታል።

በካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በኩል በተቻለ መጠን ለተጎዱት ግለሰቦች እርዳታ ለማቅረብ የተደረገውን የቤተክርስቲያኗን ጥረት አጽንኦት ሰጥተዋል በማንሳት፣ “የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተፈናቃዮች እና በጦርነት ቀጠና የሚኖሩትን ለመርዳት ትጥራለች” ብለዋል።

የስነ-ልቦና እና የመንፈሳዊ ጉዳቶች

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በጦርነቱ ምክንያት የሚደርሰውን ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ “ጉዳት” በሕዝቡ ላይ በተለይም በሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና ተገደው ጦርነት ውስጥ በገቡ ሰዎች ላይ የሚኖረውን እጅግ ሰፊና የተለያየ ተፅዕኖ በማንሳት፣ “እያንዳንዱ ጦርነት ብዙ ሰዎችን በአካል ብቻ ሳይሆን በነፍስ እና በመንፈስ ላይም ጉዳት ያደርሳል” በማለት የጦርነት አስከፊነትን ጠቁመዋል።

ቤተክርስቲያኗ በተለይ የአእምሮ ጉዳት እንክብካቤ ላይ በማተኮር በማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እገዛ ለመስጠት ማቀዷን ያነሱት ብጹእ ካርዲናሉ፥ በተለይ በግጭቶቹ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ በርካታ ህጻናትን እና እናቶቻቸውን፣ እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር ሰለባ በሆኑ ሴቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኒቱ በነዚህ ወሳኝ ዘርፎች ላይ ከመንደር ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ገዳማዊያን ባለሙያዎችን፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን እና ካቴኪስቶችን በንቃት በማሰልጠን ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

የአንድነት ኃይል

የአቢያተ ክርስቲያናትና እና የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ሚናን በማጉላት ያነሱት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ውስጥ ያላትን መሠረታዊ ሚና ጠቁመው፣ “በሰብአዊነት መስክ በጋራ በመስራት፣ ከፌደራል መንግስት እውቅና ባገኘንበት በአገር አቀፍ ደረጃ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንችላለን” ካሉ በኋላ፥ ምክር ቤቱ ሁሉንም ዋና ዋና ሃይማኖታዊ ቤተ እምነቶችን ያካተተ መሆኑን፣ ብሎም በዕርቅ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሰራ፣ የጦርነት ጉዳቶችን በማከም እና በሰብአዊ እርዳታ ሥራዎች ላይ በጋራ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

መጪው ጊዜ ተስፋ አለው

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ለኢትዮጵያ የተስፋ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ሀገሪቱ ጥንታዊ የክርስቲያን ቅርሶች መገኛ መሆኗን እና በአይሁዶች፣ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ በሰላም አብሮ የመኖር ታሪክ አፅንዖት ሰጥተው አንስተዋል። ብጹእነታቸው በሃገሪቱ ውስጥ እየተተገበረ ያለውን የብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ህዝቡ በብሄር እንዲከፋፈል ምክንያት መሆኑን አንስተው ፥ ፌደራሊዝሙ የሚጠቅም ቢሆንም ብሄርን ወይም ቋንቋን መሰረት ያደረገ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል።

ከጂኦፖለቲካዊ እይታ አንጻር የኢትዮጵያን ፋይዳ ሃገሪቷ ባላት የ120 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት አንፃር ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፥ ይህም ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። ይሄንን እውነታ ያነሱት ብጹእነታቸው “ሰባ በመቶው ህዝብ ወጣት እና አገሩን የሚወድ ቢሆንም በድህነት እና በግጭቶች ምክንያት ለስደት ተዳርገዋል” ብለዋል።

ለወጣቶች የሚያስፈልጋቸውን ስጡ

ከዚህ ጋር በተያያዘም ብጹእ ካርዲናል ለወጣቶች የሙያ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበው፣ “ወጣቶች ወደ ውጭ አገር ሄደው ጥሩ ደመወዝና ክብር እንዲኖራቸው ቢፈለግ እንኳን መጀመሪያ በአገራቸው ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ማሰልጠን አለብን” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ በመጨረሻም ምንም እንኳን ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም፥ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህም ባሻገር “አዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል” ካሉ በኋላ፥ “ኢንደስትሪያችንን ለማጠናከር ሰላም፣ ትምህርት እና ኢንቨስትመንቶች እንፈልጋለን” ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ቃለ ምልልሳቸውን አጠቃለዋል።
 

10 July 2024, 13:32