ፈልግ

በፓሪስ የተዘጋጀው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በፓሪስ የተዘጋጀው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት   (AFP or licensors)

የፈረንሳይ ጳጳሳት በክርስትና ላይ የሚሳለቁ ትዕይንቶች በመቅረባቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገለጹ

የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ማግሥት ሐምሌ 20/2016 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፥ ዘንድሮ በፓሪስ ከተማ እየተካሄዱ በሚገኙ የኦሎምፒክ ውድድሮች መካከል በክርስትና ላይ የሚሳለቅ ትዕይንት በመቅረቡ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። ጳጳሳቱ በመግለጫቸው፥ ዝግጅቱ አስደናቂ የውበት፣ የደስታ እና መልካም ትዝታን የሚያስቀር መሆኑ በመግለጽ ቢያወድሱትም፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በአንዳንድ አላስፈላጊ ትዕይንቶች ላይ ያደረባቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፈረንሳይ ሴይን ወንዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድሮች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በጀልባዎች የታጀቡ 85 የስፖርት ልዑካን የተገኙ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ አርቲስቶች እንደ ካናዳዊ ሴሊን ዲዮን እና አሜሪካዊቷ ሌዲ ጋጋ የመሳሰሉት ትርኢቶቻቸውን አቅርበዋል።

የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት የዘንድሮው የኦሊምፒክ ውድድሮች መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በርካታ ተመልካቾቹ አስደናቂ የውበት፣ የደስታ፣ መልካም ትዝታዎችን የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ ያላቸውን አድናቆት ቢገልጹም “ነገር ግን በክርስትና እምነት ላይ የሚሳለቁ እና አጸያፊ ትዕይንቶችን ያካተተ ነበር” ብለው፥ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ትችቶች ከቀረቡባቸው ትዕይንቶች መካከል ግንባር ቀደሙ በጣሊያናዊው ሠዓሊ በሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ የተሳለ “የመጨረሻው እራት” የጥበብ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሌሎች ቤተ እምነቶች ያሰሙት ቅሬታ
በብዙሃን መገናኛዎች በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰራጨውን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ በርካታ የሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎች ለፈረንሳይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ያሳዩትን አጋርነት ጳጳሳቱ በመግለጫው ገልጸዋል።

“በአንዳንድ አላስፈልጊ በሆኑ ትዕይንቶች ያዘኑትን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖችን” እናስባለን ያሉት የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በመቀጠልም፥ “የኦሎምፒክ ውድድሮች የመክፈቻ በዓል ከጥቂት አርቲስቶች ርዕዮተ ዓለም አድሎአዊ አመለካከት የዘለለ መሆኑን እንደሚረዱ ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል።

የተወሰኑ አማኞችን ማግለል
የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ አባ ሁጌስ ደ ዋይልሞ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ በጻፉት መልዕክት፥ በኅብረት በተወሰኑ አማኞች መገለል መካከል ያለውን ተቃርኖ በማጉላት ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ለማራመድ ተብሎ ህሊናን መጉዳት አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የመገናኛ መምሪያ ፕሬዝዳንት እና የፍሬጁስ ቱሎን ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ፍራንሷ ቱቬት፥ የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መግለጫን በማጠናከር በሰጡት አስተያየት፥ “ከልክ ያለፉ የትዕይንቱን ትርኢቶች ሳልረሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን አሳፋሪ እና ከባድ ስድብ እቃወማለሁ” ብለዋል።

በጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የፓሪስ የ 2024 ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አሎይሲዮ ቅዳሜ ሐምሌ 20/2016 ዓ. ም. በሰጡት ምላሽ፥ “የልዩነት ድንበር ለማስወገድ ባደረግነው ውሳኔ እንቆማለን” ብለዋል።

አንድነት እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት
የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በመግለጫው ማጠቃለያ፥ “ስፖርት የአትሌቶችን እና የተመልካቾችን ልብ በእጅጉ የሚያስደስት ድንቅ እንቅስቃሴ ነው” ብሎ፥ “የኦሎምፒክ ውድድር የአንድነት እና የሰው ልጅ ወንድማማችነት እውነታ የሚያገለግል እንቅስቃሴ ነው” በማለት አስታውሷል።



29 July 2024, 17:43