ሕንድ ውስጥ አካል ጉዳተኛ ልጆችን የሚንከባከቡ የናዝሬት በጎ አድራጎት ገዳማዊያት እህቶች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአዕምሮ እክል ያለባቸውን ልጆች ለማገልገል ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት በመነሳት፣ የናዝሬት በጎ አድራጎት እህቶች እ.አ.አ በ1995 ‘አሻ ዲፓም ዳር የእንክብካቤ ማዕከልን’ አቋቁመዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሻ ዲፓም የአእምሮ እክል ያለባቸውን ልጆች በመንከባከብ እና ልጆቹ ባላቸው ልዩ ችሎታዎች እና እምቅ አቅም ላይ በማተኮር ሁለንተናዊ እድገታቸው እንዲመቻችላቸው እድሎችን ይፈጥርላቸዋል።
ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቦችን ለዕለታዊ ተግባራት አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን ያስታጥቃቸዋል፣ የትምህርት እና የሙያ እድሎችን እንዲከታተሉ ያበረታታል፣ እንዲሁም በማህበራዊ እና በትርፍ ሰዓት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ያደርጋል።
ተማሪዎቹ በተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች ላይ የተሰማሩ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ሻማ በማምረት፣ ምግብ በማብሰል፣ እንዲሁም አበባ፣ አምባር እና የተለያዩ ጌጣጌጦችን እና ሰንደሎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም፣ የልብስ ስፌት እና የአትክልተኝነት ትምህርቶችን ይማራሉ።
ባለፉት ዓመታት፣ አሻ ዲፓም ወደ 460 የሚጠጉ ህጻናትን ረድቷል፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን አሻሽሏል፣ እንዲሁም አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ረድቷል። ወደ 50 የሚጠጉ ተማሪዎች ደግሞ ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ ድጋፍ አድርጓል።
ከተማሪዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ በዞን፣ በክልላዊ እና በብሔራዊ ልዩ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ፣ እንዲሁም በአሜሪካ እና በግሪክ በተደረጉ የዓለም አቀፍ ልዩ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፈው ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
ጁሊያን ሳንቶ በተለይ ትምህርት ቤቱ ከሚኮራባቸው ልጆች አንዱ ሲሆን፥ የእሱ የለውጥ ታሪክ የልጆቹን፣ የወላጆችን፣ የገዳማዊያትን እና የአሻ ዲፓም ሰራተኞችን ጥረት እና ስኬት ያሳያል።
የጁሊያን ሳንቶ ጉዞ
ጁሊያን ሳንቶ የአዕምሮ ዝግመትን (ኦቲዝም) ጨምሮ የማየት ችግር ያለበት አካል ጉዳተኛ ልጅ ሲሆን፥ ከአምስት ዓመት በፊት በክራውፎርድ ክልል፣ ትሪቺ ከተማ ወደሚገኘው አሻ ዲፓም ልዩ ትምህርት ቤት ሲገባ ከፍተኛ መሰናክሎች አጋጥመውታል።
በዚያን ጊዜ የእናቱን ፊት እንኳን መለየት አይችልም ነበር፥ እሷን ለመለየት እንደ ቁመት ባሉ አካላዊ የመለያ ዘዴ ይጠቀም ነበር። ጁሊያን ወደ ቅድመ-መጀመሪያ ደረጃ ሲሸጋገር፣ በአይን እክል እና በኦቲዝም ምክንያት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ ማለትም መመገብ፣ ልብስ መልበስ እና የመታጠቢያ ቤት መገልገያዎችን መጠቀም ላይ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። መጠኖችን፣ ቀለሞችን እና ቅርጾችን መረዳት አለመቻሉ ችግር ፈጥሮበታል።
ትምህርት ቤቱ የእይታ ችግሮቹን ለመቅረፍ ሁሉንም አስፈላጊ የህክምና ዕርዳታዎችን የሰጠው ሲሆን፥ መምህሩ ከሆኑት ወይዘሮ ሮዝሊን ፍራንሲስ በመመራት እና በገዳማዊያቱ ጠንካራ ክትትል በህይወቱ ላይ ለውጥ የሚያመጣ የሶስት ወር ልዩ የስሜት ህዋሳት ስልጠና ብሎም የማየት ችሎታውን ለማሻሻል በተሰጠ ስልጠና ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
ድርብ ችግር ያለባቸውን አካል ጉዳተኞችን መንከባከብ
ጁሊያን ለበርካታ ዓመታት ከወሰደው ሰፊ ሥልጠና በኋላ ቃላቶችን የመደጋገም (የመንተባተብ) ችግሩን በተሳካ ሁኔታ አሸንፏል። አሁን በክፍል ውስጥ ያሉትን ነገሮች በብቃት መለየት፣ የአካል ክፍሎችን መለየት፣ ቃላቶችን መረዳት፣ የተለያዩ ቅርጾችን እና ቀለሞችን መለየት እና ሌሎችንም ማድረግ ይችላል።
ጁሊያን የፍራፍሬ፣ የአትክልት፣ የልብስ ዓይነቶችን፣ መኪናዎች፣ ወፎች እና ሌሎች ፍጥረታት ስሞችን የመግለጽ ችሎታ አዳብሯል። በተጨማሪም የጠዋት ጸሎቶችን ማንበብ፣ ጠቅላላ እውቀትን ማሳየት፣ የቁጥር ስሞችን ማስታወስ እና አናባቢዎችን እና ተነባቢዎችን መለየት ይችላል።
ምንም እንኳን የእይታ እክል ችግሮች ቢኖሩም፣ ጁሊያን እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታዎችን የማስታዎስ አስደናቂ ችሎታ አለው።
ራስን ለመቻል የተደረጉ ጉልህ እመርታዎች
የጁሊያን ሳንቶ እናት ጆአን ማታራሲ አሻ ዲፓም ልዩ ትምህርት ቤት ከተቀላቀለች በኋላ በልጇ ላይ በታየው አስደናቂ እድገት ያላትን ታላቅ ደስታ እና ምስጋና ገልፃለች።
እናቱ ጁሊያን ራሱን ለመቻል ጉልህ ጥረት እንዳደረገ ገልጻ፥ አሁን ፍላጎቱን በልበ ሙሉነት መናገር ይችላል ካለች በኋላ፥ የአጻጻፍ ብቃቱ ጉልህ መሻሻል አሳይቷል፣ ስለትምህርት ቤቱ እንቅስቃሴ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ በንቃት ይጋራል ብላለች።
ልጆችን ከመግፋት ይልቅ አብሮ ወደ መጫወት እና ከእኩዮቹ ጋር ጓደኝነትን ወደ መፍጠር በመሸጋገሩ የጁሊያን ባህሪ የተረጋጋ እና የበለጠ አካታች ሆኗል። በተለይም የመምህራኑን መመሪያዎች በትክክል የመከተል እና የመመለስ ችሎታ አዳብሯል።
“ጁሊያን ወደ አሻ ዲፓም ከመግባቱ በፊት ሁሉንም መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለመፈፀም በእኔ ላይ ተሞርኩዞ ነበር፥ በዚህም ምክንያት የልጄን ሁኔታ ስመለከት ተስፋ ቆርጬ ነበር። ነገር ግን ወደ አሻ ዲፓም ትምህርት ቤት ከተቀላቀለ በኋላ፣ የተሻሻሉ የአመጋገብ ልማዶችን በማሳየት እና የትምህርት ቤቱን አልባሳት በመልበስ ራሱን ችሎ ለትምህርት ቤት ይዘጋጃል” ስትል ጆአን በደስታ አጋርታለች።
አክላም ጁሊያን በዕለት ተዕለት የትምህርት ሂደቱ እርዳታ ለማግኘት ወደ እሷ እንደሚቀርብ፣ ስራዎቹን በጋለ ስሜት እና በራስ መተማመን እንደሚያጠናቅቅ ተናግራለች።
የእግዚአብሔር እገዛ እና ጥበቃ በአገልግሎት
የአሻ ዲፓም ልዩ ትምህርት ቤት ወደ 460 ከሚጠጉ ህጻናት ጋር በመሆን ክብራቸውን በማደስ እና ስኬታማ ህይወት እንዲመሩ በማስቻል በለውጥ ጉዞ ላይ ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል ወደ 50 የሚጠጉ ተማሪዎች ራሳቸውን ችለው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ። በተለይም ከማዕከሉ ስድስት ሴት ልጆች እና አራት ወንዶች ጋብቻ ፈፅመው በህብረተሰቡ ውስጥ በክብር እየኖሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም አሻ ዲፓም ትምህርት ቤት ቀን ቀን ለ45 ልጆች መኖሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህርት የሆኑት ሲስተር ሳሌት ሜሪ፣ “እነዚህን ልዩ ልጆች ለመርዳት በመቻላችን ለእኛ ትልቅ እድል ነው። የእግዚአብሄርን ፊት በየቀኑ በእነሱ ውስጥ እናያለን፥ በፊት ለዓመታት በመደበኛው ትምህርት ቤቶች ውስጥ እሰራ ነበር፥ ወደዚህ ቦታ መጥቼ እነዚህን ልዩ የሆኑ ልጆች መርዳት በመቻሌ ሃይማኖታዊ ሕይወቴ ላይ ጥልቅ ትርጉምና እርካታ አምጥቷል” በማለት ገልጸዋል።
ሲስተር ሳሌት ሜሪ እነዚህ ልጆች ምግብ እና አስፈላጊ ነገሮችን በሚያቀርቡ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ደግነት በየቀኑ የሚያጋጥሟቸውን አስገራሚ ነገሮች በማንሳት፥ በሕይወታቸው እና በአገልግሎታቸው የእግዚአብሔር የማያቋርጥ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዳለ አምናለሁ ብለዋል።
እንደ ጁሊያን ባሉ ተማሪዎች ላይ የሚታዩትን አወንታዊ ለውጦች በመመልከት በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከራቸውን ገልጸው፥ “እግዚአብሔር በናዝሬት በጎ አድራጎት ገዳማዊያት እህቶች በኩል ለህዝቡ ይገለጣል” ሲሉ ሲስተር ሳሌት ሜሪ አጠቃለዋል።