ፈልግ

ሰኔ 25 በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሃትራስ መንደር ተረጋግጠው የሞቱ ሰዎች ጫማዎች ሰኔ 25 በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ሃትራስ መንደር ተረጋግጠው የሞቱ ሰዎች ጫማዎች   (AFP or licensors)

የሕንድ ብጹአን ጳጳሳት በሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ተረጋግጠው ለሞቱት እና ለቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ቅርበት ገለጹ

የህንድ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኒው ዴልሂ በስተደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ሙጋል ጋርሂ መንደር ውስጥ በሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ ቢያንስ 121 ሰዎች ተረጋግጠው በመሞታቸውን ምክንያት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል። አደጋው ያጋጠመው አትራ ፕራዴሽ ግዛት ሳትሳንግ በተባለ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ መሆኑን የአከባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሻላብህ ማቱር ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህንድ ብጹአን ጳጳሳት አደጋውን አስመልክትው ባወጡት መግለጫ “ለሞቱት ነፍሳት ዘላለማዊ ዕረፍት እንጸልያለን፣ የቆሰሉትም በፍጥነት እንዲያገግሙ ተስፋ እናደርጋለን” በማለት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ያላቸውን “መንፈሳዊ ቀረቤታ” ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ የመረጋገጥ አደጋው እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ግልጽ ባይሆንም የዓይን እማኞች ፌስቲቫሉ የተካሄደበት ስፍራ መውጫ በጣም ጠባብ መሆኑን እና አቧራማ አውሎ ንፋስ ግራ መጋባት እና ድንጋጤ ፈጥሮ ሰዎች መሯሯጥ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰውም በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ እጅግ የሚወደደው ሰባኪ ቡሆሌ ባባ ከተፈቀደው ቁጥር በላይ ህዝብ በተሰበሰበበት ረግረጋማ ቦታ ለሃይማኖቱ ተከታዮች ሲሰብክ በነበረበት ቦታ እንደሆነም ተገልጿል። ይህ አደጋ  በህንድ ውስጥ ከአስር አመታት ወዲህ የደረሰ አስደንጋጭ አደጋ ነው ተብሏል።

አንዳንድ ዘገባዎች እንደዘገቡት በዝግጅቱ ላይ ከ250,000 በላይ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፥ ይህ አሃዝ አዘጋጆቹ ፈቃድ ካገኙላቸው 80,000 ሰዎች በእጅጉ ይበልጣል ተብሏል።

በተጨማሪም የፖሊስ ምርመራ እንደሚያሳየው ተከታዮቹ በሰባኪው በተነካው መሬት ላይ አፈር ለመሰብሰብ ሲሞክሩ ግርግሩ መጀመሩን ይጠቁማል።

በግርግሩ መሃል አንዳንድ ተሰብሳቢዎች በመንገድ ዳር በሚገኝ ፍሳሽ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ወድቀው መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፥ ሌሎች ደግሞ የሃይማኖት መሪውን እና ቡድኑን መጀመሪያ ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ታግደው ነበር ተብሏል።

የተጣሉ አልባሳት እና ጫማዎች ከክስተቱ በኋላ በጭቃማው ቦታ ላይ ወድቀው የታዩ ሲሆን፣ ይህም ከተጨናነቀው አካባቢ ለመውጣት ሲሞክሩ ተሰብሳቢዎቹ እርስ በእርሳቸው በመተጣጠፍ የተፈጠረውን ትርምስ ያመለክታሉ።

የክልሉ የአደጋ አስተዳደር ማዕከል የሟቾችን ቁጥር ያረጋገጠ ሲሆን ሁሉም ተጎጂዎች ከሞላ ጎደል ሴቶች መሆናቸውን ገልጿል።

በዝግጅቱ ወቅት ተረኛ የነበረችው የ50 ዓመቷ የፖሊስ አባል ሺላ ማውሪያ በአደጋው ጊዜ ስለነበረው ስትገልጽ “ሁሉም፣ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ አጠቃላይ ተሳታፊ በአንድ ጊዜ ከዝግጅቱ ቦታ ወጡ። ሁሉንም በአንድ ጊዜ የሚያስወጣ በቂ ቦታ አልነበረም፥ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ፣ ተደነቃቅፈው በመውድቅ መረጋገጥ ጀመሩ” ብላለች።

ሌላ የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ደግሞ የነበረውን ሁኔታ ስትናገር፤ “ስነ-ስርዓቱ እንዳበቃ ሰዎች በፍጥነት ለመውጣት ሲሞክሩ መገፈታተር እና መረጋገጥ ተፈጠረ። በጣም ብዙ ሰዎች ቱቦ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸው አልፏል” ስትል ተናግራለች።

በአቅራቢያው በሚገኝ ሆስፒታል ጊዜያዊ አስከሬን ማቆያ ውስጥ፣ የሟቾቹ ቤተሰቦች ከአስከሬኖች ውስጥ የጠፉ ዘመዶቻቸውን ሲፈልጉ እንደነበርም ተገልጿል። ከነዚህም መካከል የ35 ዓመቱ አርሶ አደር ራም ኒቫስ የጠፋችው አማቱን ፍለጋ በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎችን ውስጥ ሲፈልግ ማደሩ የገለጸ ሲሆን፥ በህይወት ልትገኝ እንደምትችል ተስፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን “የትም ልናገኛት አልቻልንም” ሲል በቁጭት ተናግሯል።

የህንድ መንግስት ሃዘኑን በመግለጽ እና በገንዘብ እርዳታ በማድረግ ለአደጋው ምላሽ የሰጠ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለሟች እና ለቆሰሉ ቤተሰቦች ካሳ እንደሚከፈል አስታውቀዋል።

ፕሬዝደንት ድሮፓዲ ሙርሙ በበኩላቸው አደጋውን “ልብ የሚሰብር” ሲሉ ሃዘናቸውን ገለጸዋል።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በህንድ ውስጥ ባሉ ትላልቅ ሃይማኖታዊ ፌስቲቫሎች ወቅት እየታየ ያለውን የደህንነት ክፍተቶች አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ በቂ ያልሆነ የህዝብ አስተዳደር እና የደህንነት ደንቦች አሁን የተፈጠረውን ከባድ አደጋ አስከትሏል ተብሏል።

በሕንድ በሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰዎች ተረጋግጠው ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በ2005 ዓ.ም. በማደሃያ ግዛት በተካሄደው የሂንዱ ፌስቲቫል ላይ 115 ሰዎች ተረጋግጠው ሞተው የነበረ ሲሆን፥ በ2000 ዓ.ም. በጆድፑር በሚገኘው ኮረብታ ላይ በሚገኝ ቤተ መቅደስ ላይ ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ የ224 ሰዎችን ህይወት ተቀጥፏል።

ለወደፊቱ እንደዚህ ያሉ አስከፊ ክስተቶችን ለመከላከል በሃይማኖታዊ ዝግጅቶች ላይ የተሻሻሉ የደህንነት እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ተብሏል።
 

05 July 2024, 16:10