ፈልግ

የኢንዶኔዥያ ወጣቶች ኮሚሽን ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በጃካርታ በሚገኘው የኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ዋና መሥሪያ ቤት ለአራት ቀናት በቆየው ዝግጅት ላይ የኢንዶኔዥያ ወጣቶች ኮሚሽን ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በጃካርታ በሚገኘው የኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ዋና መሥሪያ ቤት ለአራት ቀናት በቆየው ዝግጅት ላይ  

የኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለወጣቶች ተሳትፎ አዲስ አቅጣጫዎችን መዘርጋቷ ተነገረ

ሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ለአራት ቀናት የተካሄደው የኢንዶኔዥያ ወጣቶች ኮሚሽን (ኮምኬፕ) ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባኤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከወጣቶች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ተከታታይ አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን ዘርዝሮ ማውጣቱ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጃካርታ በሚገኘው የኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ዋና መሥሪያ ቤት የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ “ጎልታ የምትታይ እና ንቁ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር ወጣት ካቶሊኮችን ማሳተፍ እና ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን፥ በጉባኤውም ላይ ከ37ቱም ሀገረ ስብከቶች የወጣት ኮሚሽኖች የተውጣጡ 63 ተወካዮች ተሳታፊ ነበሩ።

“ክሪስቶስ ቪቪት” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያን መነሻ በማድረግ ምልአተ ጉባኤው ውይይቶቹን 'አቃፊነት እና ማሳደግ' በሚሉ ሁለት ወሳኝ ተግባራትን ያማከለ ነበር ተብሏል።

የወጣት ኮሚሽኖቹ የተመሰረቱበት ዋና ዓላማው የወንጌልን መልእክት በተጨባጭ መንገድ በማሰራጨት በህብረተሰቡ ላይ በጎ ተጽዕኖ የምታሳድር ‘ንቁ’ እና 'ጎልታ የምትታይ' ቤተክርስቲያንን ለማስፋፋት ነው።

በጉባኤው ላይ ለውይይት የቀረቡት እነዚህ አዳዲስ ስልቶች የሃዋሪያዊ ሥራን ማሻሻል እና የወጣት ካቶሊኮችን ተግባራዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን የሚያሟሉ ተጨማሪ አካታች አሰራሮችን መፍጠር የሚሉትን ያካተቱ ሲሆን፥ ምልአተ ጉባኤው በተጨማሪም በፓሌምባንግ ከተማ የተካሄደውን ‘ሶስተኛው የኢንዶኔዥያ ወጣቶች ቀንን’ እና የወጣቱን ተልዕኮ እንደገና ማደስ የቻለውን በሊዝበን በተካሄደው የ2023 የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ በንቃት መሳተፍ መቻላቸውን በማንሳት አበረታች በማለት እውቅና ሰጥቷል።

ምልአተ ጉባኤው ከዚህም በተጨማሪ የአእምሮ ጤና ጉዳዮች፣ ከኮሮና ወረርሽኙ በኋላ ያለው የስራ አጥነት መስፋፋት፣ የአካባቢ ስጋቶች እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ በወጣቶች ላይ የሚኖረውን ሰፊ ተፅዕኖ የመሳሰሉ ቀጣይ ተግዳሮቶችን በማንሳት ተወያይቷል።

ልዑካኑ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመወጣት የቤተክርስቲያንን የወጣቶች ተሳትፎ እንደገና ለማጎልበት እና ለመምራት የመንፈስ ቅዱስ እገዛ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት በቁርጠኝነት መሰራት እንደሚያስፈልግም ተስማምተውበታል።

የምልአተ ጉባኤው አንዱ ቁልፍ ውጤት ወጣቶቹ ግልጽነት እና የትብብር መንፈስን እንዲያጎለብቱ ብሎም ከልብ የሆነ ተሳትፎ እና ተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ እንዲቻል የወጣት ካቶሊኮች አጋሮች ቀጣይነት ያለው እገዛ እንዲያደርጉ የተደረገ ጥሪ ነው።

ይህም ወጣቶች በቤተክርስቲያን እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲመሩ እና በንቃት እንዲሳተፉ እድሎችን መፍጠር፣ እምነታቸውን እና ስጋታቸውን በትክክል የሚገልጹበት ቦታ እንዲኖራቸው ማድረግን ያካትታል ተብሏል።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ለወጣቶች ህይወት ገጽታ ለውጥ ምላሽ በመስጠት እንድትቀጥል በወጣት መሪዎች እና አጋሮች መካከል ቀጣይነት ያለው ግምገማ እና ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አጉልቷል።

ወደ ፊት የሚሰጡት ስልጠናዎች እና ግብዓቶች መሪዎችን በዲጂታል ሚዲያ፣ በሥነ-ምህዳር ተሟጋችነት እና በአእምሮ ጤና ጉዳዮች ላይ በብቃት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው ክህሎት እንዲኖራቸው በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ይህም ለወጣቶች አገልግሎት ሁለንተናዊ አቀራረብ እንዲኖራቸው ያግዛል ተብሏል።

የወጣት ተኮር ፕሮግራሞችን ለማስቀጠል እና ለማስፋፋት የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አካላት እና የውጭ አጋሮች የሚያካተቱበት የትብብር እና የገንዘብ ድጋፍ ሞዴሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የገንዘብ ምንጭ የማግኛ ስልቶች ላይም በሰፊው ተወያይተዋል።

ጉባኤው በመጨረሻም ለሁሉም ወጣት ካቶሊኮች ንቁ፣ አሳታፊ እና ደጋፊ ማህበረሰብን መፍጠር ለሆነው የቤተክርስቲያኗ ዋነኛ ተልእኮ ጠንካራ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ለቤተክርስቲያኑ ተልእኮ እና የስብከተ ወንጌል ጥረቶች ዋና ተሳታፊ እንዲሆኑ ወጣቶችን ከልብ እንዲያዳምጡ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የቀረበውን ጥሪ በድጋሚ በማቅረብ ተጠናቋል።
 

08 July 2024, 14:51