የኢራቅ ክርስቲያን ማህበረሰቦች የሚደርስባቸውን የማጥፋት ተግባር በጽኑ እንደሚቃወሙ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ድጋፍ ለሚፈልጉ ቤተክርስቲያናት እርዳታ በሚያደርገው ተቋም (ACN) አማካይነት በተዘጋጀው የኦንላይን ኮንፈረንስ ላይ ብጹእ አቡነ ሴማን በጠንካራው የወይራ ዛፎች ተፈጥሮ እና በክርስቲያን ኢራቃውያን ጽኑ መንፈስ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት አስረድተዋል።
ብጹእነታቸው “አይ ኤስ የተባለው ኢስላማዊ መንግስት እኛን ለማጥፋት ሞክሮ ነበር፣ ነገር ግን አልተሳካላቸውም” ሲሉ ከአሥር ዓመታት በፊት የተጀመረውን ክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ሁኔታ አስታውሰዋል። የብጹእነታቸው ምሳሌያዊ አነጋገር በህይወት ለመትረፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር ጠንክሮ ለመገኘት የወሰነውን ማህበረሰብ ምንነትን ይገልፃል ተብሏል።
ውይይቱ ከዚህም በተጨማሪ በቀጠናው እየተባባሰ የመጣውን ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶችንም አመላክቷል።
የኤርቢል ሃገረስብከት የከለዳውያን ማህበረሰብ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ባሻር ዋርዳ በበኩላቸው ስለ እነዚህ ውጥረቶች ያላቸውን ስጋት ገልፀው፥ በሰፊው የክልል ግጭቶች ውስጥ እራሳቸውን እንደ ኢላማ ወይም አጠቃላይ ተጎጂ ሆነው የሚያገኙትን ክርስቲያኖች ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ ጠቅሰዋል።
ዛሬ ላይ ከእስላማዊ መንግስት ታጣቂዎች ቀጥተኛ ዛቻ ባይኖርም፣ ትተው የሄዱት የከፋፋይ ርዕዮተ ዓለም ቅሪቶች በህብረተሰባዊ መግባባት ላይ ፈተና እየፈጠሩ ይገኛሉ ተብሏል።
ብጹእ አቡነ ሴማን ማህበረሰቦችን ወደ “ገለልተኛ ደሴቶች” ተለይተው እዲቆዩ የሚያደርገው ሃይማኖታዊ መገለል መንስኤው የመስተጋብር እና የጋራ መግባባት እጦት መሆኑን በማንሳት ነቅፈዋል።
ብጹእነታቸው የመከባበር እና የመደመር ባህልን ለማዳበር ያለመ ከሀይማኖት ልዩነት ይልቅ ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያ የሚሰጡ የትምህርት እና የህግ ማዕቀፎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አስምረውበታል።
ድጋፍ ለሚፈልጉ ቤተክርስቲያናት እርዳታ የሚያደርገው ተቋም ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያበረታቱትን የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ፣ በነነዌ ከተማ ክርስቲያናዊ ህልውና እንዲያንሰራራ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።
የዓለም አቀፍ ተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሬጂና ሊንች እንደገለጹት ድርጅቱ ለኢራቅ የክርስቲያን ማህበረሰብ ሁለገብ ድጋፍ ማድረግ የጀመረው በጎሮጎሳዊያኑ በ 2014 ዓ.ም. ባደረገው የአስችኳይ ጊዜ ዕርዳታ ሲሆን፥ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ሰፊ የመልሶ ግንባታ ጥረቶችን አድርጓል ብለዋል።
ይህንንም በማስመልከት እንደተናገሩት “በቀጣዮቹ ዓመታት፣ ማለትም ኢስላማዊው መንግስት ከስፍራው ከለቀቀ በኋላ በመጀመሪያ የተፈናቃዮቹን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለሟሟላት ጥረናል፣ ከዚያም አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተናል፣ በመጨረሻም ነባሮቹን ቤቶች መልሶ በመገንባት ወደ ከተማቸው እና መንደራቸው መመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲመለሱ ረድተናል” በማለት የተቋማቸውን አስተዋጽዖ አስረድተዋል።
ዛሬ፣ አይ ኤስ ወደ ስፍራው ከመምጣቱ በፊት ከነበሩት ክርስትያኖች መካከል ግማሽ ያህሉ ወደ ተመለሱበት፣ እንደ ቋራቆሽ ባሉ ከተሞች ውስጥ የመልሶ ማገገም ምልክቶች ይታያሉ።
የማህበረሰቡን የመልሶ ማቋቋም ሂደት ውስጥ አሳዛኙ ሁኔታ ወደ ሌላ ሃገራት ከተሰደዱት ውስጥ በተለይ ልጆች ያሏቸው አብዛዎቹ በዘላቂነት ተመልሰው ሊመጡ እንደማይችሉ ሲታወቅ የብስጭት ስሜትን ይፈጥራል ብለዋል ሃላፊዋ።
ብጹእ አቡነ ዋርዳ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እና ሌሎች ክርስቲያን ያልሆኑ ማህበረሰቦች ትምህርታዊ ድጋፍን እንደሚሰጠው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ነፃ የትምህርት ዕድል መርሃ ግብር እና ሌሎች ተነሳሽነቶችን በመጥቀስ፥ እነዚህ በተግባራዊ የደግነት ሥራዎች የአብሮነት እና የወንድማማችነት ወንጌልን ይገልፃሉ ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ዋርዳ በመጨረሻም፣ “ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሸሸጊያ ብቻ ሳትሆን የሕዝቡ የሕይወት መስመር ናት” በማለት ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ ድጋፍን ለመስጠት ሃይማኖታዊ ተግባሯን እንዴት እንደምታከናውንና ሌት ተቀን ክፍት የሆነች የተቀደሰች ሥፍራ መሆኗን አስረድተዋል።