ፈልግ

የሚያርመንን ሰው አንጥላ የሚያርመንን ሰው አንጥላ 

የሚያርመንን ሰው አንጥላ

ማንኛውንም ሰው በድለንና አሳዝነን በወዳጅነትና በወንድማማችነት መንፈስ ሊያርመን ወይም ሊገስጸን ቢፈልግ ብዙ ይሰማናል ቶሎ እንቆጣለን አንቀበለውም እንቃወመዋለን። በመልካም ሐሳብ በደላችንን አስረድቶን ሊያርመን የሚፈልገውን ብዙ ጊዜ በክፉ ዓይን እንመለከተዋለን። በእኛ ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ለጥቅማችን ብለው ሲገስጹን ክፉኛ እንጠላቸዋለን። አንዲት ዝነኛ ሴት በመስተዋት ፊቷን ስትመለከት በወጣትነቷ ጊዜ የነበራት ቁንጀናና ውበት ተበላሽቶ ስታይ እጅግ ተቆጥታ አስቀያሚ ፊቷን ያሳያትን መስተዋት አደቀቀችው። ከዚህ በኋላ መስተዋት የሚባል ነገር አልያዘችም።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን  

ይህ የሚገርም ምሳሌ እነዚያ ተግሳጽን የሚጠሉ፣ እውነትን ነግረው ሊያረሙ የሚፈልጉ ወንድሞችን ጠልተው ተቆጥተው የሚሸሹና የሚርቁ ሰዎችን የሚያመለክት ነው። እንደዚህች ጉደኛ ሴት እንደ መስተዋት ጉድለታቸውን አስረድቶ የሚመክራቸውን ይሸሻሉ። ሌሎች ለጥቅማቸው ብለው ያስቡትን እነርሱ በክፋት እያሰቡት ደግሞም ክፋታቸው እንዳይገለጥና በእርሱም ሊኖሩ እንደሚፈልጉ ያስረዳል። ቅዱስ ዮሐንስ ስለነዚህ ሰዎች ሲናገር «ክፉ ተግባሩ እንዳይገለጥ ከብርሃን ይሸሻል ብርሃንን ይጠላል” (ዮሐንስ 3፡20) ይላል። 

«እኔስ ኃጢአተኛ ነኝ” ይል የነበረ አንድ መነኩሴ ሰራፕዮን ወደሚባል ባሕታዊ ሄደ። ባሕታዊው ስራፕዮን አንድ ቀን በማዕድ ተቀምጠው ሲበሉ በአፍ ብቻ ኃጢአተኛ ነኝ እያለ በመዞር ይለፍፍ የነበረውን መነኩሴ ሊጠቅመው ብሎ የሰማውን አንዳንድ ጉድለት ሊያርመው ፈለጐ ፍቅርና ለዛ በተሞላበት አነጋገር ልጄ ሆይ በጥሩ መንገድ ላይ ትገኛለህ፣ በዚሁ ቀጥልበት በይበልጥ እንድትሻሻል ግን ከቤት ወደ ቤት «እኔ ኃጢአተኛ ነኝ” እያልክ ከመዞር ተቆጠብ፤ ይልቅስ በቤትህ ውስጥ ተቀምጠህ እና ቤትህን ዘግተህ ጸሎትንና ጽሞናን የቅዱሳን መጸሐፍትን ንባብ ውደድ፣ ነገሩ እንዲገባህ እንደገና እደግማወለሁ” አለውና ደገመለት። መነኩሴውም ይህን ጠቃሚ ምክር በሌላ አመለካከት ተርጉሞ አንደ ስድብ በመቁጠር በመቆጣት ውስጣዊ ሐዘኑንና ቁጭቱን ገለጠለት። ያዋረደው መስሎት መጥፎ መለሰለት። ሰራፕዮን ለዚህ ተዘጋጅቶ አስተዋለውና «በጭራሽ ትሕትና የለህም” በማለት አሰናበተው።

ወላጆቻችንና አለቆቻችን እንዲሁም አዋቂዎች ለእኛ ጥቅም ሲያርሙንና ሲገስጹን እንደ መነኩሴው እንቆጣለን እናጉረመርማለን፣ በደላችን ሲገለጥ እናዝናለን በመሸፋፈን እንከላከላን እናመካኛለን፣ ክፉ በማድረጋችን መቀጣት እንደሚገባን እያወቅን እናኰርፋለን። «ታዲያ የሚደረገው እኮ እንደዚህ አይደለም፣ ጊዜው አይደለም፣ እኔ እኮ የምታረመው እንዲህ አይደለም፣ እንደዚህ ዓይነት ተግሳጽ እና ቅጣት አልፈልግም፣ ባሰብኝ” እያልን በእነርሱ ላይ እናጉረመርማለን። ይባስ ብለን ደግሞ እንቀየማቸዋለን፣ በመጥፎ ዓይን በመመልከት እንገላምጣቸዋለን።

ከዚህም በላይ በመጥፎ ንግግርና በኃይለ ቃል እንመልስላቸዋለን። ፍላጐታችንና ፈቃዳችንን እንድናደርግ ያልተወንን እናዝንበታለን። «ባቢሎንን ፈወስናትና ተንከባከብናት፣ ግን ልትድን አልፈለገችም። እንግዲህ እንደ ፈቃዷና እንደ ዕድሏ ትተናታል” (ኤር. 51፣9) ይላል መጽሐፈ ኤርሚያስ። የሚመክረንን ሰው ከጠላን ራሳችንን እንጠላለን፣ ስህተታችንን እንወዳለን ማለት ነው። «የተገለጠ ዘለፋ፣ ከተደበቀ ፍቅር ይሻላል” (ምሳሌ 27፡5)። “የወዳጅ ማቁሰል ለክፉ አይሰጥም፣ የጠላት መሳም ግን የውሸት ነው” (ምሳሌ 27፡6)። «ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፣ ዘለፋ የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል” (ምሳሌ 15፡32)። «ተግሳጽን የሚወድ ሰው በአዋቂዎች መካከል ይገኛል፣ የልቡ ባለቤት ይሆናል፣ ተግሳጽ የሚጠላ ግን ኃጢአትን ይከተላል፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ግን በተገሣጽ ልቡ ይቀየራል” (መ. ጥበብ 21፡7)።

ቁም ነገረኛ ሰዎች ለመሆን ከፈለግን ተግሣጸና ቅጣትን አንጥላ። አሜን ብለን በትሕትናና በትዕግሥት እንቀበለው። በአንጻሩ ከብዙ ስህተት ለመዳን ከፈለግን የመሪዎቻችንን የአዋቂዎችን የሽማግሌዎችን ተግሳጽ እንቀበል፤ ቅጣታቸው ለጥቅማችን እንደሆነ አንገንዘብ። ቅዱሳን የሚገሥጿቸውን፣ የሚቆጡአቸውን፣ ስህተታቸውን የሚነግሩአቸውን ይወዷቸዋል፣ ወዳጅም ያደርጓቸዋል። ምንም ሳያጠፉ ቢቀጡ ይደሰታሉ። እንደ እነርሱ ትዕቢትን እና ራስ መውደድን ትተን ትሑታን እንሁን፣ ስንፍና እንዳለብን እንወቅ። ስለዚህ ለጥቅማችን ብለው የሚያርሙንን ሰዎች አንጥላ። ማንኛውም ተግሳጽ በደስታ ተቀብለን እንጠቀምበት።

18 July 2024, 15:53