ኒውዚላንድ ውስጥ በሕጻናት እና በአቅመ ደካሞች ላይ ጥቃት ሲደርሶባቸው እንደ ነበር ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በኒውዚላንድ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1950 እና 2019 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ በመንግሥት እና በሃይማኖት ተቋማት ይተዳደሩ በነበሩ እንክብካቤ መስጫ ማዕከላት ውስጥ ቢያንስ በ200,000 ሕጻናት እና አቅመ ደካማ ጎልማሶች ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል ወይም ችላ ተብለዋል ሲል ስድስት ዓመታትን የፈጀ የሮያል ኮሚሽን ግኝት አስታውቋል። ግኝቱ ይፋ የሆነው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሮያል ኮሚሽን በእንክብካቤ መስጫ ማዕከላት ውስጥ ይደርሱ የነበሩ ጉዳቶችን አስመልክቶ ለኒውዚላንድ ፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት በኩል እንደሆነ ታውቋል።
በኒውዚላንድ መንግሥት ጥያቄ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 የተቋቋመው የምርመራ ኮሚሽኑ ከጥቃቱ ከተረፉ 2,300 በላይ ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል። ኮሚሽኑ ምርመራውን ያካሄደው 655,000 ሰዎችን ይደግፉ በነበሩ ወላጅ አልባ ሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከላት፣ የአእምሮ ጤና ተቋማት እና በሌሎች የእንክብካቤ መስጫ ሂደቶች ላይ እንደሆነ ታውቋል።
የማይታሰብ ሃገራዊ ጥፋት ነው!
ከሪፖርቱ ጋር ይፋ የወጣው የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ የአቶ ኮራል ሾው መግለጫ ግኝቱን “የማይታሰብ ብሔራዊ ጥፋት ነው” ሲል ገልጾታል። በማዕከላቱ ውስጥ ይፈጸሙ የነበሩ ሕገወጥ ድርጊቶች የተባሉት ድብደባዎች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ በረሃብ መቅጣት፣ የኤሌክትሪክ ንዝረቶች፣ የኬሚካል እገዳዎች፣ የሕክምና ሙከራዎች እና ማምከን፣ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ እና ስሜታዊ ጥቃቶች እንደነበሩ ታውቋል።
ብዙዎቹ ሰለባዎች ከቤተሰቦቻቸው ተወስደው በመንግሥት እና በእምነት ተቋማት የእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ የተቀመጡ እና ባብዛኛው የማኦሪ የቀደምት ተወላጆች እንደ ነበሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ጥቃቱ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው አቅመ ደካማ ጎልማሶችንም ያካተተ እንደሆነ ታውቋል። ከጊዜ ወደ እየተስፋፉ የመጡ እነዚህ በደሎች ባለፉት ሰባት አሥርት ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል። በተጨማሪም ከጥቃቱ ሰለባዎች 42 በመቶ የሚሆኑ በተለያዩ ቤተ እምነቶች በሚተዳደሩ የእንክብካቤ መስጫ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች እንደሆኑ ጥናቱ አረጋግጧል።
ሥር የሰደደ ስልታዊ በደል ነበር
ትክክለኛ እና አጠቃላይ የተጎጂዎች ቁጥር ከተገመተው 200,000 በላይ ሊሆን እንደሚችል የኮሚሽኑ ሪፖርት ገልጿል። ኮሚሽኑ በማከልም በመንግሥት እና በእምነት ተቋማት የመረጃ እጥረት እና ደካማ የመዝገብ አያያዝ፣ የጊዜ መራዘም፣ የመረጃ ግልጽነት እጦት፣ በደሎችን ለመደበቅ በሚወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት ትክክለኛ አሃዝ መናገር እንደማይቻል ገልጿል።
አንዳንድ የጥቃቱ ሰለባዎች በእንክብካቤ ላይ እያሉ እንደሞቱ ወይም እራሳቸውን እንዳጠፉ የገለጸው የኮሚሽኑ ሪፖርት፥ በሕይወት የተረፉትም ቢሆኑ በደረሰባቸው እንግልት እና ቸልተኝነት የተነሳ የዕድሜ ልክ ሰቆቃ እየገጠማቸው እንደሆነ አመልክቷል።
የጥቃቱ የተረፉት ፍትህን ተነፍገዋል
ሆኖም ቅሬታዎቻቸው እና የፍትህ ጥያቄዎቻቸው ያልተሰማላቸው እና ችላ የተባለላቸው መኖራቸውን የገለጸው የኮሚሽኑ ሪፖርት፥ በመንግሥት እና በሃይማኖት መሪዎች በኩል በደል እንደሚደርስባቸው ቢታወቅም በድርጊታቸው የማይጠየቁ በመሆናቸው ተጨማሪ ግፍ እንዲፈጽሙ የሚበረታቱ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጦ፥ ብዙዎች ጥቃት ፈጻሚዎች ከነበሩበት ማዕከል ወደ ሌላ ማዕከል ተዛውረው ጥፋታቸውን መቀጠላቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።
የሕዝብ የይቅርታ እና የካሳ ጥያቄ
አጣሪ ኮሚሽኑ በዝርዝር ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል፥ 138 ምክረ ሃሳቦች የተቋማቱ ኃላፊዎች ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ እና መንግሥትም የአገሪቱን የአደጋ ማካካሻ መርሃ ግብርን እንደገና እንዲያጤነው እና ከጥቃት ለተረፉት ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል።
በሪፖርቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኒውዚላንድ ካቶሊካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (NZCBC) ፕሬዚዳንት ብጹዕ አቡነ ስቲቭ ሎው አጣሪ ኮሚሽኑን ለሥራው አመስግነው፥ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚደረገውን ጥበቃ ለማሻሻል ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ገልጸዋል።
ጥበቃን ለማሻሻል ቀጣይነት ያለው የቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነት
የኒውዚላንድ ካቶሊካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብጹዕ አቡነ ስቲቭ ሎው በመግለጫቸው፥ ላለፉት 30 ዓመታት በአቴአሮዋ ኒውዚላንድ በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ በደሎችን እና የሚደረጉ ጥበቃዎችን አስመልክቶ ለሚቀርቡ ሪፖርቶች ምላሽ በመስጠት ትልቅ ዕድገት ማሳየቷን አስታውሰዋል።
“ይህ ዕድገት እንዲቀጥል እና ቤተ ክርስቲያናችን የሰዎች የደህንነት ሁኔታ ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ የምናደርገውን ጥረት መቀጠል አለብን” ብለዋል። የሜቶዲስት እና የአንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት ለውጥ ለማምጣት ቃል የገቡ ሲሆን፥ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በመግለጫዋ፥ “ከጥቃት ለተረፉ ሰዎች ዕዳ አለብን” ስትል ተናግራለች።
ለመንግሥት የቀረበ የይቅርታ እና የካሳ ጥያቄ
የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ሉክሰን በበኩላቸው፥ የኒውዚላንድ መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ወር ላይ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ተናግረው፥ የማሻሻያ ሂደቱን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን እና ጠቅላላ የካሳ ክፍያው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም አስረድተዋል።