ፍልስጤማዊያን ሴቶች የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ ላይ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት ወቅት የእስራኤል ወታደሮች የሆሊ ፋሚሊ ትምህርት ቤትን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ ለቀው ሲወጡ ፍልስጤማዊያን ሴቶች የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ ላይ ባደረሱት የቦምብ ጥቃት ወቅት የእስራኤል ወታደሮች የሆሊ ፋሚሊ ትምህርት ቤትን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ ለቀው ሲወጡ  (AFP or licensors)

የኢየሩሳሌም ሃገረ ስብከት በጋዛ በሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ላይ የደረሰውን ድንገተኛ ጥቃት አወገዘ

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት በእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ስር በሚተዳደረው እና በጋዛ ከተማ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ትምህርት ቤት ውስጥ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ሃገረስብከቱ በጽኑ አውግዟል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እሁድ ጧት በጋዛ ከተማ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ትምህርት ቤት ላይ እስራኤላውያን ወታደሮች በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት አራት ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የእየሩሳሌም የላቲን ሃገረስብከት ድርጊቱን በጽኑ አውግዟል።

አራት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል

በእስራኤል አየር ሃይል የተከፈተው ድንገተኛው የአየር ጥቃት ያነጣጠረው በትምህርት ቤቱ ወለል ላይ በሚገኙ ሁለት የመማሪያ ክፍሎች ላይ ሲሆን፥ በክፍሎቹም ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማዊያን ተፈናቃዮች ተጠልለዋል። ከተገደሉት ሰዎች መካከልም የሀማስ ከፍተኛ የአስተዳደር ባለስልጣን እና የቡድኑ ምክትል የሰራተኞች ሚኒስትር የሆኑት ኢሃብ አል ጉሴይን ይገኙበታል ተብሏል።

የእስራኤል ጦር ሕንጻው የታጣቂዎች መሸሸጊያ ሆኖ እንደሚያገለግል፥ እንዲሁም በጊቢው ውስጥ “ሃማስ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ተቋም” እንደነበረው በመግለጽ፥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እና አደጋ በመቀነስ እርምጃዎችን መውሰዱን የእስራኤል መከላከያ ሃይል ገልጿል።

ሰኔ 30 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመራ ትምህርት ቤት ላይ የደረሰው ድንገተኛ ጥቃት

በካቶሊክ ትምህርት ቤት ላይ የተፈፀመው ድንገተኛ ጥቃት የተከሰተው የእስራኤል ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመራ ትምህርት ቤት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ካደረሱ ከሰዓታት በኋላ ሲሆን፥ በጥቃቱ ሁለት የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና የሥራዎች ኤጀንሲ ሰራተኞችን ጨምሮ በትንሹ 16 ሰዎች ሲገደሉ፣ 75 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ የጋዛ ባለስልጣናት ገልጸዋል። የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ በተቋሙ ላይ በደረሰው ተደጋጋሚ ጥቃት ቁጣውን መግለጹ ተነግሯል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን ወደ እስራኤል ዘልቆ ጥቃት ካደረሰ በኋላ በተጀመረው የጋዛ ሰርጥ ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። ሆኖም እስራኤል የሃማስ እና ሌሎች ታጣቂዎች በእነዚህ ቦታዎች ተደብቀዋል ስትል ትከሳለች።

ሲቪሎች ከጦርነቱ አከባቢ ርቀው መቆየት አለባቸው

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ ሃገረስብከት በመግለጫው፣ ተዋጊ ያልሆኑ ንጹሃን ሰዎችን ዒላማ ማድረግ፣ ወይም ሰላማዊ ሰዎች በጦርነቱ አከባቢ መኖር አለመኖራቸውን የማያረጋግጥ ማንኛውንም የትጥቅ እርምጃዎችን “በጽኑ” በማውገዝ፥ “ሁለቱ አካላት በክልሉ ያለውን አሰቃቂ የደም መፋሰስ እና የሰብአዊ አደጋዎችን በአፋጣኝ የሚያስቆም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ” ተስፋ እንደሚያደርግ እና በትጋት መጸለዩን እንደሚቀጥል ገልጿል።

ቀዳሚ ክስተቶች

በጋዛ ከተማ የሚገኘው እና 600 ያህል የተፈናቀሉ ክርስቲያኖችን ያስጠለለው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊት ሰበካ ቅጥር ግቢ ላይ የእስራኤል ኃይሎች ከሐማስ ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ምክንያት የደረሰበት ጥቃት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ተብሏል። ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ አንድ እስራኤላዊ አልሞ ተኳሽ በግቢው ውስጥ የነበሩ ሁለት ክርስቲያን ሴቶችን ማለትም እናት እና ልጇን መግደሉ ይታወሳል።

ይህ ድርጊት የተከሰተው ቅዱስ ፓርፊዮስ በሚባለው የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኝ ህንፃ ላይ በደረሰ የአየር ድብደባ በህንፃው ሥር ተጠልለው የነበሩ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ህይወታቸውን ካጡበት ጥቃት ከሁለት ወራት በኋላ መሆኑም ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ቅድስት መንበር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ደጋግመው አሳስበዋል።

ግንቦት ወር ላይ የፀጥታው ምክር ቤት በኒውዮርክ ባደረገው ግልጽ ክርክር የቅድስት መንበር ቋሚ ተልእኮ እንዳሳሰበው እንደ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና የአምልኮ ቦታዎች ያሉ የሲቪል መሠረተ ልማቶች የጦርነቱ ኢላማዎች መሆናቸውን እና ጥበቃ የሌለው የንጹሐን ህይወት ያለአግባብ እያለፈ መሆኑን በምሬት ገልጿል።

እስራኤላዊያን ተጎጂዎች እና ታጋቾች እንዲሁም የፍልስጤማዊያን ሞት ቁጥር

በቅርቡ፣ የቅድስት ሀገር ፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን ሀማስ መስከረም 26 ባደረሰው ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ውድመት እና ግድያ ሕጋዊ የሚያደርግ የ “ፍትሃዊ ጦርነት” ክርክርን ውድቅ አድርጓል።

ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ወረራ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የፍልስጤም አሸባሪዎች ወደ እስራኤል ክልል በመግባት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድለው፣ 251 ሰዎችን ደግሞ አግተው የወሰዱ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 116ቱ እስካሁን እንዳልተለቀቁ እና 42ቱ ሳይሞቱ አይቀርም ተብሎ ይታመናል። እስራኤል በጀመረችው የአጸፋ ጦርነት እስካሁን በጋዛ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች የሆኑበት ቢያንስ 38,000 ሰዎች መሞታቸውን በጋዛ የሚገኘው በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
 

09 July 2024, 13:50