ፈልግ

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት አርማ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት አርማ 

ካርዲናል አምቦንጎ፥ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለዓለም ልታዳርስ መጠራቷን ገለጹ

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (SECAM) የተመሠረተበት ሃምሳ አምስተኛ ዓመት ሐምሌ 22/2016 ዓ. ም. ተከብሯል። የኅብረቱ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ዕለቱን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር በአፍሪካ ያለች ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአህጉሩ ወንጌልን በመስበክ ትልቅ መሻሻል እንዳሳየች ጠቁመው፣ በአፍሪካ እና በዓለም ላይ ላላት የሲኖዶሳዊ ገጽታ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት በይፋ የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 29/1969 ዓ. ም. ሲሆን ዓላማውም በመላው የአፍሪካ አህጉር እና ደሴቶች መካከል ኅብረትን በመፍጠር በወንጌል አገልግሎት ልዩ ተልዕኮ ላይ ለመተባበር እንደሆነ ይታወቃል።

የጳጳሳቱ ኅብረት ከተመሠረተ ከሁለት ቀናት በኋላ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ ከሐምሌ 31 እስከ ነሐሴ 2/1969 ወደ አፍሪካ አኅጉር ባደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞአቸው በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ ላይ የተካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ስብሰባ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል።

“እናንተ አፍሪካውያን የራሳችሁ ሚሲዮናውያን ናችሁ!"
ሐምሌ 22/2016 ዓ. ም. ተከብሮ ለዋለው 55ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል የተመረጠ መሪ ሃሳብ የተወሰደው ኅብረቱ በተመሠረተበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ “እናንተ አፍሪካውያን የራሳችሁ ሚሲዮናውያን ናችሁ!" በማለት ካሰሙት የማይረሳ ንግግር የተወሰደ እንደሆነ ታውቋል።

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፣ የአፍሪካ እና የማዳጋስካር የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የዘንድሮው ክብረ በዓል በተለይ የኡጋንዳ ሰማዕታት 60ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተከበረ በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ተካፋዮች በሮም በተገኙበት እና የተልዕኮ ቀን መስዋዕተ ቅዳሴ በተፈጸመበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እሑድ ጥቅምት 18/1964 የ22ቱ የዩጋንዳ ሰማዕታት ቅድስና ከታወጀ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ አፍሪካዊት አገር ዩጋንዳን ለመጎብኘት መወሰናቸው ይታወሳል።ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ በማከልም የአፍሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የተከበሩ ቃላት ዘንድሮ ለተመረጠው ጭብጥ ትኩረት መስጥቷን ገልጸዋል።

ንቁ እና ያደገች ቤተ ክርስቲያን
“ከታሪካዊው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተና ሐዋርያዊ ጉብኝት ወዲህ በአፍሪካ ያለች ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በብዙ መልኩ ማደጓን ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ገልጸው፥ በአሁኑ ጊዜ 256 ሚሊዮን ምዕመናን እንዳሏት፣ ከጠቅላላው የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር 18 በመቶው እንደሆኑ እና አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች የምትገኝ፣ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ብዛት ጋር በአፍሪካ የምትገኘው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥር በመስደድ ዛሬ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በመልዕክታቸው በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የስልጣን ተዋረድ ከሰበካ ሆነ ከገዳማውያን አባቶች ከተውጣጡ አገር በቀል ቀሳውስት የተዋቀረ እንደሆነ እና በዓለም አቀፍ ሚሲዮናውያን ማኅበራት ውስጥ በአመራርነት የሚሳተፉ የአፍሪካ ገዳማውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው፥ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የአፍሪካ የሀገረ ስብከት ካህናት ለተወሰነ ጊዜ ከሀገረ ስብከታቸው ወጥተው ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስረድተዋል።

“የሀገረ ስብከቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት መደበኛ የሀገረ ስብከት መዋቅሮችን ማለትም የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎችን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ የጤና ማዕከላትን፣ መንፈሳዊ ተቋማትን፣ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶችን እና የገዳማውያት እና የገዳማውያን ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማቋቋማቸውን አስረድተዋል።

ለሰው ልጅ ዕድገት እና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን
“በአፍሪካ ያለችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጅ ዕድገት በመቆም ቀዳሚ ሥፍራን ይዛለች” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ፥ “አሁን ድምጽ ለሌላቸው ድምፅ በመሆን የአፍሪካን ሕዝብ ኢ-ፍትሃዊ የዕዳ ጫና እንዲቀነስ ወይም አንዲሰረዝ ለማድረግ ትሟገታለች” ብለው፥ የአፍሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እራሷን እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ በጉልህ በማነጽ እና በአፍሪካ እና በደሴቶቹ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መለያ በሆኑት በንዑስ ክርስቲያን ማህበረሰቦች ተሞክሮ እራሷን በማሳደግ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ውስጥ የክርስትና እምነትን ማዳበር
በአፍሪካ ውስጥ የክርስትና እምነትን ማዳበር አስደናቂ ዕድገት ቢሆንም አፍሪካ ኢየሱስ ክርድቶስን መራቧን እና መጠማቷን ቀጥላለች ብለዋል። ለዚህም ነው ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1994 ልዩ የአፍሪካ ጳጳሳት ሲኖዶስ በጠራው መሠረት፣ ከአፍሪካ ሕዝብ መካከል 30% የሚሆኑ ክርስቲያኖች፣ ክርስቲያን ላልሆኑ ሕዝቦች ወንጌልን መስበክ መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የክርስትና እምነትን የማዳበር አስፈላጊነት በድጋሚ ገልጸው፥ “ወንጌልን ማስፋፋት ውጤታማ የሚሆነው የክርስትና እምነት በሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ብቻ ነው” ሲሉ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ አሳስበው፥ “የወንጌል መልዕክት አብረውት ለሚኖሩ ሰዎች እንግዳ ሆኖ ሊቆዩ አይችሉም” ብለዋል።

በግጭት እና በድህነት ለተሰቃየች አፍሪካ የተስፋ ወንጌልን ማምጣት
ከዚህም በላይ አህጉሪቱ ድህነትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን፣ የጎሳ እና የሃይማኖት ግጭቶችን፣ ስደትን እና ጥገኝነትን፣ ሙስናን፣ የአካባቢ መራቆትን፣ የጦር መሣሪያ፣ የአደንዛዥ ዕፅ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በሌሎች በርካታ አሳሳቢ ችግሮች መካከል ክርስቲያኖች አስታራቂ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲያመጡ፣ የሰላም ምንጭ እና የእርቅ ወኪሎች እንዲሆኑ መጠራታቸውን ተናግረው፥ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አባል፣ በመንግሥት የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙት፣ ወይም በምጣኔ ሃብት መስክ የሚሠሩ ክርስቲያኖች ባሉበት ሁሉ የተስፋ ወንጌልን ማወጅ አለባቸው ብለዋል።

ለምዕራቡ ዓለም ወንጌልን መመስከር
ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በመልዕክታቸው በአፍሪካ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተቀረው ዓለም በተለይም ለአውሮፓ አኅጉር ወንጌልን እንድትመሰክር መጠራቷን አሳስበው፣ በአፍሪካ ውስጥ የወንጌል አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት ሚስዮናውያን እንደ ነበሩ አስታውሰው፥ አሁን ግን ዓለማዊው ርዕዮተ ዓለም ብዙዎችን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እያፈናቀለ እንደሚገኝ እና የአገልጋዮች ቁጥርም እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በመልዕክታቸው፥ የሚስዮናዊነት ጥረት ለሲኖዶሳዊ ይዘት ያለውን አስፈላጊነት ገልጸው፥ “በሲኖዶሳዊው ጉዞ የታደሰ እና በኅብረት መንፈስ የተጠናከረ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን በንዑስ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ውስጥ እንደምትገኝ፣ እርስ በርስ በመደማመጥ እና መንፈስ ቅዱስን በማዳመጥ፥ ከአዳዲስ ዘዴዎች እና አወቃቀሮች ጋር ወንጌል ወደ ሕዝቦች ሁሉ እስኪደርስ ድረስ ለመመስከር ተጠርታለች” ሲሉ ተናግረዋል።

“በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት ሁላችንም በቤተ ክርስቲያን የተልዕኮ ሕይወት ንቁ ተሳትፎ አለን ያሉት” ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ፥ ቤተ ክርስቲያን የሰውን መዳን የምሥራች እንድትሰብክ ወደ ምድር ዳርቻ ተልካለች” ብለዋል።

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት እና በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በመጨረሻም፥ በአፍሪካ እና በማዳጋስካር የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በሙሉ ይህን ዓመታዊ ክብረ በዓል በመጠቀም በአህጉሪቱ ላሉ ካቶሊክ ምዕመናን ስለ አፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ህልውና እና ተልእኮ በማሳወቅ እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

30 July 2024, 16:48