ፈልግ

ብጹእ አቡነ ፖል ክዩንግ-ሳንግ ሊ ከቡድናቸው ጋር በደስታ ሲወያዩ   ብጹእ አቡነ ፖል ክዩንግ-ሳንግ ሊ ከቡድናቸው ጋር በደስታ ሲወያዩ  

የሴኡል ሃገረ ስብከት የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የካቴድራሉን ጊቢ ወደ ካምፕ መቀየሩ ተነገረ

የሴኡል ሃገረ ስብከት በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የቤተክርስቲያኑን ወጣት አባላትን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በሜዮንግዶንግ ካቴድራል ጓሮ የሚገኘውን ክፍት ቦታ ወደ ካምፕ ለውጦታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሴኡል የሚከበረው የ 2027 (እ.አ.አ.) የዓለም ወጣቶች ቀን (WYD) የሰበካው አዘጋጅ ኮሚቴ ባዘጋጀው “ካምፕ በካቴድራል” የሚል ዝግጅት ላይ ወደ 600 የሚጠጉ ወጣቶች ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ተሰብስበዋል።

ዝግጅቱ በቤተክርስቲያኒቱ እና በወጣት ተከታዮቿ መካከል የውይይት እና በጋራ ልምድ የዳበረ ድልድይ ለመገንባት ያለመ ነው ተብሏል።

ይህ “አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” (ኢሳይያስ 41:10) በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መርሃ ግብር ቀደም ሲል በካቴድራሉ ይደረጉ ከነበሩ ዝግጅቶች የተለየ እንደነበርም አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በካቴድራሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘውን ክፍት ቦታ ለወጣቶች በሚመች መልኩ እንደ ካምፕ በማዋቀር እና በካህናት፣ በገዳማዊያን እህቶች እና በጎ ፈቃደኞች በተዘጋጁ የካምፕ ወንበሮች ላይ ክብ ሰርተው የተቀመጡ አሥር ቡድኖች በመመስረት ነው ዝግጅቱ የተካሄደው። በዝግጅቱም ላይ ቀለል ያሉ ምግቦች እና ለስላሳ መጠጦች የነበሩ ሲሆን፥ ይህም በወጣቶቹ ዘንድ የመቀራረብን እና እንግዳ ተቀባይነት ስሜትን ለመፍጠር እና ለማጎልበት ታስቦ እንደተደረገም ተነግሯል።

በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ላይ፣ ብዙ ወጣት ተሳታፊዎች ከዚህን በፊት ያልተለመደ ስለሆነ ከጳጳሱ አጠገብ ለመቀመጥ ተጨንቀው እና ተገርመው ነበር፥ ነገር ግን ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ፣ ፍርሃታቸው እየተገፈፈ ትርጉም ያለው ውይይቶችን ሲያካሂዱ ነበር።

በዝግጅቱ ላይ አራት ወጣት ተናጋሪዎች የወቅቱ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማንሳት የእምነት ልምዳቸውን ለሌሎች ያካፈሉ ሲሆን፥ እያንዳንዱ አቀራረብ በሲኖዶሱ የቡድን ውይይት አካሄድ ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ተነግሯል።

የሴኡል ሃገረ ስብከት የወጣቶች ህብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳንግ-ዎክ ሊ ቤተክርስቲያኒቷ ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የምታደርገው ክትትል እና ድጋፍ እየቀነሰ ስለመምጣቱን እና በዚህ ምክንያት በወጣቶቹ ላይ ስለሚያስከትለው መንፈሳዊ ግድየለሽነት ጎላ አድርገው ገልጸዋል።

ሊ ይሄንን በማስመልከት “ወጣቶች የአገልግሎትን ትርጉም እንዲያውቁ ለመርዳት ጥሩ መሪዎች እና ያልተለመዱ አዳዲስ የማህበረሰብ ዝግጅቶች ያስፈልጉናል” ብለዋል።

የሴኡል ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፒተር ሶን-ታይክ ቹንግ ለተሳታፊ ወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት ታሪኮቻቸውን ለማካፈል ላሳዩት ታማኝነት እና ፈቃደኝነት ምስጋናቸውን ገልጸው፥ “የህይወት ታሪኮቻችሁን በመስማታችን በጣም ደስተኞች ነበርን። ወጣቶቹ ላሳለፉት ጠቃሚ ጊዜ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፥ ከአሁን በኋላም የተለያዩ ስብሰባዎችን ማዘጋጀታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ብጹእነታቸው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን አባባል በማስታወስ “ምንም ብናከናውን ወይም ማንንም ብንሆን፣ እግዚአብሔር እንደ እኛነታችን ይወደናል" ካሉ በኋላ "ለመጪው የዓለም የወጣቶች ቀን የዝግጅት ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር በደስታችሁ፣ በሀዘናችሁ እና በህመማችሁ ጊዜያት ከእናንተ ጋር ይሁን” በማለትም ወጣቶቹን በመባረክ አበረታተዋል።

የሰበካው አዘጋጅ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ላይ ሊቀ ጳጳስ ቹንግ የወጣቶችን ድምጽ ለመስማት ያደረጉትን ትጋት እንደሚያደንቅ ከገለጸ በኋላ፥ “የካቴድራል ካምፕ” ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ይህንን ራዕይ በማሳየት በቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና በወደፊት መጋቢዎቿ መካከል ልዩ የሆነ የውይይት መድረክ አመቻችቷል” በማለት ገልጿል። 

ባለፈው ዓመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሴኦል የ2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን እንደምታስተናግድ መግለፃቸው ይታወሳል። በምላሹም ሊቀ ጳጳስ ቹንግ በተለያዩ ባህሎች እና ሀይማኖቶች ውስጥ “ወንድማማችነትን፣ መንፈሳዊነትን እና ማህበራዊ ትስስርን” የሚያበረታታ ክስተት ለመፍጠር ቁርጠኛ ሆነው እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
 

02 July 2024, 14:25