ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር የሚያደርጉት ጉብኝት የማኅበራዊ ለውጥ ውይይት እንደሚያቀጣጥል ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አገሪቱ አርባ ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማስተናገድ በምትዘጋጅበት ወቅት በእምነት እና በሕዝብ ፖሊሲ መካከል የሚደረገው ውይይት መጠናከሩ ተነግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአካባቢው የካቶሊክ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በሰፊው ህብረተሰብ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ማለትም በማህበራዊ ፍትህ፣ በቤተሰብ እሴቶች እና ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ማኅበራዊ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይነገራል።
ሃይማኖታዊ እሴቶችን ከፖለቲካዊ ሥራቸው ጋር በማዋሃድ የሚታወቁት አቶ ያም፥ የእያንዳንዱን ግለሰብ ክብር ማስጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን፥ “ካቶሊኮች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም የተፈጠርነው በእግዚአብሔር አምሳል በመሆኑ የማንኛውም ሰው ሕይወት፣ አመለካከት ወይም የፆታ ዝንባሌ ምንም ይሁን ምን የእያንዳንዱን ሰው ክብር ለመጠበቅ ተጠርተናል” ብለዋል።
የአቶ ያም መልዕክት ያስተጋባው በሲንጋፖር የፍቺ መጠን በጨመረበት እና የወሊድ መጠን ባሽቆለቆለበት፣ ባህላዊ የቤተሰብ አወቃቀሮች ፈተና ውስጥ በወደቁበት ወቅት እንደሆነ ሲነገር፥ አቶ ያም መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የቤተ ክርስቲያን አቋም የሆኑትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ “የወንጌል ደስታ” እና “ፍቅር በቤተሰብ” የሚሉ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸውን በመጥቀስ ነው።
የጋብቻ እና የፆታ ቅድስና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠብቀው ያቆዩት ባሕላዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደሆነ አቶ አሌክስ ገልጸው፥ የቤተሰብ ሕይወትን የሚያጠናክሩ፣ ጤናማ ግንኙነቶችን የሚያበረታቱ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ የሚሆኑ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።
ሁሉን አቀፍ ሥርዓትን በመደገፍ ሰብዓዊ እሴቶችን፣ አንድነትን እና ልዩነትን ለሚያከብር፣ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እና መንፈሳዊ ዕድገትን ለሚያጎለብት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ አቀራረብ አፅንዖት የሰጡት አቶ ያም፥ “ይህም በኅብረተሰባችን እና በኢኮኖሚያችን ውስጥ የሚታዩ ልዩነቶችን ለመቀበል እና ለማሳደግ እንደሚያስችል፥ በተራውም የበለጠ ጠንካራ የሰው ኃይል ይገነባል” ብለው፥ በኢኮኖሚ ልዩነቶች ላይ የበለጠ ፍትሃዊ ህብረተሰብን ለማፍራት ያለመ ፖሊሲዎችን በመደገፍ ለድሆች በሚቀርቡ አማራጮች ላይ ለሚደረግ ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥቷል።
“በሲንጋፖር ውስጥ ያለው አስከፊ ድህነት ሌላ ቦታ ካለው ያነሰ ልምድ ቢኖረውም፣ በሀብታሞች እና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት መስፋፋቱ አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ነው” በማለት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የፍቅር፣ የፍትህ እና የአብሮነት ራዕይ ጠቅሰዋል።
“የቅዱስነታቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት ዘይቤ እኛ ምዕመናን የኅብረተሰቡን ፍትህ አልባነት ለመቅረፍ፣ ከማኅበረሰቡ የተገለሉትን ለመደገፍ እና ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን፣ የማኅበረሰባችን እና የአገራችን ማዕከል በማድረግ ውይይትን እና እርቅን ለማበረታታት ይደግፈናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አሌክስ ያም እንደ ካቶሊክ የፓርላማ አባልነታቸው፥ ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከልዩ ልዩ ማኅበራዊ ዘርፎች መሪዎች ጋር በየዕለቱ በመተባበር እምነታቸውን እንደሚያሳድጉ፣ ተስፋቸውም በኅብረት በመጓዝ፣ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት በመመራት ወንጌላዊ እና ሚስዮናዊ ቤተ ክርስቲያን በመሆን ለሁሉም ሰው የበለጠ ፍትሃዊ እና ሩህሩህ ዓለምን መገንባት እንደሆነ ከሲንጋፖር ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረዋል።