ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር  

ታሊታ ኩም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ላይ የተሰማራው ታሊታ ኩም የተሰኘ የገዳማዊያት ኅብረት የወንጀሉ ተጎጂዎችን ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል። ኅብረቱ ጥያቄውን ያቀረበው፥ “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት በሚደረግ ጥረት ላይ ሕጻናትን ወደ ጎን አንበል” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 23/2016 ዓ. ም. በተከበረው ዓለም አቀፍ ቀን እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ አስተባባሪ እህት አቢ አቬሊኖ፥ ዕለቱን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ለመጠበቅ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን በየዓመቱ ሐምሌ 23 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ቀንን ታሊታ ኩም የገዳማዊያት ኅብረትም አክብሯል።

በሕጻናት ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ደኅንነት በመጠበቅ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ እንዳይሆኑ ጥሪያቸውን ያቀረቡት እህት አቬሊኖ፥ በባህላዊ ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠን ምክንያት በተለይ ሕጻናት እና ሴቶች ለወንጀል እና ለብዝበዛ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። በብዙ የዓለም ክፍሎች በተለይም በድህነት ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ አሳዛኝ ክስተቶች አስመልክቶ መረጃ እንዳላቸው እህት አቬሊኖ አክለው ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (ILO) ባወጣው ዘገባ መሠረት ከአምስት እስከ 17 አመት ዕድሜ ያላቸው 152 ሚሊዮን ህጻናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ እንደሚሆኑ ገልጾ፥ በዓለም ውስጥ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከሚጠቁት ሦስቱ መካከል አንዱ በህጻንነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል መከላከያ ጽሕፈት ቤት (UNODC) በሪፖርቱ አመልክቷል። ከዚህ የተለዩ የጥቃት ዓይነቶች የጉልበት ብዝበዛ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ሕገወጥ የጉዲፈቻ ዝውውር፣ ወሲባዊ ብዝበዛ እና የኢንተርኔት ላይ ጥቃቶ እንደሆኑ ጽሕፈት ቤቱ አክሎ አመልክቷል።

በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ጦርነቶች እና ሌሎች ቀጣይ ግጭቶች ሕጻናት ላይ በተለያዩ ደረጃዎች የመጎሳቆል አደጋዎችን ያስከተለ ሲሆን፥ በተለይ ከህጻናት መንከባከቢያ ማዕከላት የተፈናቀሉትን ጨምሮ ከወላጅ ቤተሰቦቻቸው የተለዩ ሕጻናት ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል። ሌላው አዝማሚያ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2023 የግሎባል ባርነት ኢንዴክስ ዘገባ መሠረት ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ወላጅ አልባ ሕጻናትን ለትርፍ እና ለብዝበዛ እንዲመቻቸው ወደ እንክብካቤ ማዕከላት እንደሚመለምሏቸው፣ በኢንተርኔት ላይ ለወሲባዊ ብዝበዛ ማስታወቂያነት እና ለሽያጭ ቴክኖሎጂዎችን እና ድረገጾችን እንደሚጠቀሙ አስታውቋል።

በዚህ አውድ ህገወጥ ዝውውርን በመከላከል እና በመዋጋት ረገድ አዳዲስ ፈተናዎች ያጋጠሙ ሲሆን፥ በተለይም በቴክኖሎጂ እና በመስመር ላይ የክትትል መድረኮች የሰዎችን ህገወጥ ዝውውርን በመዋጋት ረገድ ልምድ ካላቸው የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች ጋር ትብብር እንደሚያስፈል ተገልጿል። ይበልጥ ለወንጀሉ ተጋላጭ የሆኑትን ከጉዳት ለመከላከል በተለይም ሕጻናትን ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ እና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሕጻናት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ መረብ አስተባባሪ እህት አቬሊኖ በመልዕክታቸው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓይኖቻችንን እና ጆሮቻችንን እንድንከፍት ያበረታቱናል” ብለው፥ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ “በጦርነት እና በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱትን፣ ለስደት የተገደዱትን እና በተለይም ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች እና በሥራ ገበታ የሚበዘብዙ ልጆች ለዕርዳታ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምተን መርዳት ምኞታችን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በታሊታ ኩም ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ አማካይነት የሚገኙ ገዳማውያት እና ወጣት አምባሳደሮች፣ የተለያዩ ተግባራትን በመጠቀም ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ዝግጅቶችን እና ዘመቻዎችን እንደሚያዘጋጁ የገለጹት እህት አቬሊኖ፥ ታሊታ ኩም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ቁርጠኛ የሆነ የገዳማውያት እና የምእመናን ዓለም አቀፍ መረብ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህንን ክስተት ለመከላከል በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ዓላማቸውም አቅመ ደካማ የሆኑ ወጣቶችን ማስተማር እና ስለ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤን ማሳደግ፥ በተለይም ሴቶችን እና ልጃገረዶችን፣ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና በሕገ-ወጥ ለወንጀሉ እና ለብዝበዛ የተጋለጡ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ገልጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ዓ. ም. 623,700 አባላት በመከላከል ጥረቱ ውስጥ መሳተፋቸውን አስረድተዋል።

በሕ-ገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ያለውን አሳሳቢ አዝማሚያ እና ዕድገት ስንመለከት፥ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትኩረት ለማሰባሰብ እንደሚሞክሩ የገለጹት እህት አቬሊኖ፥ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በግንቦት ወር በተካሄደው የታሊታ ኩም ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት አባላት የሰጡትን ምስክርነት በማኅበራዊ ሚዲያቸው አማካይነት ሲያካፍሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሌለበትን ዓለም ለመገንባት እናልማለን ያሉት እህት አቬሊኖ፥ ይህም ሁሉንም የኅብረተሰብ፣ የመንግሥት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንዲሁም እያንዳንዳችንን የሚያሳትፍ ጥሪ እንደሆነ ገልጸው፥ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑትን በተለይም ሕጻናትን ከብዝበዛ መጠበቅ እና በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑ ሕጻናትን መደገፍ እንደሚገባ አሳስበው፥ ሁላችንም የተስፋ አምባሳደሮች እንድንሆን ተጠርተናል ሲሉ አስረድተዋል። ተግባሮቻቸው በኅብረት እና በርህራሄ ሕይወትን መቀየር እና ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የፀዳ ዓለምን መፍጠር መሆኑን የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ መረብ አስተባባሪ እህት አቬሊኖ በመልዕክታቸው አስረድተዋል።

 

31 July 2024, 15:03