ፈልግ

አባ ኢቫን ሌቪስኪ እና ቦህዳን ሄሌታ አባ ኢቫን ሌቪስኪ እና ቦህዳን ሄሌታ 

ፕረዚዳንት ዘለንስኪ ቅድስት መንበር 2 ካህናት እንዲፈቱ ላደረገችው አስተዋጽዖ ማመስገናቸው ተነገረ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ በሩስያ ሃይሎች ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሁለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሆሊ ረዲመር ጉባኤ አባላት የሆኑት አባ ኢቫን ሌቪስኪ እና አባ ቦህዳን ሄሌታን ጨምሮ አስር የዩክሬን እስረኞችን እንዲፈቱ “የላቀ አስተዋጽዖ” ላደረጉት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ለቫቲካን ዲፕሎማሲ ቡድን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሆሊ ረዲመር ወይም የቅድስተ ቅዱሳን አዳኝ (ቤዛውያን) ጉባኤ አባል የሆኑት እነዚህ ካህናት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እስረኛ ስትለዋወጥ ከፈታቻቸው አሥር ግለሰቦች መካከል ናቸው። ሁለቱ ካህናት የታሰሩት ህዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን ለረጅም ጊዜ የት እንዳሉ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በኤክስ (ትዊተር) ገፃቸው ላይ አስሩ ሰዎች የመፈታታቸውን ዜና ሲያበስሩ ባሰፈሩት ጽሁፍ “እስረኞቹን ለማስፈታት ሲሰራ የነበረውን ቡድናችንን ጨምሮ የረዱትን ሁሉ አመሰግናለሁ። በተለይ እነዚህ ሰዎች ወደ ቤት በሰላም እንዲመለሱ ቅድስት መንበር ላደረገችው ከፍተኛ አስተዋጽዖ እና ጥረት እውቅና መስጠት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ሁለቱ የጉባኤው አባላት በሩሲያ በተያዙ ግዛቶች ውስጥ ነበሩ

በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ እና መሪ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ ከፕረዚዳንት ዘለንስኪ ጋር ተመሳሳይ አስተያየቶችን ያስተላለፉ ሲሆን፥ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ ብፁዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና መላው የቫቲካን የዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት አመስግነዋል። ብጹእነታችው በተጨማሪም ሁለቱ የሃይማኖት አባቶች እንዲፈቱ ደጋግመው ሲጠይቁ ለነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ዙፒን እና በዩክሬን ለሚገኙት ሐዋርያዊት ሊቀ ጳጳስ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።

በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው እስረኞቹ ነፃ እንዲወጡ ለማድረግ እያንዳንዳቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል በማለት ጠቅሷል።

መግለጫው በተጨማሪም ሁለቱ አባቶች በጊዜያዊነት በሩሲያ በተያዙ ግዛቶች ውስጥ ያሉ ማኅበረሰባቸው ጋር ለመቆየት እንደወሰኑ እና ወደ ፊትም በሥፍራው የሚገኙትን ሁለቱንም የግሪክ ካቶሊክ እና የሮማ ካቶሊክ ማህበረሰቦችን እንደሚያገለግሉ ጠቅሷል።

ሁለቱ ካህናት የተያዙት የጦር መሳሪያ አላቸው በሚል ሀሰተኛ ክስ ሲሆን፥ ሜጀር ሊቀ ጳጳስ ስቪያቶስላቭ ሁለቱ ካህናት በህይወት እንዳሉ ማረጋገጫ ያገኙት በቅርቡ እንደሆነም ተጠቅሷል።
 

01 July 2024, 15:57