ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ የፍቅር ወሲባዊ ገጽታ

ይህ ሁሉ ወደ ጋብቻ ወሲባዊ ገጽታ ያመጣናል። እግዚአብሔር ራሱ ለፍጥረታቱ የሰጠው ታላቅ ስጦታ የሆነውን ወሲባዊነት ፈጠረ። ይህ ስጦታ መዳበርና አቅጣጫ መያዝ ካለበት ‹‹እውነተኛ እሴቱን ከማደኸየት›› መከላከል ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ‹‹የሰውን ወሲባዊ እሴት ይቃወማል›› ወይም ቤተክርስቲያን ወሲባዊነትን የምትታገሰው ‹‹ለተዋልዶ አስፈላጊ ስለሆነ ብቻ ነው›› የሚለውን አባባል አልተቀበሉትም። ወሲባዊ ፍላጎት የሚናቅ ነገር አይደለም፤ ‹‹አስፈላጊነቱንም የሚያስጠረጥር አንዳችም ጥረት የለም››።

ጥልቅ ስሜቶችንና ወሲባዊነት ዙሪያ ሥልጠና መውሰድ ስሜታዊና ወሲባዊ ፍቅርን ይቀንሳል ብለው ለሚፈሩ ሰዎች ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምላሽ ሲሰጡ፣ ሰዎች ‹‹በግንኙነቶቻቸው ውስጥ ሙሉና የዳበረ ግኑኝነት እንዲኖራቸው ተጠርተዋል››፤ ይህም ግኑኝነት የራስን የልብ ትርታዎች ለይቶ የማወቅ ፍሬ ነው›› ብለዋል። ይህም እያንዳንዱ ሰው ‹‹ በጽናትና በkሚነት የራሱን አካል ምንነት ማወቅ እንዳለበት›› እንዲሁም ሥነ ሥርዓት መያዝና ራስን መግዛት እንደሚገባው ያስገነዝባል። ወሲባዊነት የተራክቦ ወይም የመዝናኛ መንገድ ሳይሆን፣ ሌላውን ሰው በቅዱስነቱና በማይገሰስ ክብሩ የሚቀበሉበት የእርስ በርስ መግባቢያ ክንውን ነው። በመሆኑም፣ ‹‹ የሰው ልብ በሌላ ዐይነት ግኑኝነት ይሳተፋል ማለት ይቻላል››።

በዚህ አገባብ፣ ወሲባዊ ፍላጎት በተለይ ሰው ወሲባዊነትን የሚገልጽበት መንገድ መስሎ ይታያል። ወሲባዊ ፍላጎት ‹‹የአካልን የጋብቻ ትርጉምና የዚያን ስጦታ እውነተኛ ክብር›› እንድናውቅ ያደርገናል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ አካል ነገረ መለኮት በሰጡት መንፈሳዊ ትምህርት እንዳስገነዘቡት፣ የጾታ ልዩነት ‹‹የመተማመንና የተዋልዶ ምንጭ›› ብቻ ሳይሆን፣ ሰው ስጦታ የሚሆንበትን ፍቅር የመግለጽ ችሎታ›› ያለው ነው። ጤናማ ወሲባዊ ፍላጎት፣ ከተራክቦ ፍለጋ ጋር በቅርበት የተገናኘ ቢሆንም፣ ሁልጊዜ ድንቅ የሆነ ስሜትን ያካተተና ከዚህም የተነሣ ስሜቶችን ሰብአዊ ለማድረግ የሚችል ነው።

ስለዚህ፣ የፍቅርን ወሲባዊ ገጽታ ተቀባይነት እንዳለው መጥፎ ነገር ወይም ስለ ቤተሰብ ጥቅም ሲባል ሊታገሡት የሚገባ ሸክም አድርገን መገመት የምንችልበት መንገድ የለም። ይልቁንም የባልና ሚስትን ፍቅር እንደሚያዳብር የእግዚአብሔር ስጦታ ተደርጎ መታየት አለበት። የሌላውን ሰው ክብር በሚጠብቅ ፍቅር የተሞላ ስሜት እንደመሆኑ፣ የሰው ልጅ ሊይዘው የሚችለውን ድንቃ ድንቆች የሚገልጽ ‹‹ንጹሕና ያልተበረዘ ማረጋገጫ›› ይሆናል። በዚህ ዐይነት፣ ለጊዜውም ቢሆን፣ ‹‹ሕይወት በጎና አስደሳች እንደ ሆነ ››ይሰማናል።

ብጥብጥና ማታለል
በዚህ አዎንታዊ የወሲብ እይታ ላይ ተመሥርተን አጠቃላይ ርእሰ ጉዳዩን በጤናማ እውነታ መቅረብ እንችላለን። ወሲብ አብዛኛውን ጊዜ ወራዳና ጤና ቢስ ይሆናል፤ ከዚሀም የተነሣ ‹‹አልፎ አልፎ በራስ የመመካትና የግል ምኞቶችንና የተፈጥሮ ባሕርያትን ለግል እርካታ የማዋያ መሣሪያ ይሆናል››። በዘመናችን፣ ወሲባዊነት ‹‹ተጠቅመህ ጣል›› በሚል አስተሳሰብ ተመርዞአል። የሌላው ሰው አካል ብዙውን ጊዜ እርካታን እስከሰጠ ድረስ ሊገለገሉበት እንደሚገባ፣ አገልግሎቱ ሲያበቃ ደግሞ እንደሚጣል ዕቃ ይታያል። ነገሩ እንዲህ ከሆነ፣ ስለ ወሲባዊነት ያለው የተተበተበ ግንዛቤ ውጤት የሆኑ የበላይነትን፣ ትዕቢትን፣ ስድብን፣ የተጣመመ ወሲባዊ አስተሳሰብንና ሁከትን እያየን በእውነት ችላ ማለት ወይም ጉዳዩን አሳንሰን ማየት እንችላለን? ወይስ የሌሎች ክብርና የራሳችን የመውደድ ሰብአዊ ጥሪ እንዲህ ‹‹ ራስን ከማግኘት›› ድብቅ ፍላጎት አንሶ መቅረት ይኖርበታል?

በራሱ በጋብቻ ውስጥ፣ ወሲብ የሥቃይና የማታለያ ምንጭ እንደሚሆን እናውቃለን። ስለዚህ፣ ‹‹የእርሱ ወይም የእርስዋ ሁኔታ ወይም በዚህ ጉዳይ ላይ የግልና አግባብነት ያለው ምኞት ሳይታይ፣ በሌላ የትዳር ጓደኛ ላይ የግዴታ ወሲብ መፈጸም እውነተኛ የፍቅር ሥራ አይደለም፤ በተለይ በባልና ሚስት የቅርብ ግንኙነት ውስጥ እንዲህ ዐይነቱን ድርጊት መፈጸም ግብረ ገብን መጣስ ነው››። ለባልና ሚስት ወሲባዊ አንድነት ተገቢ የሆኑ ድርጊቶች ‹‹እውነትም ሰብአዊ በሆነ መንገድ›› ሲፈጸሙ፣ እግዚአብሔር ከፈቀደው ወሲባዊ ባህርይ ጋር ይጣጣማሉ። ቅዱስ ጳውሎስ አበክሮ ሲናገር ፡- ‹‹በዚህ ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን ወይም እህቱን አያታልል›› (1 ተሰ. 4፡6) ይላል። ጳውሎስ ይህን የተናገረው ሴቶች ሙሉ በሙሉ የወንድ የበታች ተደርገው ከሚቆጠሩበት አባታዊ ባህል አንጻር ቢሆንም፣ ወሲብ በሁለቱም ጥንዶች መካከል መግባባትን እንደሚያካትት አስተማረ። ከዚህም አኳያ ለተወሰነ ጊዜ፣ ነገር ግን ‹‹በስምምነት›› (1 ቆሮ. 7፡5) ወሲባዊ ግንኙነትን የማዘግየት ሁኔታንም ያነሣል።

ባለትዳሮች ‹‹ያለመረጋጋት ሥጋት›› (ሊገጥማቸው እንደሚችል ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስጠንቅቀዋል። በሌላ አነጋገር፣ ባልና ሚስት የተጠሩት ይበልጥ ሥር ለሰደደ አንድነት ቢሆንም፣ በሁለታቸው መካከል ያሉትን ልዩነቶችንና ተገቢ ርቀት የመደበቅ ሥጋት አለ። ምክንያቱም ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ ተገቢና የማይጣስ ክብር አላቸው። አንዱ የሌላው መሆናቸው ቀርቶ አንዱ የበላይ ሲሆን፣ ‹‹የእርስ በርስ መካከል ያለው የአንድነት መዋቅር ከመሠረቱ ይቀየራል››። የበላይነት የሚሰማቸው ሰዎች የራሳቸውን ክብር ወደሚቃረኑበት ደረጃ የሚደርሱት በዚህ የበላይነት አስተሳሰብ ነው። በመጨረሻም፣ ‹‹ከራሳቸው አካል ጋር ራሳቸውን ማመሳሰል›› አይችሉም፤ ምክንያቱም ጥልቅ ትርጉሙን ያጡታል። ወሲብን የማምለጫ መንገድ አድርገው ስለሚጠቀሙበት የወሲባዊ አንድነትን ውበት ይክዱታል።

ማንኛውም የጾታ የበታችነት በግልጽ መወገድ አለበት። ይህም ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት ሴቶች ‹‹ለባሎቻችሁ ተገዙ›› (ኤፌ. 5፡22) የሚለውን ምንባብ ያለ አግባብ መተርጎምን ያካትታል። ይህ ምንባብ በዘመኑ የነበሩ ባህላዊ ፈርጆችን የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ የእኛ ሥጋት የዚህ ባህላዊ ቅንብር ሳይሆን ባህሉ የሚያስተላልፈው ግልጽ መልእክት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አበክረው እንደገለጹት፣ ‹‹ፍቅር ሚስት የወንድ አገልጋይ ወይም ባሪያ የምትሆንበትን ማናቸውንም ዐይነት የበታችነት ያስወግዳል… በጋብቻ አማካይነት የሚመሠርቱት ሱታፌ ወይም አንድነት ራስን ለእርስ በርስ መሰጣጣትን ያካተተ መሆኑ፣ አንዱ ለአንዱ መገዛትም ነው››። ስለዚህ፣ ጳውሎስ አያይዞ ሲናገር ፣‹‹ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል›› (ኤፌ. 5፡ 28) ይላል። ይህ ‹‹አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ›› (ኤፌ. 5፡ 21) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመሠረቱ ማንኛውንም ሰው በራስ የመደሰትን ግለኝነት እንዲያስወግድና ሁልጊዜም ስለ ሌሎች ማሰብ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። በጋብቻ ውስጥ ይህ የጋራ ‹‹ተገዥነት›› ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፤ በመተማመን፣ በመከባበርና በእንክብካቤ የሚገለጽ አንዱ ራሱን ለሌላው በነጻነት እንደ መስጠት የሚቆጠር ነው። ወሲባዊነት ያለ አንዳች ልዩነት ይህን የጋብቻ ወዳጅነት የሚሰጥ ሲሆን፣ ዓላማውም ሌላውን ምሉእ ለማድረግ ነው።

እንደዚሁም ወሲባዊነትንና ወሲባዊ ተራክቦን እንዳይጣመሙ መከላከል፣ ራሱን ወሲባዊነትንና ወሲባዊ ፍቅርን ወደ ማንኳሰስ ወይም ችላ ወደ ማለት ሊያመራን አይገባም። የጋብቻ ዓላማ እያንዳንዱ የትዳር አጋር የግል ፍላጎቶችን ሁሉ ትቶና የግል እርካታ ሳያሳስበው የሌላውን በጎ በመሻት ራስን ለሌላው በመሥዋዕትነትና በለጋስነት የሚሰጥበት ሁኔታ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። እውነተኛ ፍቅር ሌላውን ለመቀበል፣ የራስን ደካማነትና ፍላጎቶች አምኖ ለመቀበልና በመተሻሸት፣ በመተቃቀፍ፣ በመሳሳምና በወሲባዊ አንድነት ውስጥ የሚገኙ አካላዊ መገለጫዎችን በሐቅና በደስታ ለመቀበል መቻልን እንደሚጠይቅ ማስታወስ ያስፈልገናል። ቤነድክቶስ 16ኛ ይህንኑ በግልጽ ሲናገሩ፣- ‹‹ሰው ፍጹም መንፈስ ለመሆንና ከእንስሳዊ የተፈጥሮ ባሕርዩ ጋር የተያያዘ ሥጋን ለመካድ ቢመኝ፣ መንፈስም ሥጋም ሁለቱም ክብራቸውን ያጣሉ››። በዚህ ምክንያት ‹‹ሰው መሥዋዕትነትን በሚጠይቅና ተላላፊ ፍቅር ብቻ ሊኖር አይችልም። ሁልጊዜ መስጠት አይችልም፣ መቀበልም አለበት። ፍቅርን ለመቀበል የሚፈልግ ፍቅርን መስጠት ይኖርበታል››። አሁንም ቢሆን ሰብአዊ ሚዛናችን ደካማ መሆኑን ከቶ አንርሳ። እውነተኛ ሰብአዊ እድገትን የማይቀበል ክፍል ስላለን፣ በማናቸውም ወቅት የቆየ የራስ ወዳድነት ዝንባሌን ሊቀሰቅስ ይችላል።

ምንጭ፥ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 149-157 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ ዳንኤል ኃይለ
 

10 August 2024, 16:22