የአይርላንድ ጳጳሳት በጎልዌይ በአንድ ካኅን ላይ በደረሰ ጥቃት የተሰማቸውን ድንጋጤ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአየርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጎልዌይ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ሠፈር ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ አባ ፖል መርፊ በ16 ዓመቱ ታዳጊ ሐሙስ ነሐሴ 9/2016 ዓ. ም. በጩቤ መወጋታቸው እንዳስደነጣቸው ገልጸዋል።
የ50 ዓመቱ ካህን አባ ፖል መርፊ በአቅራቢያው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ተወስደው የመጀመሪያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ በአካባቢው ወደሚገኝ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና ዕርዳታ ያገኙ ሲሆን፥ ጉዳቱ ከባድ ቢሆንም ለሕይወት የሚያሰጋ እንዳልሆነ ተገልጿል።
ጉዳቱን ፈጻሚው የ16 ዓመት ታዳጊ በጸጥታ ኃይሎች ወዲያው ተይዞ ድርጊቱ የሽብር ጥቃት ከሆነ በሚል የማጣራት ሂደት እየተካደበት እንደሚገኝ ታውቋል። የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሞን ሃሪስ ድርጊቱን “አስደንጋጭ” ሲሉ ገልጸው፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ፖሊስ ላደረገው ፈጣን እርምጃ እና ምላሽ አመስግነዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ ለአባ መርፊ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል
የአየርላንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጥቃቱ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ለተጎጂው ካኅን ሙሉ ጤናን ተመኝተውላቸዋል።
የጎልዌይ ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዱዪግናን ዓርብ ነሐሴ 10/2016 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፥ “ዜናው እጅግ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነው” ብለው፥ “አባ መርፊ ከደረሰባቸው አደጋ ሙሉ በሙሉ እንዲያገግሙ፥ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሠራዊቱ አባላት እና በዚህ ወቅት የሕክምና ዕርዳታ በማድረግ ላይ ለሚገኙት የሕክምና ባለሙያዎች እጸልያለሁ” ብለዋል።
ለጸሎት እና ለይቅርታ የቀረበ ጥሪ
የዋተርፎርድ እና የሊስሞር ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አልፎንሰስ ኩሊናን በመግለጫቸው፥ ጥቃቱን በጥብቅ አውግዘው፥ ምዕመናን በሙሉ አባ መርፊን እና በድርጊቱ ተጠያቂ ለሚሆነው ግለሰብ ይቅርታን በማድረግ በጸሎታቸውም እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።
“የተጎዱትን ካኅን መደገፍ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች እንደገና እንዳይከሰቱ ለማድረግ መተባበር አለብን” ብለዋል። አስተዳደጋቸው ወይም እምነታቸው ምንም ይሁን ምን በሁሉም ዘንድ ሰላምን፣ መግባባትን እና መከባበርን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ መወያየት እንደሚገባ ያሳሰቡት ብጹዕ አቡነ አልፎንሰስ፥ በጸሎት መሰባሰብ እና ይቅር ባይነት ወደ እርቅ ሊመራን የሚችል ኃይለኛ መሣሪያ ነው” በማለት አስታውሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አባ መርፊ ዓርብ ነሐሴ 10/2016 ዓ. ም. በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ደጋፊዎችን በሙሉ ለጸሎታቸው፣ ለፍቅራቸው እና ለአሳቢነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።