ፈልግ

አንድ ፓኪስታናዊ ክርስቲያን ወጣት ለብጹእ ካርዲናል ጆሴፍ ኮውትስ በካራቺ ቅዱስ ፓትሪክ ቤተክርስቲያን የአበባ ጉንጉን ሲያጠልቅላቸው - ሃምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ ፓኪስታናዊ ክርስቲያን ወጣት ለብጹእ ካርዲናል ጆሴፍ ኮውትስ በካራቺ ቅዱስ ፓትሪክ ቤተክርስቲያን የአበባ ጉንጉን ሲያጠልቅላቸው - ሃምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.  

ብጹእ ካርዲናል ኮውትስ በፓኪስታን በሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ሰላምን በማበረታታት ተሸለሙ

በፓኪስታን የካራቺ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ጆሴፍ ኮውትስ በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ሰላም ለመፍጠር ላደረጉት ጥረት የፓኪስታንን ‘ታምግሃ-ኢ- ኢሚቲያዝ’ (Tamgha-i-Imtiaz) የተባለውን ሽልማት ተቀብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በፓኪስታን መንግስት የሚዘጋጀው ይህ ትልቅ የክብር ሽልማት በፓኪስታን ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሲቪል ባስመዘገበው ስኬት መሰረት የሚሰጥ ሲሆን፥ ሽልማቱ ለሲቪል ወይም ለወታደራዊ አካላት እንደሚሰጥ ይታወቃል።

የፓኪስታን ፕሬዝዳንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ የካራቺ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ ካርዲናል ጆሴፍ ኮውትስን ይሄንን የክብር ሽልማት የሆነውን የታምግሃ ሽልማትን በሀገሪቱ 78ኛው የነፃነት ቀን ክብረ በዓል ላይ ሸልመዋል።

‘ፓክ ኒውስ’ የተባለው የፓኪስታን ሚዲያ ነሃሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደዘገበው፣ ይህ ለ104 ግለሰቦች የተሰጠው ሽልማት ለአገሪቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና የተሰጠበት ሥነ ሥርዓት አካል ነው በማለት ገልጿል።

የታምግሃ ሽልማት በፓኪስታን ውስጥ ለሚኖር ማንኛውም ሲቪል ለሀገር ላደረገው ልዩ አስተዋፅዖ እውቅና ይሰጣል ያለው ዘገባው፥ ለፓኪስታን ታላቅ አገልግሎት ላበረከቱ የውጭ ዜጎችም ሊሰጥ ይችላል በማለት አብራርቷል።

ብጹእ ካርዲናል ኮውትስ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች መካከል ውይይትን በማጎልበት እና ማህበራዊ ደህንነትን እና አናሳ ማህበረሰብ መብቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ላደረጉት ጥረት እውቅና ያገኙ ሲሆን፥ የብጹእነታችው ተነሳሽነቶች በመላው ፓኪስታን የጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት እና የማህበረሰብ ደህንነትን ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል።

ፕሬዘዳንት ዛርዳሪ በመርሃ ግብሩ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በሃይማኖቶች መካከል መስማማትን ለመፍጠር ካርዲናል ኮውትስ ላበረከቱት አስተዋፅዖ ከልብ በማመስገን፥ “ለሰብአዊነት ያላቸው አገልግሎት እና የተለያዩ እምነቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ የተጫወቱት ሚና ለመላው የፓኪስታን ህዝብ መነሳሳትን ይፈጥራል” በማለት ፕሬዝዳንቱ ብጹእ ካርዲናል በሀገሪቱ ሰላም እና ብልጽግና ላይ ያላቸውን ተጽእኖ አጉልተው ገልጸዋል።

የሽልማት ሥነ ስርዓቱ ለመጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የታቀደ ሲሆን፥ ከሌሎች የክብር ተሸላሚዎች መካከል የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊው አርሻድ ናዲም እና ሟቹ የተራራ መውጣት ስፖርተኛ ሙራድ ሳድፓራ ለስፖርቱ ላበረከተው አስተዋፅኦ የሲታራ-ኢ-ኢምቲያዝ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
 

21 August 2024, 14:16