ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ በሪሚኒ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጉባኤ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ በሪሚኒ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጉባኤ ላይ   (ANSA)

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ ዛሬ ሰላምን ማምጣት ከባድ ቢሆንም ተኩስ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳሰቡ

በጣሊያን ሪሚኒ ከተማ በመካሄድ ላይ ከሚገኘው ጉባኤ መክፈቻ ቀደም ብለው በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በቅድስት ሀገር ሰዎች ራሳቸውን ለአመፅ አሳልፈው እንዳይሰጡ የሚያደርጉ አንዳንድ ተስፋዎች መኖራቸውን ተናግረው፥ ዛሬ በቅድስት ሀገር ሰላምን ማምጣት ከባድ ቢሆንም ነገር ግን በአስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በአሁኑ ጊዜ ስለ ሰላም ማውራት አንችልም” ያሉት በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ በቅድስት ሀገር በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ከአሥር ወራት በላይ የዘለቀው ግጭት አሁን ያለበትን ሁኔታ በግልፅ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ “ለሰላም መኖር” በሚል ርዕሥ በሪሚኒ ከተማ የተዘጋጀውን ስብሰባ ከመክፈታቸው ቀድም ብለው ለቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ባደረጉት ንግግር፥ “የተኩስ ማቆም ሥራን መሥራት እና የፈውስ ሂደትን ለመጀመር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በማገድ እርስ በርስ መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።


“ወደ ሰላም የሚያደርስ መንገድ አለ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እንደገለጹት፥ “ነገር ግን ወደ ሰላም አቅጣጫ የሚወስድ መንገድ በተቋም ደረጃ ለመራመድ ፍላጎት የለም” ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ በችግር ውስጥ የሚገኝ የፖለቲካ እና የሃይማኖት አመራርን እንደምጠይቅ ገልጸው፥ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከመሠረት ጀምሮ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የተስፋ ጭላንጭል አለ”
በዚህ ወቅት “ተስፋ” የሚለው ቃል አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ ነገር ግን በቃሉ ትርጉም ግራ መጋባት እንደማይገባ አሳስበው፥ “ተስፋ” ማለት ነገሮች በሙሉ ወደ ማብቂያው ደረጃ መቃረባቸውን የሚገልጽ ሳይሆን፥ የሰው ዓይን ማየት የማይችለውን በመንፈስ ቅዱስ ዓይን እንድናይ የሚያስችለን ውስጣዊ አመለካከት ነው” ብለዋል።

በአካባቢው የሚታየው የተስፋ ጭላንጭል በጋዛ እና በዌስት ባንክ ለምትገኝ እና ወደ 600 የሚጠጉ ምዕመናን የዕለት እንጀራን በማቅረብ ላይ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያንን ብርታትን እንደሚሰጥ አስረድተዋል። በጦርነቱ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል የተዘጉ ክሊኒኮች እና ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ ይህም የተለመዱ ዕለታዊ ግንኙነቶችን እንደገና ለመጀመር እና ከጭቆና በመውጣት ለነዋሪው የጎደለውን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በቃለ ምልልስ ላይ፥
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በቃለ ምልልስ ላይ፥

ሰላም በራሱ ባሕል ነው
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ ቃለ ምልልሳቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ሁሉም ሰው ሰላምን ለማምጣት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚችል አስታውሰው፥ ሰዎች በተቀራረቡበት በግሎባላይዜሽን ዓለም ውስጥ ሰላም በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሚሠራ የፖለቲካ፣ የትምህርት እና የሚዲያ ቁርጠኝነት ባሕል እንደሆነ አስረድተዋል።

አሁን በመካሄድ ላይ ያለው ድርድር የመጨረሻው ዕድል ነው
በቅድስት ሀገረ የኢየሩሳሌም ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በሪሚኒ ስብሰባ መክፈቻ ወቅት ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በቅድስት ሀገር ያሳለፏቸውን 35 ዓመታትን እና ከልዩ ልዩ የሃይማኖች መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ያካበቱትን ልምድ አካፍለዋል።

የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ አሁን ያሉት ድርድሮች ወሳኝ እና እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑም አረጋግጠዋል። በእስራኤል ጦር እና በሃማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንደሚያበቃ እና የሰላም ድርድሩም አንዳንድ ችግሮችን እንደሚፈታ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “ጥርጣሬ ቢኖረኝም ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ዕድል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ግጭቱ የበለጠ ሊስፋፋ እንደሚችል ያልሸሸጉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ፥ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት አንዱ ሌላውን መቃወም የዕለት ተዕለት ቋንቋ መሆኑ በእውነት አይደንቅም ብለዋል። “በዚህ ሁኔታ ውስጥ በተለይ ጥላቻን፣ አለመተማመንን እና ጥልቅ ንቀትን ለማስወገድ መጸለይ አለብን” ብለው፥ መልካም ጊዜን መልሶ ለመገንባት የሁሉም ወገን ቁርጠኝነት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረጉ የጋራ ውይይቶችን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ በዚህ ወቅት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፥ ጦርነቱ በሕዝቦች መካከል መከፋፈልን በመፍጠሩ ባሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንደማይደረጉ እና በተቋም ደረጃም ቢሆን ተገናኝቶ እርስ በርስ ለመነጋገር አለመቻሉን ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬርባቲስታ በቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያ፥ ከምሁራን ይልቅ በማኅበረሰቦች መካከል የበለጠ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ጠይቀው፥ የሃይማኖት አባቶች ራሳቸውን ለሌሎች ክፍት በማድረግ ይልቁንም ዓይናቸውን ወደ ሰማይ የሚያቀኑ ማኅበረሰቦችን የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

 

21 August 2024, 15:46