ብጹእ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በጋዛ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እየተመለከቱ ብጹእ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በጋዛ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እየተመለከቱ 

ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ የጋዛ የሰላም ውይይት ተቃውሞዎች ቢኖሩም ወደ ስምምነት እየተቃረበ ነው አሉ

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ፒየር ባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የጋዛ ጦርነት የሚያበቃበት ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም ግን አሁንም ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ አስጠንቅቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“እየታዩ ያሉት ነገሮች ተስፋ ሰጪ ናቸው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኳታር ዶሃ በተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት ውይይት ውጤት ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሁንም ድረስ ግጭቶቹ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ቢሆንም፥ ከቀናት በኋላ ድርድሩ በካይሮ ይቀጥላል ተብሎም ይጠበቃል።

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና በጋዛ የሚገኙ የእስራኤል ታጋቾችን በማስፈታት ላይ የሚያተኩር በአሜሪካ፣ ግብፅ እና ኳታር አደራዳሪነት እየተካሄደ በሚገኘው ድርድር ከዶሃ ያልተገለጠ ብሩህ ተስፋ ይታያል፥ በዚህ ጊዜ ግቡን ማሳካት ይቻላል ብለው ያምናሉ? ተብለው የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ አዎን፣ በዚህ ጊዜ፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ጥሩ ሁኔታዎች እንዳሉ አምናለሁ። በተፈጥሮ፣ አንዳንድ እንቅፋቶች ስለማይጠፉ ሁል ጊዜ የሰላም ውይይቱን የሚቃወሙ ሊኖሩ ይችላሉ፥ ሆኖም ግን በመጨረሻ ይህንን የጦርነት ምዕራፍ ለመደምደም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ አምናለሁ። በዚህም ምክንያት፣ ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ በኢራን ቀጥተኛ ጣልቃገብነት ግጭቱ በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም ወደ ሊባኖስም ጭምር እየተዛመተ ነው ካሉ በኋላ፥ ብጹእነታቸው በመቀጠል “ደግሜ እላለሁ፣ ብዙ ችግሮች አሉ፣ ነገር ግን ይህን ሁኔታ ለመቋጨት ከአደራዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካም ጭምር ከፍተኛ ጥረት እንዳለ አምናለሁ፥ በመሆኑም ያሉት ሁኔታዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው” ብለዋል።

“አዎን፣ በዚህ ጊዜ፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ጥሩ ሁኔታዎች እንዳሉ አምናለሁ። በተፈጥሮ፣ አንዳንድ እንቅፋቶች ስለማይጠፉ ሁል ጊዜ የሰላም ውይይቱን የሚቃወሙት ሊኖሩ ይችላሉ፥ ሆኖም ግን በመጨረሻ ይህንን የጦርነት ምዕራፍ ለመደምደም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ አምናለሁ”

አሁን እየተደረጉ ባሉ የሰላም ድርድሮች ምክንያት ኢራን በእስራኤል ላይ የምታደርገውን የጣልቃ ገብነት ስጋት ያስቀራል ተብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል ወይ ተብለው የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ "አዎ፥ ሆኖም ግን ራሳችንን ማታለል የለብንም። ግጭቱ እስካሁን አላበቃም። በጋዛ ሰርጥ የዓለም ማህበረሰብ በግልጽ እያየ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ክስተት እና ሁል ጊዜም አንደበት አልባ እንድንሆን እያደረገን የሚገኘውን በተከታታይ እየተወሰደ ያለውን የቦምብ ጥቃት በግልጽ እያየን እንገኛለን" ብለዋል።

በእርግጥ በጋዛ የቦምብ ጥቃቶች ያለማቋረጥ ቀጥለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማስ ነሃሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደገለጸው፣ ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ በጋዛ ከ40,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልጿል፥ በጋዛ ያለው የክርስቲያን ማህበረሰብ ይህንን ሁኔታ እንዴት እያሳለፈው ነው? ተብለው የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ ከጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል በጋዛ ከተማ ውስጥ የሚገኘው በቁጥር አነስተኛ የሆነው ማህበረሰባችን ምንም እንኳን አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፥ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በተቻለ መጠን፣ በተሻለ እና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር እየሞከረ ይገኛል ብለዋል።

እኛ ከ ‘ማልታ ናይትስ’ ከሚባለው ግብረሰናይ ድርጅት ብቻ ከምናገኘው እርዳታ ሳይሆን ከሌሎች በርካታ ማኅበራት ከምናገኘው ሰብዓዊ ድጋፍ ህዝቡን ለመርዳት በመሞከር ላይ እንገኛለን። የመጨረሻዎቹን ከሺህ የሚበልጡ የእርዳታ ጥቅሎችን የላከልን ‘ሜኖናዊት ቸርች’ የሚባል ተቋም ነው። እነዚህ እርዳታዎች በዚህ በጣም አሳሳቢ እና አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ያለውን የአብሮነት መንፈስ ለማየት የሚያስችለን በጣም ቆንጆ ምሳሌ ነው በማለት አስረድተዋል።

የአብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት በጋዛ እና በሊባኖስ ድንበር ላይ ብቻ ቢሆንም፥ በዌስት ባንክ ያለው ሁኔታ በየቀኑ አሳሳቢ እና አስጊ እየሆነ መጥቷል፥ ከእነዚህ አካባቢዎች ምን አይነት መረጃዎች እየደረሶት ነው? የተባሉት ብጹእ ካርዲናል፥ ጥያቄው እውነት መሆኑን ገልጸው፥ ስለ ጋዛ ብዙ ነገር ይዘገባል፥ ነገር ግን በዌስት ባንክ ግዛት ውስጥም በጣም አሳሳቢ ሁኔታ አለ። ከጥቂት ቀናት በፊት ጥቂት የማይባሉ ሰፋሪዎች በአንድ የፍልስጤም መንደር ላይ ባደረሱት የጅምላ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት በርካታ ጉዳቶችን አስከትሏል ብለዋል።

“ስለ ጋዛ ብዙ እየተወራ ነው፣ ትክክል ነው፥ ነገር ግን በዌስት ባንክ ግዛት ውስጥ በጣም አሳሳቢ ሁኔታም አለ”

ይህ በዌስት ባንክ ውስጥ ቀጣይነት ያለው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚገኘው ውጥረት በእነዚህ ወራት ተለይተው የሚታወቁት ተከታታይ ክስተቶች የቅርብ ጊዜ ትዕይንት ነው። ውጥረት፣ የእስራኤል ታጣቂ ሃይሎች ባሉበት ሁኔታ እንኳን በሰፋሪዎች እና በፍልስጤማውያን መካከል የማያቋርጥ ግጭት አለ፣…በአጭሩ የፍልስጤምን ህዝብ ህይወት የበለጠ ውስብስብ እና አስቸጋሪ የሚያደርግ ቀጣይነት ያለው ውጥረት አለ ብለዋል።

ግጭቱ በዌስት ባንክ እንደ አዲስ ሊፈነዳ እንደሚችል የጠቆሙት ብጹእነታቸው፥ ለዚህም ነው ጠንክረን መሥራት ያለብን ካሉ በኋላ፥ በመጀመሪያ ደረጃ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ እንዳለበት ገልጸው፣ ከዚያም በዌስት ባንክ በተቻለ መጠን ስርዓትን፣ ደህንነትን እና ህይወትን ወደነበረበት መመለስ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ነገሮች ቀላል ባይሆኑም ወደ ተሻለው ነገር መጓዝ አለብን ያሉት ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ፥ “ሁል ጊዜ እንደምናገረው በዌስት ባንክ የምናየው ጥላቻ፣ ንዴት፣ ንቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፋ ወደ መጣው ጽንፈኝነት እና ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆኑ የጥቃት ዓይነቶችን እንዴት እንደመራ የሚያሳይ ግልጽ እና ተጨባጭ ምሳሌ ነው። ስለዚህ በፖለቲካ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም ብዙ መሥራት አለብን፣ ምክንያቱም የዚህ ጥቃት መነሻው ሃይማኖታዊም ጭምር በመሆኑ ነው፥ እነዚህ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ እንዲገለሉ እና አሁን ያላቸውን ጥንካሬ ሁሉ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል።
 

19 August 2024, 13:46