ፈልግ

በዩኬ እየተካሄደ ያለው አመጽ - ዮርክሻየር፣ ሃል ከተማ በዩኬ እየተካሄደ ያለው አመጽ - ዮርክሻየር፣ ሃል ከተማ 

አብያተ ክርስቲያናት በዩናይትድ ኪንግደም የተንሰራፋውን የፅንፈኞች የዘረኝነት አመፅን አወገዙ

በእንግሊዝ ሃገር የሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች ባለፈው ሳምንት በሳውዝ-ፖርት ከተማ በደረሰው አሰቃቂ የስለት መሳሪያ ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰውን የፀረ- ስደተኞች አመፅ የብሪታንያ ማህበረሰብ እሴቶችን አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉ ተቃውመውታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዩናይትድ ኪንግደም ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፥ ስደተኞችን እና ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረገው ተቃውሞ በንብረት እና በፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ማድረሱም ተነግሯል። አመጹን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀኝ አክራሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በጉዳዩ ላይ ለመምከር ካቢኔያቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

ይሄን ተከትሎ በእንግሊዝ እና በዌልስ የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች ለንደንን ጨምሮ በዩናይትድ ኪንግደም ለቀናት በርካታ ከተሞችን እያወደመ ያለውን የቀኝ አክራሪ እና ፀረ-ስደተኛ አመፅን አጥብቀው አውግዘዋል።

ብጥብጡ የተቀሰቀሰው ሀምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ሳውዝ-ፖርት ከተማ በሚገኘው የህፃናት የውዝዋዜ ትምህርት ቤት ውስጥ በደረሰ ከባድ የስለት ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፥ በጥቃቱም ሶስት ህፃናት ሲገደሉ ሌሎች ሰዎችም መቁሰላቸው ተነግሯል።

ከጥቃቱ በኋላ ከሩዋንዳዊ ወላጆች በዌልስ ከተማ የተወለደው አክስኤል ሩዳኩባና የተባለው የ17 ዓመቱ እንግሊዛዊ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ጥቅምት 15 ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የታወቀ ሲሆን፥ የድርጊቱ መነሻ ምክንያቱ ገና በውል ባይታወቅም፥ የሃገሪቱ ፖሊስ ግን ሽብርተኝነት ነው በማለት ገልጿል።

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በሚወጡ የሃሰት ዜናዎች ምክንያት አመፁ ተባብሷል
ሆኖም ከጥቃቱ በኋላ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ለስለት መሳሪያ ጥቃቱ አንድ ሙስሊም ስደተኛ ተጠያቂ እንደሆነ በተናፈሱት የውሸት ዜናዎች ምክንያት ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረገ ተቃውሞ መንሰራፋቱ ተጠቁሟል።

በሀገሪቱ ከአስርት ዓመታት ወዲህ በህጻናት ላይ ከተፈጸሙት አስከፊ ጥቃቶች አንዱ የሆነው ይህ ጥቃት በብሪታንያ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፥ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ባሉ በርካታ ከተሞች የቀኝ አክራሪ እና ፀረ-ስደተኛ ሀይሎች የአመፅ ሰልፎችን እያካሄዱ ይገኛል።

የቀኝ አክራሪ ሃይሎች በማህበራዊ ድረ-ገፆች በኩል በሚያሰራጩት የተሳሳተ መረጃ እና በጥላቻ፣ በጸረ-ስደተኛ እና ፀረ-ሙስሊም ትርክቶች ምክንያት በተዛመተው አመፅ፥ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ፖሊሶችን በቤንዚን በተሞሉ ጠርሙሶች እና በጡብ ድንጋይ በማጥቃት፣ የድንገተኛ አገልግሎት ሰራተኞችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች በመፈፀም እና የስደተኞች መኖሪያ ቤቶችን በማቃጠል አመጹ ተንሰራፍቷል።

በቅርብ ከተፈጸሙት ክስተቶች ውስጥ ሰኞ አመሻሽ ላይ በሰሜናዊ አየርላንድ በምትገኘው ቤልፋስት ከተማ በጥላቻ ስሜት በተሞሉ አመፀኞች በአንድ ስደተኛ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ጥቃት ስደተኛው በከባድ ሁኔታ በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተነግሯል።

ብጥብጡ ከተጀመረ ጀምሮ ከ400 በላይ ሰዎች እንደታሰሩ፣ እንዲሁም አዲስ የተመረጡት የሰራተኛ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ወረርሽኙን 'የቀኝ አክራሪዎች አመፅ' በማለት የገለፁ ሲሆን፥ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በድህረ-ገጾች በኩል ሁከት መቀስቀስን የሚከለክሉ ህጎችን ማክበር እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

ብጹአን ጳጳሳት አመጽ የብሪታንያ ማህበረሰብን የሲቪል እሴቶችን ያጎድፋሉ ማለታቸው
ይህ በእንዲህ እያለ የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የብሪታንያ ማህበረሰብ እሴቶችን አደጋ ላይ የሚጥል ዘረኝነትን መሰረት ያደረጉ ሁከቶችን በጽኑ አውግዟል።

የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፖል ማክሌናን እነዚህ አመፆች “የሀገራችንን የሲቪል ህይወት መሰረት የሆኑትን እሴቶች ሙሉ በሙሉ ችላ ማለታቸውን ያሳያሉ” በማለት ገልጸዋል። ብጹእነታቸው በመቀጠልም “ይህ ጥቂት ሰዎች የተሳተፉበት የአመፃ ተግባር፥ ስደተኞችን ያለመታከት በአንድነት መንፈስ እጃቸውን ዘርግተው ከሚቀበሉት እና ከሚረዱት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የቤተ ክርስቲያን ቡድኖች እና በጎ ፈቃደኞች ሥራ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነው” ካሉ በኋላ፥ “ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከተከሰቱት አስከፊ ክስተቶች በኋላ ማህበረሰባችንን እንደገና መገንባት እንድንችል ጥረታቸውን ገፍተው እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን፣ ለዚህም እንጸልያለን” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ማክሌናን በብሪታንያ ለሚገኙ ስደተኞች ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ፥ “እዚህ በማህበረሰቡ ዘንድ የተወደዳችሁ ናችው፥ በመሆኑም ደህንነት እንዲሰማችሁ ሁላችንም የምንችለውን ማድረግ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል። ብጹእነታቸው አደጋው ቢገጥምም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሥራቸውን በጽናት መስራት ለቀጠሉት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከልብ የመነጨ ምስጋና በማቅረብ፥ “ለጋራ ጥቅም ሲባል አገልግሎት ለምትሰጡ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

የጥቃት ዒላማ የሆኑ ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልጋል መባሉ
በብሪታንያ ውስጥ ስደተኞችን ከሚደግፉ ድርጅቶች መካከል የጄስዊት የስደተኞች አገልግሎት (JRS-UK) ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ሳራ ቴዘር የብሪታንያ መንግስት በሁከቱ ምክንያት ከባድ የስሜት መረበሽ እና ጥልቅ የሆነ ስጋት ላይ ያሉትን በጥገኝነት ጥያቄ ሂደት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ የሁሉንም ሰዎች ደህንነት ለማረጋገጥ አስቸኳይ እርምጃዎችን እንዲወስድ ተማጽነዋል።

ወይዘሮ ሳራ ቴዘር ሁሉም የብሪታኒያ ዜጎች ይህንን የጥላቻ መንፈስ የሚያራምዱትን፣ የተዛባ መረጃን እና ዘረኝነትን እንዲሁም ከፋፋይ ንግግሮችን እንዲቃወሙ በመጠየቅ፥ “ብዙውን ጊዜ አደጋን ሸሽተው እዚህ ህይወታቸውን መልሰው ለመገንባት እድሉን የሚፈልጉ ሰዎች በፖለቲከኞች እና በሌሎች ተፅእኖ ፈጣሪዎች ሰብአዊነታቸው ይጣሳል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ዌልቢ ማሕበራዊ ህይወት እጦት ዓመፅን አያጸድቅም ማለታቸው
የካንተርበሪው የአንግሊካን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ በበኩላቸው ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ አመፁን በጠንካራ ቃላት በማውገዝ፥ ሁከት ፈጣሪዎቹ “እራሳቸው የለበሱትን ባንዲራ ያረክሳሉ” ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በማከልም እንደተናገሩት “አመፀኞቹ የሃገሪቷን ክርስቲያናዊ እሴቶች ስለመጠበቅ ይናገራሉ” ነገር ግን “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩ ሕይወት እንዲኖርህ በሕይወት ዘመንህ ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲጠየቅ ‘አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ፣ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፣ ጠላትህንም ውደድ’ ማለቱን” አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ ዌልቢ እንደተናገሩት፣ በተጨናነቀ አካባቢ መኖር ለጥቃት ሰበብ ባይሆንም፣ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሀብት በሀብታሞች እና በድሆች መካከል የበለጠ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጋራት እንደነበረበት በመግለጽ፥ “ማህበራዊ እጦት በምንም መልኩ ይህንን ጥቃት የሚያረጋግጥ አይደለም። ነገር ግን የኢኮኖሚያችን ጥቅሞች ለተቸገሩ ሰዎች ሁሉ እንዴት እንደሚካፈሉ መለስ ብለን ማየት አለብን” ካሉ በኋላ፥ “በምድር ላይ ካሉት ሰባቱ የበለጸጉ አገሮች አንዷ ብሪታኒያ እንደመሆኗ፣ ሁሉም ሰው በዜግነቱ ከሃብቷ እኩል ማግኘት ይኖርበታል” ብለዋል።

የብሪታንያ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ደብዳቤ
የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ቪንሰንት ኒኮልስ፣ ዋና ረቢ ሰር ኤፍሬም ሚርቪስ፣ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ፣ ዋና ኢማም ዶክተር ሰይድ ራዛዊ እና የኢማሞች ብሔራዊ አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ኢማም ቃሪ አሲም ለታይምስ መጽሄት በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፥ ሁከትና ብጥብጥን በጽኑ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

ደብዳቤው በመስጊዶች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲሁም በፖሊስ እና በግል ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት “በአገራዊ የሞራል ህልውና ላይ ያነጣጠረ ነው” በማለት ይገልፃል።
 

07 August 2024, 13:25