ፈልግ

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ዕርገት የሚያሳይ ምስል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ዕርገት የሚያሳይ ምስል   ( (foto © Custodia di Terra Santa))

የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን እመቤታችን ድንግል ማርያምን የሰላም አርአያችን ስለሆነች እናመሰግናታለን አሉ

የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓልን ምክንያት በማድረግ የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ፍራንቺስኮ ፓቶን በኢየሩሳሌም በሚገኘው የደብረ ዘይት ቤተክርስቲያን የተካሄደውን ሥርዓተ ቅዳሴ በመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ምእመናን በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እንዲሰፍን ጠንክረው እንዲጸልዩ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አባ ፍራንቺስኮ ፓቶን የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የእርግርት በዓል አስመልክቶ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የደብረ ዘይት አጎኒ ባዚሊካ የተካሄደውን ሥርዓተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ባደረጉት ስብከተ ወንጌል፣ በመካከለኛው ምስራቅ ላለፉት አስር ወራት የቆየውን አስከፊ ግጭት በማንሳት፥ የእናታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የእርገት በዓልን አስመልከተው ባቀረቡት ጸሎት ሰላም በምድሪቷ እንዲወረድ እና “በመጨረሻም የሰው ልጅ ዕርቅ እንዲያገኝ” ተማጽነዋል።

ክፉዎች ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ
አባ ፓቶን በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የምታቀርበውን የራዕይ ምንባብ አስታውሰው፣ በበረሃ የምትገኝ አንዲት ሴት ልጇን ልትወልድ፣ የተወለደውን ሕፃን ለመብላት የተዘጋጀ አንድ ኃይለኛ እና አስፈሪ የሆነ፣ ነገር ግን ውስን አጥፊ ኃይል ብቻ የተሰጠውን ከድራጎን ጋር የተነፃፀረውን አውሬ ያየችበትን ራዕይ በማስታወስ አስተንትነዋል።

አባ ፓቶን ምንም እንኳን ለዚህ የራዕይ ክፍል በርካታ ትርጉሞች እንደሚሰጡት ቢያውቁም እሳቸው ግን ሴቲቱ የቤተክርስቲያን አምሳል መሆኗን በተጨማሪም እመቤታችን ድንግል ማርያምም መሆኗን እንደሚገነዘቡ በመጥቀስ፥ በዘንዶው የተመሰለው ደግሞ “ክፋትን በሁሉም መገለጫዎች እና በተጠራባቸው ስሞች ሁሉ እናያለን” ብለዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሴቲቱና በዘንዶው መካከል የተገለጸው ተጋድሎ፣ “ክፉው በእግዚአብሔር ፍቃድ የሆነውን የአዲስ ዓለም መወለድን ለማፍረስ የሚያደርገውን የማያቋርጥ ሙከራ” መሆኑን ከመግለጽ ሌላ ምንም አይደለም ካሉ በኋላ፥ “የሰው ልጅ መወለድ ከአሁን በኋላ በዓመፅ፣ በጦርነት፣ በገበያ፣ በባህላዊ ቅኝ ግዛት፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ባርነት ውስጥ አይቀርም” በማለትም አክለዋል።

ቅድስት ማርያም የመጨረሻ እጣ ፈንታችን ትንቢት ናት
የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን በስብከታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስም በሥጋም ወደ መንግሥተ ሰማያት ስትገባ፣እኛም ‘ወደ ግጭት የማንጎተት እና የማንዳከምበት’ ወደ መጨረሻው እጣ ፈንታችን የምንደርስበት ይሆናል ያሉ ሲሆን፥ “ይልቁንም” አሉ በመደነቅ ስሜት፥ “ለሕዝብ፣ ለቋንቋና ለባሕሎች ሁሉ ቦታ ወዳላት ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እና ወደ አምላካችን ከፍ ከፍ የምንልበት ነው” ብለዋል።

                    “የእኛ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ወደ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ማለት ነው...”

በዚህ አግባብ ይላሉ ካህኑ፥ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ስታደርግ እንደነበረው በመልአኩ ብስራት እግዚአብሔርን ባመነች ጊዜ እና በመስቀሉ ሥር በቆመች ጊዜ “በከንቱ ክፋት፣ ንጹሕ ሆና ሳለ በደረሰባት መከራ እና በልጇ ኢፍትሐዊ ሞት ሳትደክም እና ሳትደነግጥ በአብ ፈቃድ ብቻ ስትኖር የነበረችው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንቢት የተነገረላት ነች” ብለዋል።

ምድራችን ከእንግዲህ የጠብና የጦርነት ቦታ አይሁን
ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ክብር በሚዘመረው መዝሙር የታጀበው በቅድስት ሀገር የፍራንቸስካዊያን ማሕበር የበላይ አበሜኒት የሆኑት አባ ፍራንቺስኮ ፓቶን ስብከት፥ ቅድስት ማሪያም ለታሪካችንም ጭምር ትንቢት ነበረች ብለዋል።

ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ፥ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ እንደተነገረው ትዕቢተኞች ከነአሳባቸው ተበታትነዋል። ታላላቅ ገዥዎች ከዙፋናቸው ወርደዋል። በመጨረሻም ትሑታን ይነሳሉ፤ የተራቡትም በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ሰላማውያን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው ይታወቃል፤ የዋሆችም ምድርን በስጦታ ይቀበሏታል ብለዋል።

ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት “ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ዛሬ የሰላምን ስጦታ እንዲሰጠን አማላጅነቷን እንለምናለን” ያሉት አባ ፓተን፥ ይህ ማለት “የራሳቸውን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ ሃይማኖት በሃይል ለመጫን የሚፈልጉ ስልጣን የላቸውም፥ ይልቁንም ትናንሾቹ በሰላም እንዲኖሩ እና ታጋቾች እና እስረኞች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ እንጸልያለን” ካሉ በኋላ፥ “ምድር ከአሁን በኋላ የጠብ እና የጦርነት ቦታ እንዳትሆን፥ ነገር ግን ከመውረር እና በሃይል ከመግዛት ይልቅ በስጦታ እንዴት እንደሚቀበሉት የሚያውቁ እና ለመንከባከብ ፈቃደኛ የሆኑ የዋሆች እንደ ስጦታ ይቀበሏት ዘንድ እንለምናለን” በማለት ጸልየዋል።

በፍልሰታ ማሪያም በዓል ላይ ለሰላም ጸሎት የተደረገ ጥሪ
ነሃሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. አባ ፓቶን ለፍራንችስካውያን ወንድሞቻቸው በላኩት መልዕክት በላቲን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት ነሐሴ 9/2016 ዓ. ም. በሚከበረው የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የሚጠቀሙበትን የጸሎት መንገድ በመከተል ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለዓለም ሰላም ጸሎት እንዲያቀርቡ አሳስበው ነበር።

በቅድስት አገር የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ነሐሴ 9 ቀን በኳታር እየተካሄደ ያለውን የተኩስ አቁም ውይይት በማስመልከት ይሄንን ጸሎት እራሳቸውም የሰላም ስጦታን ለመጠየቅ እንደሚጠቀሙበት በመግለጽ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ተመሳሳይ የጸሎት ጽሑፍ እንዲደግሙ ጋብዘዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ለቅድስት ሀገር ምእመናን በላኩት ደብዳቤ ላይ፡ “ሁላችንም በዚህ ወቅት በብዙ ግፍ እና በእርግጥም በቁጣ... ብዙ ተሰቃይተናል” ካሉ በኋላ፥ “ብዙ ነገር ከተናገርን በኋላ እና ሁሉንም በተለይም በጣም የተጎዱትን ሰዎች ለመርዳት እና ለመቅረብ የተቻለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ አንድ የቀረን ነገር ቢኖር መጸለይ ብቻ ነው” ብለዋል።

                                                                “የቀረው ነገር መጸለይ ብቻ ነው”
 

16 August 2024, 13:21