ፈልግ

ከግራ የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ፣ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆአዎ ሎሬንሶ እና የኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ ከግራ የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ፣ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆአዎ ሎሬንሶ እና የኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ 

የኮንጎ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት የሉዋንዳው ስምምነት እንዲከበር በማለት ጥሪ አቀረቡ

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ፥ በሩዋንዳ እና በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት እንደ ቀደመው ዋጋ ቢስ ሆኖ እንዳይቀር አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮንጎ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳቱ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ያለውን ዘረኝነት ለማስወገድ የተደረገው ጥረት አዝጋሚ ለውጥ እያሳየ ቢሆንም ዓለም አቀፍ አጋሮች የሰላምን ፍኖተ ካርታ በበቂ ሁኔታ እንዲደግፉት ጠይቀዋል።

ጉልህ እርምጃ ተወስዷል
የአንጎላ ፕሬዝዳንት አቶ ጆአዎ ሎሬንሶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በሩዋንዳ ሪፐብሊክ ሁለተኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ መጨረሻ ላይ የተፈረመው የሉዋንዳ የተኩስ አቁም ስምምነት በነሐሴ ወር 2016 ዓ. ም. ተግባራዊ ይሆናል” ብለዋል።

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሰሜናዊ ኪቩ ግዛት ውስጥ በአገሪቱ ወታደራዊ ሠራዊት እና በሩዋንዳ ይታገዛል በሚባለው ኤም 23 አማፅያን መካከል ግጭቶች ተከስተው ሁከቱ በአካባቢው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉ ታውቋል።

ኮንጎ ሩዋንዳን የኤም 23 አማፂያንን ትደግፋለች ስትል ትወቅሳለች። የሩዋንዳ ጦር ሠራዊት በግጭቱ ተሳትፏል ስትል ኮንጎ የምታቀርበውን ክስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባዎች አረጋግጠዋል። ነገር ግን በቅርብ የተደረሰው የሉዋንዳው የተኩስ አቁም ስምምነት ለተወሰኑ ዓመታት ሲቀጣጠል የቆየውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጉልህ እርምጃ ይሆናል ተብሏል።

አንድ እርምጃ ወደፊት ብሏል
የኮንጎ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በጋዜጣዊ መግለጫቸው፥ “በእርምጃው ሁሉም ወገኖች እንኳን ደስ አላችሁ” ካለ በኋላ፥ ነገር ግን ይህ በሩዋንዳ እና በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት መንግሥታት መካከል የተፈረመው የመጀመሪያው ስምምነት እንዳልሆነ ገልጾ፥ “የቀደሙት ስምምነቶች በሙሉ በቸልታ ተጥሰዋል፣ ምንም ዓይነት ማዕቀብ አልተጣለም” ሲል ገልጿል።

የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ሁለቱን ፈራሚዎች ማለትም የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና ሩዋንዳ ይህን ስምምነት እንዲያከብሩ የጋበዘ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ አጋሮችም ይህን ፍኖተ ካርታ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመደገፍ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ እና በምሥራቁ የኮንጎ ግዛት በሕዝብ ላይ የሚደርስ መከራ እንዲያቆም ጥሪ አቅርቧል።

የኮንጎን ሕዝብ በጎሳ መከፋፈል ይቁም
በኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፐብሊክ ምሥራቁ ክፍል የሚታየውን የደህንነት እና የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ለመፍታት ያለሙ የተለያዩ ጅምሮች መኖራቸውን የገለጸው የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ፥ በቅርቡ በሉዋንዳ የተደረሰውን ስምምነት ጨምሮ ሌሎች ጥረቶች ጥቂቶች ቢሆኑም ነገር ግን ጉልህ እድገት መኖሩን አስረድቷል። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ባለው ግጭት በተሳተፉት አካላት እና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል አዝጋሚ የለውጥ ሂደት መኖሩን የገለጸው የጳጳሳቱ ጉባኤ፥ በማከልም “በእነዚህ ግጭቶች የተጎዳውን የኮንጎ ማኅበረሰብ መከራ ለማስቆም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ” ወስዷል ሲል አስታውቋል።

በኮንጎ ያለው ጦርነትም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው
የኮንጎ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በመግለጫቸው፥ እስከ አሁን ድረስ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ምሥራቁ ክፍል የሚካሄደው ጦርነት “በዩክሬን ወይም በመካከለኛው ምሥራቅ ካለው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ቅድሚያ ተሰጥቶታል” ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ገልጾ፥ በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች መካከል የሰው ልጅ ሕይወት እየጠፋ፣ ሰብዓዊ መብቶቹ እየተጣሱ እና ክብሩም እየተረገጠ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኮንጎ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት የሉዋንዳው ስምምነት እንዲከበር ባቀረቡት ማሳሰቢያ፥ በተደጋጋሚ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወንዶች በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠሩ በመሆናቸው፥ በአገራቸው ተከባብረው በሰላም እንዲኖሩ ማስቻልን ከግምት በማስገባት፥ አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።


 

13 August 2024, 16:09