የፓሪስ ኦሎምፒክን ምክንያት በማድረግ በኖትር ደም ካቴድራል ደጃፍ የተደረገ የተለያዩ ሃይማኖቶች ስብሰባ የፓሪስ ኦሎምፒክን ምክንያት በማድረግ በኖትር ደም ካቴድራል ደጃፍ የተደረገ የተለያዩ ሃይማኖቶች ስብሰባ   (ANSA)

በፓሪስ ኦሎምፒክ አምስት የተለያዩ ሃይማኖቶች ወንድማማችነትን ለማክበር ተሰባሰቡ

የዘንድሮው የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የቫቲካን ተወካይ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኢማኑኤል ጎብሊያርድ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት እሁድ ዕለት በኖትር ዳም ካቴድራል ደጃፍ ስለተካሄደው የተለያዩ ሃይማኖቶች በጋራ ያዘጋጁት ሥነ ሥርዓት አስፈላጊነትን በማስታወስ፣ መርሃግብሩ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት መልዕክትን አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 1924 ዓ.ም. በፓሪስ በተካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወቅት የኖትር ዳም ካቴድራል ልዩ የሆነ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ሥነ ሥርዓት ተዘጋጅቶ እንደነበር ይታወሳል። ከ 100 ዓመታት በኋላ በዓለም ላይ በጣም አስፈላጊ የሆነው የኦሎምፒክ ስፖርት የሚደግፈውን የወንድማማችነት መንፈስ ለማክበር በታዋቂው የፓሪሶች መለያ በሆነው ካቴድራል ደጃፍ ሃምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌላ የአምስት ሃይማኖቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች
ሃምሌ 18 እሑድ ጠዋት 4 ሰዓት ላይ የአምስቱ ዋና ዋና የዓለም ሃይማኖቶች ተወካዮች፣ ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ከደረሰበት ከባድ የእሳት አደጋ በኋላ በእድሳት ላይ ከሚገኘው እና በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ይከፈታል ተብሎ በሚጠበቀው የፓሪስ ዋና መለያ ምልክቶች ውስጥ አንዱ በሆነው የኖተር ዳም ካቴድራል ደጃፍ ላይ ተሰባስበዋል።

የአምስቱ ሃይማኖት ተወካዮች ከኦሎምፒክ መንደር ውስጥ በሚገኘው የተለያዩ ሃይማኖቶች ህብረት ማዕከል በመጡ አንድ መቶ ካህናት በመታጀብ፣ ስፖርት የሰው ልጅን መልካም ነገሩን በመጠቀም የዓለምን ህዝቦች እንዴት ማገልገል እንደሚችል ያላቸውን ሀሳብ አካፍለዋል።

ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን የፓሪስ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ረዳት የሆኑት ብጹእ አቡነ ፊሊፕ ማርሴት፣ የፈረንሳይ የፕሮቴስታንት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቄስ ክርስቲያን ክሪገር እና የብሔራዊ ኦርቶዶክስ ሆስፒታል ቄስ የሆኑት አንቶን ጌሊያሶቭ የክርስትናን ሃይማኖት ወክለው በሥፍራው የተገኙ ሲሆን፥ ከእነዚህም በተጨማሪ፥ የፈረንሳዩ ዋና ረቢ ሀይም ኮርሲያ፣ የፓሪስ መስጊዶች ማህበር ፕሬዝዳንት ናጃት ቤናሊ፣ የፈረንሳይ የቡድሂስት ህብረት ተባባሪ ፕሬዝዳንት ላማ ጂግሜ፣ እንዲሁም የሂንዱ ማህበረሰብን ወክለው ሻይሌሽ ብሃቭዛር መርሃግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

በ2024 ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ የቅድስት መንበር ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የዲግ ሃገረስብከት ጳጳስ ብጹእ አቡነ ኢማኑኤል ጎቢሊያርድ ለቫቲካን የዜና ወኪል ዣን ቤኖይት እንዳስረዱት፥ ዝግጅቱ የተካሄደበት ‘ኖትር ዴም ደ ፓሪስ’ ጥልቅ የሆነ ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ዙሪያ “ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ መልዕክት የሚያስተላልፍ ቦታ” መሆኑን ጭምር አስረድተዋል።

የሃይማኖት መሪዎቹ በመርሃ ግብሩ ላይ በጸሎት፣ ልባዊ ምክር በመለገስ እና በንባብ በመታጀብ ሃሳባቸውን በነፃነት የተናገሩ ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ጎቢሊያርድ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት የጥሞና ጊዜያትን ተፅእኖ ጎላ አድርገው ገልጸው፥ “ይህ የተለመደውን ጸሎት ለመግለፅ በጣም ቆንጆው መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፣ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነገር እንድትናገሩ ይፈቅድላችዋል” ብለዋል።

“እግዚአብሔር ተአምር አደረገ”

የዘመናዊው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጀማሪ በሆነው ባሮን ፒየር ደ ኩበርቲን አነሳሽነት እ.አ.አ. ሐምሌ 5 ቀን 1924 ዓ.ም. የተዘጋጀው የመጀመሪያው የሃይማኖቶች የጋራ ስብሰባ ሁሉንም አትሌቶች ከሞላ ጎደል አንድ ላይ አካቶ እንደነበር ይታወሳል።

ብጹእ አቡነ ጎቢሊያርድ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት መጀመሪያ ላይ ውጥኑ አንዳንድ ውዝግቦችን ፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰው፥ “ዴ ኩበርቲን በወቅቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መስዋዕተ ቅዳሴም ሆነ መባረክ፣ በመሠዊያው ላይ የሚሳተፉ ካህናትን ወይም ማንኛውንም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥነ ሥርዓትን እንደማያካትት፥ ነገር ግን በሚያምር ሁኔታ የተቀናጁ የተወሰኑ ውብ መዝሙሮችን እና በጣም ጥቂት የሆኑ ዓለማዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግርን እንደሚያካትት አብራርቶ ነበር” በማለት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ሥነ ሥርዓቱ ከጊዜ በኋላ በተለያዩ ሚድያዎች አድናቆት እንደተቸረው የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የፈረንሳዩ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ፓሪስ ሶየር “እግዚአብሔር ፕሮቴስታንቶችን፣ ቡዲስቶችን፣ አይሁዶችን እና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በማሰባሰብ ተዓምር አድርጓል” ሲል አስነብቧል።

የወንድማማችነት መንፈስ
ብጹእ አቡነ ጎቢሊያርድ እንደተናገሩት ይህ ያልተለመደ እና ልዩ ክስተት ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ሃይማኖቶች ወንድማማችነታቸውን ለመግለጽ ይፈልጉ እንደ ነበር የሚያሳይ ሲሆን፥ ይህ የሆነውም በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ የአንድነት መንፈስ በኦሎምፒክ መንደር በሚገኘው እና አምስት የጸሎት ክፍሎች ያሉት፣ እንዲሁም በውድድሮቹ ወቅት መንፈሳዊ ድጋፍ በሚሰጠው የሃይማኖቶች ህብረት ማዕከል ውስጥ በሚደረጉ ጨዋታዎች በሙሉ ላይ ከሚሳተፉ የኦሎምፒክ አትሌቶች ጋር አብሮ መጓዙን ይቀጥላል ተብሏል።
 

06 August 2024, 16:50