ሲስተር ጆይ አቡህ ከቅድስት ማርያም ሙያ እናቴክኒክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር - ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲስተር ጆይ አቡህ ከቅድስት ማርያም ሙያ እናቴክኒክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር - ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. 

የጋና ሲስተሮች በየትምህርት ቤቶች ውስጥ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብር ጀመሩ

በጋና የሚገኙት የእመቤታችን ቅድስት ማሪያም ሚስዮናውያን እህቶች ማህበር በምስራቃዊ ጋና፣ ኩዋዩ አፍራም ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ላሉ ተማሪዎች ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል ስለ ሚቻሉባቸው መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮችን እያካሄዱ የሚገኙ ሲሆን፥ በጋና የታሊታ ኩም ትሥሥስር ተወካይ የሆኑት ሲስተር ጆይ አቡህ ጉዳዩን አስመልክተው “ወንጀለኞች ኢላማቸውን ለማሳካት ስለሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ዘዴዎች እናስተምራቸዋለን” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም የተዘጋጀው በታሊታ ኩም ትሥሥር አማካይነት ሲሆን፥ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ጋና ደቡባዊ ከተማ በሆነችው የዶንኮርክሮም ከተማ በሚገኙት የኩዋሁ አፍራም ወረዳ ሰሜናዊ አከባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተካሂዷል።

በአፍራም ወረዳ ውስጥ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በዓለም አቀፍ የሴት ገዳማዊያት ጉባኤ በሆነው የቅድስት እመቤታችን ሚስዮናውያን እህቶች በኩል እየተከናወነ እንደሆነም ተገልጿል።

የገዳማዊያቱ ተልእኮ በሁሉም ዓይነት ፍላጎት ውስጥ ያሉ ሰዎችን በተለይም ድሆችን፣ የተጨቆኑ እና የተበዘበዙ ሰዎችን በተቻለ አቅም ለመድረስ የሚፈልግ ሲሆን፥ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር የሚመራው በጋና የታሊታ ኩም ተወካይ በሆኑት ሲስተር ጆይ አቡህ እንደሆነም ተነግሯል።

ሲስተር ጆይ በጋና ያሉትን ትምህርት ቤቶች ጎብኝተዋል
የናይጄሪያ ተወላጅ የሆኑት ሚስዮናዊዋ ሲስተር ጆይ በዶንኮርክሮም ከተማ በሚገኘው የግብርና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እና መምህር ሆነው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፥ ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ዙሪያ ግንዛቤ ለማግኘት በመንደሩ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶችን እየጎበኙ እንደሆነ ተነግሯል።

ዘመቻው በቅርቡ ከተካሄደባቸው ት/ቤቶች መካከል በዶንኮርክሮም የሚገኙት የቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አታኮራ መሰረታዊ ትምህርት ቤት፣ የቅድስት ማርያም ሙያ እና ቴክኒክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም የአዴምራ እና ዶንኮርክሮም የግብርና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኙበታል።

የዘመቻዎቹ ዓላማ ተማሪዎቹን በየአካባቢያቸው የሚፈፀሙ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መስፋፋትን ለማስገንዘብ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ “ወንጀለኞቹ ኢላማቸውን ለማግኘት ስለሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ዘዴዎች እናስተምራቸዋለን” ያሉት ሲስተር ጆይ “አጭበርባሪዎቹ ሰለባዎቻቸውን በከተሞች ውስጥ ሥራ እንደሚያገኙ በማስመሰል የተሳሳተ ተስፋ እንደሚሰጡዋቸው እና ወደ ቤታቸው ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን ለመንከባከብ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንደሚቆጥቡ ያሳምኗቸዋል” በማለት አብራርተዋል።

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት ውስጥ ያሉትን አንዳንድ አደጋዎች በመጥቀስ፥ ተጎጂዎችን ለሴተኛ አዳሪነት፣ 'የዘመናዊ ባርነት' ተብሎ ለሚጠራው እና የትምህርት ዕድል እንኳን እንዳያገኙ ለሚያደርገው ቋሚ የቤት ሰራተኝነት ጀምሮ ለተለያዩ አደጋዎች እንደሚጋለጡ ያስረዱ ሲሆን፥ ቡድኑ በጎበኟቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

ሲስተር ጆይ ጉብኝታቸውን አስመልክተው “በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ በግዳጅ ጋብቻ እና በሌሎችም ወንጀሎች ለተጠረጠሩት ሰዎች ከለላ የሚሰጠውን አካል በማሳወቅ ነቅተው እንዲጠብቁ እና የወንድሞቻቸው ጠባቂ እንዲሆኑ መክረን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

የጋና ታሊታ ኩም ትስስር
ሲስተር ጆይ የገዳማዊያቱን ተስፋ እና ፀሎት ያካፈሉ ሲሆን፥ አንድ ቀን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በጋና ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ክፍሎች ድርጊቱ እንደሚያበቃ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የጋና ታሊታ ኩም ትስስር መጋቢት 2010 ዓ.ም. የተመሰረተ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፥ የተወሰኑ ምዕመናንን ጨምሮ ገዳማዊያን እህቶችን እና አባቶችን ያካትታል።

በጋና የሚገኙ ገዳማዊያት በጋና ገዳማዊያን የበላይ አለቆች ጉባኤ (CMSR-Gh) አስተባባሪነት እና ድጋፍ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ብዝበዛን ለመዋጋት እና ድርጅታዊ የትብብር ሞዴል ለመፍጠር በትምህርት ቤቶች እና በማህበረሰቦች ውስጥ ባሉ እንዲሁም 'አረንጓዴ ግጦሽ' ፍለጋ መንደሮችን ለቀው ሲወጡ ሊደርስ በሚችለው አደጋ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር የጥብቅና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በቅንጅት እና በትስስር ይሰራል።

በአሻንቲ ክልል ውስጥ በሚገኘው እንደ ኩማሲ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ገዳማዊያቱ ከተጎጂዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ስለ ችግሩ ስለሚያወሩ የታሊታ ኩም ትስስር ሥራውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰራ የተነገረ ሲሆን ፥ ነገር ግን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሩ በስፋት እየተካሄደባቸው ባሉ እና ተጎጂዎች ለተሻለ ክትትል ወደ ከተማ በሚላኩባቸው እንደ ዶንኮርክሮም ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች በተለየ መልኩ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል።
 

20 August 2024, 13:30