የደቡባዊ አፍሪካ ጳጳሳት ክልላዊ ስብስብ የ50 ዓመታት ልምዱን በመጠቀም ተልዕኮውን ያጠናክራል ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በደቡባዊ አፍሪካ ክልል የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ፍላጎትና የሁለተኛው የቫቲካን ምክር ቤት ትንቢታዊ ራዕይ ውጤት የሆነውን የዚህ ህብረት (ኢምቢሳ) ህልውናን ምክንያት በማድረግ የኢምቢሳ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አባ ራፋኤል ሶፓቶ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ህብረቱ ያለውን ተልዕኮ በማንሳት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አባ ራፋኤል ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “ኢምቢሳ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል የሚገባው እውነተኛ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ልምድ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ይህ ሊደረስበት የሚገባው የተቋቋመበት ዓላማ ሲሆን፥ ይህም በአካባቢው ያሉ ተግዳሮቶችን እና ችግሮችን በመጋፈጥ ሃዋሪያዊ አሰራር ልምድን ለመለዋወጥ እና የጥረቶች አንድነት መድረክ እንዲሆን ነበር የተቋቋመው ብለዋል።
ኢምቢሳ በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ የሚታየውን መንፈሳዊ እድገትን እንደሚገነዘብ ጠቁመው “በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሕያውነት ጉልህ ነው፣ ከ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለወጣቶች የበለጠ ትኩረት ሰጥተናል፣ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የክርስቶስ ሕያውነት” በሚለው ሃዋሪያዊ ጽሁፋቸው ላይ ከገለጹት ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል።
አባ ሶፓቶ አክለውም ከዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የክህነት እና የሃይማኖታዊ ሕይወት ጥሪዎች ቁጥር ነው፣ ይህም “የተቀበልነው እምነት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ያመለክታሉ” ብለዋል።
እየተካሄደ ባለው ሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ በመመሥረት ኢምቢሳን አጠናክሮ ወደፊት በመግፋት ሕብረተሰቡን የመቆጣጠር አዝማሚያ ካለው ግለሰባዊነትና ትምክህተኝነት ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
አባ ሶፓቶ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ “በክልሉ ደረጃ በተደረገው የጋራ ጥረት የተቸገሩትን በተለይም ስደተኞችን እና በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎችን በመንከባከብ ህብረቱ የተፈጠረበትን ግብ አሳክቷል” ብለዋል።
የ ኢምቢሳ (IMBISA) ጉልህ ሚና
በአንጎላ የሳውሪሞ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የኢምቢሳ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ሆሴ ማኑኤል ኢምባምባ በበኩላቸው ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢምቢሳ ሚና የማይካድ መሆኑን ገልጸው፥ የተገለሉ እና በጣም የተቸገሩ እንዲሁም የሰውን ልጅ እና 'የጋራ ቤታችንን' ክብር የሚጎዱ በደሎችን ሁሉ ለመከላከል ህብረቱ ጉልህ ጥረት አድርጓል ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ኢምባምባ አክለውም “ኢምቢሳ የሚያጋጥሙት ፈተናዎች ቢኖሩም ተልእኮውን ግን ሁሌም በንቃት ይፈጽማል፥ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ሃሳቦችን ለማጋራት፣ ለውይይት፣ ለኅብረት እና ለአብሮነት አስተማማኝ ቦታ መስጠቱን” በአጽንኦት በማንሳት፣ “ህብረቱ የተስፋ ትንቢታዊ ድምፅ ሆኗል” በማለት ገልጸዋል።
በተለይም በአመጽ፣ በፖለቲካ አለመቻቻል፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሃይማኖታዊ ቡድኖች ወረራ መረጋጋት በማይታይበት ክልላት ህብረቱ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ እና በወንጌል እሴቶች ላይ የተመሰረተ የሕይወትን ትክክለኛ ትርጉም እንዲያገኙ በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ኢምባምባ አክለው እንደገለጹት የክልሉ ብጹአን ጳጳሳት፣ ገዳማዊያን እና ምዕመናን ሁሉም ለቤተክርስቲያኑ ተልዕኮ ቁርጠኛ ናቸው ካሉ በኋላ፥ “ኢምቢሳ በቤተሰብ፣ በባህሎች እና በተቋማት መካከል ድልድይ የመገንባት ሚና እንዲወስድ እንፈልጋለን" ብለዋል።
“መንገዱ ረጅም ነው፣ ነገር ግን በእምነት፣ በተስፋ እና በበጎ አድራጎት ሥራ በመበረታታት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ እሴቶችን ወደ ተሻለ ነገር መለወጥ እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።
የጋራ አገልግሎት እና የላቀ ተልዕኮ
በሞሶቶ የሞሃሌ ሆክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጆን ትልሆሞላ እንደገለፁት ኢምቢሳ የተለያዩ ሃሳቦችን በማስተናገድ የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ደግሞ ብጹአን ጳጳሳት በኢምቢሳ ስብሰባዎች ተጠርተው እርስ በእርሳቸው ሃሳብ እንዲካፈሉ እና እንዲደማመጡ፣ የሀገራቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች መሰረት በማድረግ እንዲሁም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንደተጠቀሰው “የጋራ መኖሪያችን” ስለሆነችው ምድራችን ጉዳይ ላይ ውይይቶችን ስለሚያደርጉ ነው” ብለዋል።
ብጹእነታቸው ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “ይህ ሃሳብን የማጋራት እድል እርስ በርስ መግባባትን፣ ትብብርን እና መተሳሰብን ያመጣል” በማለት አክለዋል።
በቃለ ምልልሱ ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ብጹእ አቡነ ትልሆሞላ፣ የኢምቢሳ አባላት ከራሳቸው ሀገረ ስብከት ወሰን አልፈው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፍላጎትና ወደ አንድ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ለሚደረገው ጉዞ ትኩረት በመስጠት ተልእኮውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። ከዚህም ባለፈ “እኛ በደቡባዊ አፍሪካ የምንገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ አንድ ማህበረሰብ ለማደግ፣ ለማገልገል እና ለመጎልበት ታሪካችንን የምናስተላልፍ ነን” ለሚለው መሪ ቃላችን እውነተኛ ምስክር መሆን አለብን ብለዋል።
“በክልሉ ውስጥ ላለው ሰፊ ራዕይ እና ታላቅ ተልእኮ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ ምእመናን ለበለጠ እና ለተሻለ ዓላማ ተባብረው መስራት አለባቸው” በማለትም ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሩስተንበርግ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሮበርት ምፊዌ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢምቢሳ አባላት ጋር በህብረት እና በመተሳሰብ መንፈስ እንዳሳለፉ ተናግረው፥ “እውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ፣ ደግነት እና የጋለ አቀባበል ከሁሉም ብጹአን ጳጳሳት፣ ከፍተኛ ጳጳሳት እና በቅርቡ ከተሾሙት ጭምር አግኝቻለሁ” ብለዋል።
የኢምቢሳ ምስረታ ጥረቶችን፣ የማስተዋል ችሎታ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን በተመለከተ፣ “ሁልጊዜም የሚሰማኝ እውነተኛ አሳቢነት፣ ቁርጠኝነት እና የብጹአን ጳጳሳት እርስ በርስ እና ለሚያገለግሉት ሰዎች ያላቸውን ትብብር ነው” በማለት ገልጸዋል።
ህብረቱ ከስኬቶቹ አንዱ በቅርቡ የተሾሙ ጳጳሳት በአእምሮ ጤና ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተካሄደ ያለው አደረጃጀት መሆኑን ጠቅሰው፥ “እንደ ብጹአን ጳጳሳት በሕይወታችን ውስጥ በሥነ ልቦናዊ ማኅበራዊ እንክብካቤ ላይ እናሰላስላለን፣ እንዲሁም በካህናቶች እና በተቀደሰ ህይወት ውስጥ ስላሉ ሰዎች እንመክራለን፥ ከዚህም በተጨማሪ ኢምቢሳ አዲስ ጳጳሳት የአገልግሎት ልምዳቸውን ለማካፈል የሚችሉበት አስተማማኝ ቦታ ይፈጥራል” ብለዋል።
ብጹእ አቡነ ምፊዌ እንደገለፁት በክልሉ ያሉ የካቶሊክ ማህበረሰብን አንድ ለማድረግ በቤተክርስቲያኒቱ አመራር ደረጃ በአውደ ጥናቶች፣በሲምፖዚየሞች እና በኮንፈረንሶች የቤተክርስቲያኒቱ አመራሮችን በማሰባሰብ በክልሉ ውስጥ በሚነሱ በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተጨባጭ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል” ብለዋል።
ኢምቢሳ የደቡባዊ አፍሪካን ቤተክርስትያን በሰፊ ርቀት በማገናኘት ቤተክርስቲያን በፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ ውጥረቶች ላይ በመሳተፍ በአካባቢው ትርጉም ያለው ሚና መጫወት የምትችልበትን መንገድ ለማንፀባረቅ እና ለመለዋወጥ ጠቃሚ መድረክ ሆኖ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
ብጹእ አቡነ ምፊዌ በማጠቃለያቸውም፣ በክልሉ ያለውን አወንታዊ ለውጥ ለማጎልበት እና አስተዋፅዖ ለማድረግ የወደፊቱ ጊዜን አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት “ቤተክርስቲያኑ የምእመናንን በተለይም የወጣቶችን ድምጽ እና ተሳትፎ ማጎልበት አለባት” ካሉ በኋላ፣ “አዲስ ራዕይን ማንቀሳቀስ በምእመናን በተለይም ለክልሉ ወጣቶች የውይይት እና የሃሳብ ልውውጥን የሚያመቻቹ የህብረቱን መዋቅሮችን በማጠናከር ላይ ማተኮር አለበት፥ ምክንያቱም ያለ ምእመናን ድምጽ እና ትብብር ምንም አይነት እድገት ልናሳይ አንችልም” ሲሉ ደምድመዋል።
ስለ ኢምቢሳ (IMBISA)
የደቡባዊ አፍሪካ ጳጳሳት ክልላዊ ስብስብ በብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች መካከል እንደ አገናኝ እና የሃዋሪያዊ ሥራ ትብብር ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ በ9 አገሮች እና በ6 ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ማለትም የአንጎላ፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (CEAST)፣ የሌሶቶ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ (LCBC)፣ የሞዛምቢክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (CEM)፣ የናሚቢያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ (NCBC)፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና እስዋቲኒን የሚያካትተው የደቡብ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤዎች (SACBC) እና የዚምባብዌ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ (ZCBC) የተዋቀረ ነው።
ክልሉ ከብጹአን ካርዲናሎች፣ ተባባሪ እና ረዳት ጳጳሳት በተጨማሪ እያንዳንዳቸው በብጹአን ጳጳሳት የሚመሩ 75 ሃገረ ስብከቶችን ያቀፈ ነው።