ፈልግ

በመላው ኢንዶኔዥያ የሚገኙ የሀገረ ስብከት ካህናት በኢንዶኔዥያ ሃገረስብከት ካህናት ማህበር ባዘጋጀው ቀጣይነት ያለው የምሥረታ መርሃ ግብር ላይ፥ ኢንዶኔዥያ፣ ነሃሴ 2016 ዓ.ም. በመላው ኢንዶኔዥያ የሚገኙ የሀገረ ስብከት ካህናት በኢንዶኔዥያ ሃገረስብከት ካህናት ማህበር ባዘጋጀው ቀጣይነት ያለው የምሥረታ መርሃ ግብር ላይ፥ ኢንዶኔዥያ፣ ነሃሴ 2016 ዓ.ም.  

የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት መንፈሳቸውን የሚያጠናክሩበት መርሃ-ግብር አካሄዱ

ከኢንዶኔዥያ የተውጣጡ ሃምሳ ስድስት የሀገረ ስብከት ካህናት በኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበር (UNINDO) አማካይነት በማዕከላዊ ጃቫ በምትገኘው በዮጊያካርታ ከተማ በተዘጋጀው አገር አቀፍ የምስረታ ፕሮግራም ላይ ተሳትፈዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በካህናት መካከል የጠነከረ ወንድማማችነት እና ትስስር ለመፍጠር ያለመው ይህ መርሃ ግብር፡ ‘በሀገረ ስብከቱ ካህናት መካከል የወንድማማችነት እና የካህናት ግንኙነትን ማሳደግ፡ ራስን እና ሌሎችን በማወቅ የተሻለ ካህን እንሁን’ በሚል መሪ ቃል ላይ ተመስርቶ የተካሄደ ነበር።

መርሃግብሩ በሃምሌ ወር መጨረሻ ላይ የሚካሄደው እና የዓመታዊ ተከታታይ ክፍል አካል ሲሆን፥ ማዕረገ ክህነታቸውን ከተቀበሉ ከአንድ እስከ አስር ባሉ ዓመታት ውስጥ ለሚገኙ ካህናት መንፈሳዊ “የመሞላት” ክፍለ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

በምስራቅ ኑሳ ተንጋራ የሚገኘው የኩፓንግ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበር ፕረዚዳንት አባ ማክሲ ኡን ብሪያ እንደተናገሩት መርሐ ግብሩ በካህናቶች መካከል ያለውን አንድነት ለማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ በማጉላት፥ “ይህ በደርዘን የሚቆጠሩ የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት በሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አስደሳች ድባብን የሚያጎለብት ለመንፈሳዊ እድሳት የሚሰበሰቡበት ሀገር አቀፋዊ ዝግጅት ነው” ብለዋል።

ፕሮግራሙ እንዲዘጋጅ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት የሳናታ ድሀርማ ዩንቨርስቲ የስነ ልቦና መምህር የሆኑት አባ ጳውሎስ ኤርዊን ከሁለቱ የአሰልጣኞች አማካሪ ከሆኑት ማርቆስ ማርዲየስ እና ቤቤት ዳርማዋን ጋር በመሆን እንደሆነም ተገልጿል።

ስብሰባው ባሳየው በጎ ተጽእኖ በተሳታፊዎች በኩል ከፍተኛ ምስጋና የተቸረው ሲሆን፥ ከፓፑዋ ክልል የቲሚካ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት አባ ሲልቬስተር ዶሞጎ እና በምዕራብ ካሊማንታን የሚገኘው የኬታፓንግ ሀገረ ስብከት ካህን አባ ዩስሪ ባስሪ እንደተናገሩት ዝግጅቱ ለካህናቱ የአገልግሎት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሚሰጠውን ጥቅም በመግለጽ ሐሳቡን አስተጋብተዋል።

በአባ ጄፍ ዋይ ቡሌ እና አባ ኢማን አኖ የሚመራው አዘጋጅ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ 56ቱ ተሳታፊ ካህናት ከመላ አገሪቱ ከሚገኙ 30 አህጉረ ስብከት የተውጣጡ መሆናቸውን የገለፀ ሲሆን፥ ነገር ግን ሰባት ሀገረ ስብከቶች ራቅ ባሉ አካባቢዎች ባለው የሎጂስቲክስ ችግር ምክንያት ተወካዮቻቸውን መላክ ሳይችሉ መቅረታቸውን ገልጸዋል። አባ ማክሲ ኡን ብሪያ አክለውም እንደተናገሩት በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ላይ በኩፓንግ ሃገረስብከት ውስጥ ተመሳሳይ የካህናት ምሥረታ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበር አጭር ታሪክ
እ.አ.አ. በ 1955 ዓ.ም. በሴማራንግ ሃገረስብከት ውስጥ የተመሰረተው የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበር፣ በኢንዶኔዥያ ላሉ የሀገረ ስብከት ካህናት ትልቅ ፋይዳ ያለው ብሄራዊ ድርጅት ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።

የማህበሩ የመጀመሪያ ሀገር አቀፍ ጉባኤ በ1977 ዓ.ም. በማዕከላዊ ጃቫ ውስጥ በሚገኘው ‘ሳላም ሀውስ’ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን፥ በወቅቱ የቡድኑን ሁኔታ የሚገልጽ ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች መጽደቁ ተገልጿል። እ.አ.አ. በ1983 ዓ.ም. በጃካርታ በተካሄደው ቀጣይ ጉባኤ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የሁሉም ሀገረ ስብከቶች ካህናት እንደተሳተፉበትም ተነግሯል።

በኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበር እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና ከተጫወቱት መሃል የኤሜሪተስ ኬታፓንግ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ብላሲየስ ፑጃርሃርጃ እና አባ ቫለንቲነስ ካርታሲዎጆ ይጠቀሳሉ። ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ አከባቢ በኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የሀገረ ስብከት ካህናት በአንዳንድ ሰበቦች ምክንያት ትንሽ ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆንም በእነዚህ ሁለት ሰዎች አማካይነት አሁን ላይ ትልቅ ተሳትፎ እንዳላቸው ተነግሯል።

የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበርን ታሪክ የሚገልጽ አዲስ መጽሐፍ
በሚቀጥሉት ወራት የኢንዶኔዥያ ጳጳሳት ጉባኤ ተቋም በሆነው ኦቦር አሳታሚ ድርጅት በኩል የሚታተም የኢንዶኔዥያ ሀገረ ስብከት ካህናት ማኅበርን ታሪክ የሚገልጽ አዲስ መጽሃፍ እንደሚወጣ ተገልጿል።
 

13 August 2024, 12:37