ፈልግ

መስከረም 2015 ዓ.ም. በደረሰው ከባድ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት አደጋ የደረሰባት በሰሜናዊ ኢራቅ ውስጥ የምትገኘው ዋናዋ የክርስቲያኖች ከተማ ቃራቆሽ መስከረም 2015 ዓ.ም. በደረሰው ከባድ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት አደጋ የደረሰባት በሰሜናዊ ኢራቅ ውስጥ የምትገኘው ዋናዋ የክርስቲያኖች ከተማ ቃራቆሽ  (AFP or licensors)

የኢራቁ ብጹእ ካርዲናል ሳኮ በሃገሪቷ እየተፈፀመ ያለው ክፋት ዘላቂ አይደለም አሉ

እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን ክርስቲያኖችን እና ያዚዲስቶችን (በኢራቅ የሚገኙ ኩርዶች) ከጨፈጨፈ 10 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ የባግዳድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ካርዲናል ሳኮ ቀኑን አስመልክተው ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት መከራ ሁሉንም ኢራቃውያን አንድ እንደሚያደርጋቸው ገልጸው “ሁላችንም ለእያንዳንዳችን ተጠያቂዎች ነን፣ ስንሞትም አምላክ ክርስቲያን ወይም ሙስሊም መሆኔን አይጠይቅም፥ ከዚህ ይልቅ 'ለወንድምህ ምን አደረግህለት?' የሚለውን ጥያቄ ነው የሚጠይቀን” ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከአሥር ዓመታት በፊት፣ ሃምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት ላይ 120,000 የኢራቅ ክርስቲያኖች ራሱን ኢስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ቡድን ያደረሰውን ጥቃት በመሸሽ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ከዚህም በላይ ኢራቅ ውስጥ የሚኖሩ ኩርዶችን (ያዚዲስቶችን) ለማጥፋት ሙከራ ተደረጓል። ከ3,000 በላይ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወንድ እና ሴት ህፃናት ተገድለዋል፥ በትንሹ 6,800 የሚሆኑ ሰዎች በተለይም ሴቶች፣ ወንድ እና ሴት ልጆች እስላማዊ መንግስት በሚባለው አክራሪ ቡድን ታፍነው ተወስደዋል። ይህ ጥቃት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ ዘር ማጥፋት ተደርጎ እውቅና ተሰጥቶታል።

የባግዳድ የከላዳውያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ይህ ለኢራቅ ሕዝብ “የጋራ አሳዛኝ ክስተት” እንደነበር በመግለጽ፥ “በሃገሪቱ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ የማይረሳ፣ ክርስቲያኖችንና ሌሎች አናሳዎችን ለጥቃት የዳረገ አሳዛኝ ክስተት ነው፥ ኢስላማዊው መንግስት መሸነፉ እርግጥ ቢሆንም፥ ነገር ግን ርዕዮተ- ዓለሙ አሁንም በኢራቅ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ዘንድ በስፋት ይራመዳል” ብለዋል። ቃለ ምልልሱ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጥያቄ፡- ከአሥር ዓመት በፊት በኢራቅ ክርስቲያኖች እና በሌሎች አናሳ ወገኖች ላይ ከደረሰው አደጋ ዛሬ የቀረው ምንድን ነው?

ፓትርያርክ ሳኮ፦ ሰዎች ለመጪው ጊዜ ብዙም እምነት የላቸውም። በመጨረሻ ሁሉም ሰው እኩል መብትና ግዴታ ያለው ዜጋ የሚሆንበት ዘመናዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ሲቪል መንግስት የሚኖረን መቼ ነው? በማለት ሁሉም ሰው ራሱን ይጠይቃል፥ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎች ኢራቅን ለቀው የሚሸሹት ለዚህ ነው። ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ለመነጋገር እሞክራለሁ፣ ይህ መጥፎ ድርጊት እንደማይቆይ እና ታጋሽ መሆን እንዳለባቸው አረጋግጥላቸዋለሁ።

ጥያቄ፡- በነነዌ ከተማ ክርስቲያኖች አለመኖራቸው ለኢራቅ ምን ማለት ነው?

መልስ፦ ክርስቲያኖች ለደህንነታቸው መፍራታቸውን ቀጥለዋል፥ ምክንያቱም ሀገሪቱ የተረጋጋች ስላልሆነች ብሎም በሃገሪቱ ውስጥ በቁጥር አናሳ ናቸው፥ ከዚህም በተጨማሪም እያንዳንዱን ሰው በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ቀውስ ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ ውጥረቶች ያሳስባቸዋል።

ጥያቄ፦ መላው ህዝብ በዚህ ስጋት እየተሰቃየ ነው ብለው ያስባሉ?

መልስ፦ የነነዌ ከተማ ክርስቲያኖችም ሆኑ ያዚዲስቶች ፈርተዋል። ጦርነትና በቀልን መሠረት ያደረገ አስተሳሰብ መቀየር አለብን። እንዴት መነጋገር እና ችግሮችን በትጥቅ ሳይሆን በውይይት መፍታት እንደሚቻል መማር አለብን፥ ጥልቅ እና ግልጽ ውይይት መደረግ አለበት። ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን፣ ቋንቋን፣ ሰዎች የሚያደርጓቸውን ንግግሮች መለወጥ አለብን።

ጥያቄ፦ ለገለጹት ሁኔታ ምዕራባውያንም ተጠያቂ ናቸው?

መልስ፦ ብቸኛው መፍትሔ ጦርነት ነው ብለው የሚያስቡት ምዕራባውያን በተወሰነ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ቸልተኛ ናቸው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንዳሉት፡ በጦርነት መቼም ቢሆን ድል አይገኝም፥ ሁሉም ሰው ተሸናፊ ነው!
የምዕራቡ ዓለም ችግር ግዴለሽነት ነው። ሁሉም ሰው በትርፍ አመክንዮ ላይ ያተኮረ ነው፥ ከዚህም ባለፈ የሞራል እና የመንፈሳዊ እሴቶች ይጎድለዋል፥ ለዚህም ማሳያ በዩክሬን እየሆነ ያለውን ነገር ማየት እንችላለን። ያሳዝናል!

ጥያቄ፡- ዛሬ ላይ ያለው የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ያጋጠመው፣ እንዲሁም በያዚዲዎች ላይ በኢስላሚክ መንግስት ተብዬው እጅ የደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል ምን ያስተምረናል?

መልስ፦ ይህንን ትውስታ በጭራሽ ለመሰረዝ ቀላል አይሆንም። ባለፈው ዓመት በቃራቆሽ ከተማ በሠርግ ሥነ ስርዓት ላይ በተፈፀመው ጥቃት ከ133 በላይ ሰዎች የሞቱበት ጥቃቶችን የመሳሰሉ በርካታ የጥላቻ ድርጊቶች አሁንም ቀጥለዋል። በተጨማሪም በያዚዲያቶች ላይ በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምክንያት... በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች የሌላ ጎሳ አባላት ስለሆኑ ብቻ ተሽጠው ከቤተሰቦቻቸው እንደሚለያዩ እንዴት መገመት ይቻላል? እዛ ምን እሴቶች አሉ ብለህ ታስባለህ? ይህ ለኛ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ አይነት ነገሮች እንዳይከሰቱ መከላከል ለማይችል ዓለም ሁሉ ይህ በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው።

ጥያቄ፡- በኢራቅ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው የዓለሙ ማህበረሰብ ዓይኑን እንዲከፍት የሚያስተላልፉት መልዕክት አለዎት?

መልስ፦ በሰብአዊነት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርሳት የለብንም ብዬ አስባለሁ፥ እኛ ወንድማማቾች ነን፣ ህይወት አስደናቂ ነገር ነው። በኢራቅም ሆነ በሌላ ቦታ ሰዎች ምንም ሳያደርጉ እንዲሞቱ መፍቀድ አይገባም። እያንዳንዳችን ስለሌሎች ተጠያቂዎች ነን፥ ስንሞትም አምላክ ክርስቲያን ወይም ሙስሊም መሆኔን አይጠይቅም፥ ከዚህ ይልቅ 'ለወንድምህ ምን አደረግህለት?' የሚለውን ጥያቄ ነው የሚጠይቀን።
 

09 August 2024, 14:58